ትንቢተ ሆሴዕ 4
4
እግዚአብሔር እስራኤልን መውቀሱ
1በዚህች ምድር በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ወቀሳ አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እርሱ የሚልህን ሁሉ ስማ፦ “በምድሪቱ ላይ ታማኝነትና ፍቅር እግዚአብሔርንም ማወቅ ጠፍቶአል። 2በመሐላ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰው ይዋሻሉ፤ ይገድላሉ፤ ይሰርቃሉ፤ ያመነዝራሉም፤ ግፍና ግድያ እየበዛ ሄዶአል። 3በዚህም ምክንያት በምድሪቱ ላይ ድርቅ ይመጣል፤ በእርስዋ የሚኖሩ ሁሉ ይደክማሉ፤ እንስሶች፥ ወፎችና የባሕር ዓሣዎች ሁሉ ያልቃሉ።”
እግዚአብሔር ካህናትን መውቀሱ
4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የምወቅሰው እናንተን ካህናትን ስለ ሆነ ሕዝቡን የሚከስ ወይም የሚወቀስ አይኑር። 5እናንተ ካህናት ሆይ! በቀን ብርሃን ትደናበራላችሁ፤ ነቢያትም ሌሊት ከእናንተ ጋር በጨለማ ይደናበራሉ፤ ስለዚህ እናት አገራችሁን አጠፋታለሁ። 6ሕዝቤ እኔን በሚገባ ካለማወቁ የተነሣ ጠፍቶአል፤ እናንተ እኔን ለማወቅ ስላልፈለጋችሁ እኔም ካህናት ሆናችሁ እንድታገለግሉኝ አልፈልጋችሁም፤ ሕጌንም ስላቃለላችሁና ስለ ረሳችሁ ልጆቻችሁ በእኔ ዘንድ የተረሱ ይሆናሉ።
7“እናንተ ካህናት ቊጥራችሁ በበዛ መጠን በደላችሁም በፊቴ እየበዛ ሄዶአል፤ ስለዚህ ክብራችሁን ገፍፌ አዋርዳችኋለሁ። 8የሕዝቤ ኃጢአት ለእናንተ መበልጸጊያ በመሆኑ ሕዝቡ ኃጢአትን አብዝተው እንዲሠሩ ትፈልጋላችሁ። 9እናንተ ካህናት እንደ ሕዝቡ ሆናችኋል፤ ስለዚህ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ቅጣት በእናንተም በካህናት ላይ ይደርሳል፤ የክፉ ሥራችሁንም ብድራት ትከፍላላችሁ። 10ሕዝቤ እኔን እግዚአብሔርን ስለ ተዉ፥ ይበላሉ አይጠግቡም፤ በአሕዛብ መስገጃ ቦታዎች ያመነዝራሉ፤ ግን ልጆችን አይወልዱም።”
እግዚአብሔር ባዕድ አምልኮን መቃወሙ
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የዝሙት ሥራ፥ የቈየና አዲስ የወይን ጠጅን መከተል የሕዝቤን አእምሮ አጥፍቶአል። 12ስለዚህ ከእንጨት የተሠራውን ጣዖት ምክር ይጠይቁታል፤ የጥንቈላ ዘንጋቸውም ለጥያቄአቸው መልስ የሚሰጥ ይመስላቸዋል፤ በዝሙት መንፈስም ተመርተው ከእግዚአብሔር ርቀዋል። 13በየተራራው ላይ መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ በየኮረብታው ላይ ቊርባን ያቀርባሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ታላላቅ በሆኑና ቅርንጫፋቸው በተንሰራፋ ጥላቸው መልካም በሆነ ዋርካ፥ በለሳና ጥድ ሥር ነው። በዚህ ምክንያት ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያን ይሆናሉ። ምራቶቻችሁም ያመነዝራሉ። 14ይሁን እንጂ ሴቶች ልጆቻችሁ ዘማውያት ምራቶቻችሁም አመንዝሮች ስለ ሆኑ አልቀጣቸውም፤ ምክንያቱም እናንተ ወንዶች ራሳችሁ በቤተ መቅደስ የሚሴስኑ ሴቶችን ተከትላችሁ ከእነርሱ ጋር ባዕድ አምልኮ ትፈጽማላችሁ፤ ስለዚህ ማስተዋል የጐደለው ሕዝብ ይጠፋል።
15“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እናንተ ብታመነዝሩም እንኳ የይሁዳ ሕዝብ በደለኛ እንዲሆን አታድርጉ፤ ወደ ጌልጌላ ወይም ወደ ቤትአዌን አትሂዱ፤ ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብላችሁም አትማሉ። #4፥15 ቤትአዌን፦ “የክፋት ቤት” ማለት ሲሆን ለቤትኤል የተሰጠ የአሽሙር ስም ነው። 16የእስራኤል ሕዝብ እንደ እልኸኛ ጊደር እምቢተኞች ሆነዋል፤ ታዲያ እግዚአብሔር እነርሱን እንደ በግ ጠቦቶች በመልካም መስክ እንዴት ያሰማራቸዋል? 17የእስራኤል ሕዝብ ከጣዖት አምልኮ ጋር ስለ ተጣመሩ ተዉአቸው የፈለጉትን ያድርጉ። 18ብዙ የወይን ጠጅ ከጠጡ በኋላ የዝሙት ሥራቸውን ይቀጥላሉ፤ አለቆቻቸውም አሳፋሪ ነገሮችን ማድረግ አጥብቀው ይወዳሉ። 19እነርሱም በነፋስ ተጠርገው የሚወሰዱትን ያኽል ርቀው ይሄዳሉ፤ ለጣዖት በመሠዋታቸውም ያፍራሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997