ትንቢተ ኢሳይያስ 9
9
ወደፊት የሚነሣው የሰላም ንጉሥ
1እነዚያ የተሠቃዩት ግን ዳግመኛ ችግር አይደርስባቸውም።
በቀድሞ ዘመን የዛብሎንና የንፍታሌም ምድር ተዋርዳ ትኖር ነበር፤ በኋለኛው ዘመን ግን ከሜዲቴራኒያን ባሕር ምሥራቅ ጀምሮ እስከ ዮርዳኖስ ማዶ ያለው በተለይም አሕዛብ ሰፍረውበት የነበረው የገሊላ ምድር ክብርን ይጐናጸፋል። #ማቴ. 4፥15።
2በጨለማ ይኖር የነበረ ሕዝብ
እነሆ ታላቅ ብርሃን አየ፤
በሞት ጥላ አገር ውስጥ ለሚኖሩትም ሁሉ ብርሃን ወጣላቸው። #ማቴ. 4፥16፤ ሉቃ. 1፥79።
3አምላክ ሆይ! ሕዝብህን አበዛህ፤
በደስታም እንዲሞሉ አደረግሃቸው፤
ሰዎች መከር በሚሰበስቡበት፥
ወይም ምርኮ በሚካፈሉበት ጊዜ ደስ እንደሚላቸው
ሕዝብህም አንተ ባደረግኸው ነገር ደስ ይላቸዋል።
4በቀድሞ ዘመን ምድያማውያንን ድል እንዳደረግህ ሁሉ፥
አሁንም በሕዝብህ ላይ የተጫነውን የአገዛዝ ቀንበርና
በትከሻቸው ላይ የተቃጣውን በትር ሰባበርክ፤
ሕዝብህን በማስጨነቅ ይገዛ የነበረውን ድል አደረግህ።
5የወራሪ ጦረኞች ጫማና
በደም የተለወሰ ልብሳቸው ሁሉ
በእሳት ይጋያል።
እንደ ማገዶ ሆኖ ይቃጠላል።
6እነሆ ሕፃን ተወልዶልናል!
ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል!
እርሱም መሪ ይሆናል፤
ስሙም “ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥
የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ” ይባላል።
7ለንጉሣዊ ሥልጣኑ ወሰን የለውም፤
መንግሥቱም ዘለዓለማዊ ሰላም የሰፈነበት ይሆናል፤
ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም፥
እውነትና ፍትሕ የሰፈነበት መንግሥት
በዳዊት ዙፋን ላይ ተመሥርቶ እንዲጸና ያደርገዋል፤
የሠራዊት አምላክ ቅናት ይህን ለማድረግ ወስኖአል። #ሉቃ. 1፥32-33።
እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የሚቀጣ መሆኑ
8ጌታ የያዕቆብ ዘሮች በሆኑ በእስራኤል ሕዝብ ላይ የፍርድ ቃሉን ላከ፤ ፍርዱም ተግባራዊ ይሆናል። 9የእስራኤል ሕዝብና በሰማርያ ከተማም የሚኖሩ ሁሉ ይህን ያደረገ እግዚአብሔር መሆኑን ያውቃሉ፤ ሆኖም፥ ትዕቢተኞችና እልኸኞች ሆነው እንዲህ ይላሉ፦ 10“ከጡብ የተሠሩ ግንቦች ፈርሰዋል፤ እኛ ግን እንደገና በጥርብ ድንጋይ እንገነባቸዋለን፤ ከሾላ ግንድ የተሠሩ ምሰሶዎች ተሰብረዋል፤ እኛ ግን በምርጥ የሊባኖስ ዛፍ እንተካቸዋለን።”
11ስለዚህ እግዚአብሔር ተቀናቃኞችን በእነርሱ ላይ ያስነሣባቸዋል፤ ጠላቶቻቸውንም በእነርሱ ላይ ያነሣሣባቸዋል። 12እርሱ ከምሥራቅ ሶርያውያንን፥ ከምዕራብ ፍልስጥኤማውያንን ልኮ እስራኤልን እንዲወሩ አደረገ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ቊጣው አልበረደም፤ ስለዚህ እጁ እነርሱን ለመቅጣት እንደ ተቃጣ ነው።
13ሕዝቡ ግን ወደ ቀጣቸው አምላክ አልተመለሱም፤ ወይም የሠራዊት አምላክን የሚሹ ሆነው አልተገኙም። 14ስለዚህ እግዚአብሔር በአንድ ቀን እንደ ራስና እንደ ጅራት እንደ ዘንባባውና እንደ ቅርንጫፉ የሚቈጠሩትን ከእስራኤል ይቈርጣል። 15ራስ የተባሉት ሽማግሌዎችና የተከበሩ አለቆች ናቸው፤ ጅራት የተባሉትም ሐሰትን የሚያስተምሩ ነቢያት ናቸው። 16ይህን ሕዝብ የሚመሩት ሁሉ አሳስተውታል፤ ሕዝቡም ከመንገድ ወጥቶ ባዝኖአል። 17ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ወጣቶቻቸውን ይቀጣል፤ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶችና አሳዳጊ ለሌላቸው ለሙት ልጆቻቸው አይራራም፤ ሁሉም እያንዳንዱ ከሐዲና ክፉ አድራጊ ሆኖአል፤ ከእያንዳንዱም ሰው አንደበት የሚነገረው ቃል ተንኰል የሞላበት ነው፤ ይህም ሁሉ ሆኖ የእግዚአብሔር ቊጣ ገና አልበረደም፤ ስለዚህ እነርሱን ለመቅጣት እጁ እንደ ተቃጣ ነው።
18የሕዝቡ ክፋት ኲርንችቱንና እሾኹን እንደሚያቃጥል እሳት ነው፤ እንደ በረሓ እሳት ደኑን በሚያቃጥልበት ጊዜ ጢሱ ተትጐልጒሎ ሲወጣ ቀጥ ብሎ የቆመ ዐምድ ይመስላል። 19የሠራዊት አምላክ ተቈጥቶአል፤ የቅጣቱም ፍርድ በአገሪቱ በሞላ እንደ እሳት ይነዳል፤ ሕዝቡም እንደ ማገዶ ይሆናል፤ ወንድም ለወንድሙ አይራራም። 20በአንድ በኩል ሆዳቸው እስኪሞላ ይበላሉ፤ ነገር ግን እንደ ተራቡ ናቸው፤ እንዲሁም በሌላ በኩል አግበስብሰው ይውጣሉ፤ ነገር ግን አይጠግቡም፤ የልጆቻቸውን ሥጋ እንኳ እስከ መብላት ይደርሳሉ። 21ይኸውም ምናሴ ኤፍሬምን፥ ኤፍሬምም ምናሴን ይወረዋል፤ ሁለቱም ነገዶች ተባብረው በይሁዳ ላይ ይዘምታሉ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ የእግዚአብሔር ቊጣ ገና አልበረደም፤ ስለዚህ እነርሱን ለመቅጣት እጁ እንደ ተሰነዘረ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 9: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997