የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ 12

12
1“የእስራኤል ሕዝብ ነፋስን ለመጨበጥ በመሞከርና ቀኑን ሙሉ የምሥራቅ ነፋስን ሲያሳድዱ በመዋል ከንቱ ሆነዋል፤ ሐሰትንና ዐመፅን ያበዛሉ፤ ከአሦር ጋር ይዋዋላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የወይራ ዘይትን ወደ ግብጽ ይልካሉ።”
2እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ የሚያቀርበው ወቀሳ አለው፤ የያዕቆብንም ልጆች እንደ አካሄዳቸው ይቀጣቸዋል፤ ባደረጉትም ክፉ ሥራ መጠን ዋጋቸውን ይከፍላቸዋል። 3ያዕቆብ ገና በማሕፀን ሳለ የመንትያ ወንድሙን ለመቅደም ተረከዙን ያዘ፤ ካደገም በኋላ አምላክን ይዞ “አለቅም” አለ፤ #ዘፍ. 25፥26። #ዘፍ. 32፥24-26። 4ከመልአኩም ጋር ታግሎ በረታ፤ አልቅሶም ምሕረትን ለመነ፤ ሌላ ጊዜም በቤትኤል የተገኘው እግዚአብሔር እኛን አነጋገረን። #ዘፍ. 28፥10-22። 5እግዚአብሔር የሠራዊት አምላክ የመታወቂያው ስሙ እግዚአብሔር ነው። 6ስለዚህ እናንተ ወደ አምላካችሁ ተመለሱ፤ ፍቅርንና ትክክለኛ ፍትሕን አጥብቃችሁ ያዙ፤ አምላካችሁ እስኪረዳችሁ በትዕግሥት ጠብቁ።
ተጨማሪ የፍርድ ውሳኔ
7እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስራኤላውያን ሐሰተኛ ሚዛን በእጃቸው እንደሚገኝ እንደ ከነዓናውያን ነጋዴዎች ሆነዋል፤ በእርሱም ያታልሉበታል፤ 8‘እስራኤል እኔ ባለጸጋ ሆኛለሁ፤ በሀብቴም ማንም ሰው በእኔ ላይ በደል ወይም ኃጢአት አያገኝብኝም’ ብሎ ይፎክራል። 9ነገር ግን ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በዳስ በዓል ጊዜ በድንኳን እንደምትኖሩ ዐይነት፥ እንደገና ተመልሳችሁ በድንኳን እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ። #ዘሌ. 23፥42-43።
10“አስቀድሜ በነቢያት አንደበት ተናግሬአለሁ፤ ብዙ ራእይም አሳይቻለሁ፤ በነቢያቱም አማካይነት በምሳሌ ተናግሬአለሁ፤ 11ይህም ሁሉ ሆኖ በገለዓድ ለጣዖት ይሰግዳሉ፤ ለጣዖት የሚሰግዱት ግን ከንቱ ይሆናሉ፤ በጌልገላ ወይፈኖችን ለመሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ነገር ግን መሠዊያዎቻቸው ተሰባብረው በእርሻ መካከል የድንጋይ ክምር ሆነው ይቀራሉ።”
12የቀድሞ አባታችን ያዕቆብ ወደ መስጴጦምያ ሸሽቶ ሄደ፤ እዚያም ሚስት ለማግኘት ሲል የበጎች እረኛ ሆኖ አገለገለ። #ዘፍ. 29፥1-20። 13እግዚአብሔር በላከው ነቢይ አማካይነት የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ መርቶ አወጣቸው፤ በዚያም ነቢይ አማካይነት ተንከባከባቸው። #ዘፀ. 12፥50-51። 14ይሁን እንጂ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን እጅግ አስቈጡት፤ በበደላቸውም ይጠየቁበታል፤ ስሙንም ስለ ሰደቡ ይፈርድባቸዋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ