የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ 13

13
በእስራኤል ላይ የተወሰነ የመጨረሻ ፍርድ
1የኤፍሬም ነገድ በእስራኤል ሕዝብ ላይ ከፍ ብሎ በነበረበት ዘመን ሲናገር የሚሰሙት ሁሉ ይንቀጠቀጡ ነበር፤ በኋላ ግን ባዓል ለተባለ ጣዖት በመስገድ ኃጢአት ስለ ሠራ በሞት ተቀጣ። 2አሁንም በጥበባቸው የቀለጡ ምስሎችና በብር የተሠሩ ጣዖቶችን በመሥራት በኃጢአት ላይ ኃጢአትን ይጨምራሉ፤ እነዚህ ሁሉ የሰው እጅ ሥራ ናቸው፤ ለእነዚህም የሰው እጅ ሥራዎች መሥዋዕት አቅርቡ ይላሉ፤ ሰዎችም በጥጃ መልክ የተሠሩ ጣዖቶችን ይሳለማሉ። 3በዚህም ምክንያት እነርሱ እንደ ማለዳ ጉም ተነው ይጠፋሉ፤ እንደ ጠዋት ጤዛም ይረግፋሉ፤ ከአውድማ ላይ በዐውሎ ነፋስ እንደሚጠረግ እብቅ ወይም በጢስ መውጫ ወጥቶ እንደሚያልቅ ጢስ ይሆናሉ።
4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ አምላካችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የላችሁም፤ አዳኛችሁም እኔ ብቻ ነኝ። 5ድርቅ በበዛበት በረሓ እንክብካቤ ያደረግኹላችሁ እኔ ነኝ። 6ነገር ግን ወደ መልካሚቱ ምድር በገባችሁ ጊዜ እስክትጠግቡ በልታችሁ እጅግ ታበያችሁ፤ እኔንም ረሳችሁ። #ዘዳ. 8፥11-17። 7ከዚህ የተነሣ እንደ አንበሳና በመንገድ እንደሚያደባ ነብርም እሆንባችኋለሁ። 8ግልገሎችዋ የተወሰዱባት ድብ እንደምታደርግ እኔም አደጋ እጥልባችኋለሁ፤ እቦጫጭቃችሁማለሁ፤ እንደሚባላ አንበሳ እሆንባችኋለሁ፤ እንደሚበጣጥስ ክፉ አውሬም እበጣጥሳችኋለሁ።
9“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! በእኔ በምረዳችሁ ላይ ስለ ተነሣችሁ አጠፋችኋለሁ፤ 10እናንተ ንጉሥና መሪዎች እንድሰጣችሁ ጠይቃችሁ ነበር፤ ታዲያ አሁን የሚያድናችሁ ንጉሥ፥ የሚከላከሉላችሁስ መሪዎች የት አሉ? #1ሳሙ. 8፥5-6። 11በቊጣዬ ነገሥታትን ሰጥቻችሁ ነበር፤ ነገር ግን በከፍተኛ ቊጣዬ አጠፋኋቸው። #1ሳሙ. 10፥17-24፤ 15፥26።
12“የእስራኤል ኃጢአትና በደል ተጽፎ ተከማችቶአል። 13እስራኤል በሕይወት የመኖር ተስፋ አለው፤ ነገር ግን የሚወለድበት ጊዜ ሲቃረብ ከእናቱ ማሕፀን ለመውጣት እንደማይፈልግ ሕፃን ሞኝ ሆኖአል። 14ከሲኦል ኀይል እታደጋቸዋለሁን? ከሞትስ አድናቸዋለሁን? ሞት ሆይ! መቅሠፍቶችህ የት አሉ? ሲኦል ሆይ! አጥፊነትህ የት አለ? እኔኮ አልራራላቸውም፤ #1ቆሮ. 15፥55። 15በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆንም የእግዚአብሔር ቅጣት የሆነው የምሥራቁ ነፋስ ከምድረ በዳ ተነሥቶ ይመጣል፤ ምንጩ ይቆማል፤ ወንዙም ይደርቃል። ነፋሱም የነበሩትን ውድ ዕቃዎች ሁሉ ገፎ ይወስድበታል። 16ሰማርያ በእኔ ላይ በማመፅዋ በሠራችው በደል ተጠያቂ ትሆናለች፤ ሕዝብዋም በጦርነት ይሞታሉ፤ ሕፃናት በምድር ላይ ይፈጠፈጣሉ፤ እርጉዞችም ሆዳቸው ይሰነጠቃል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ