መጽሐፈ መሳፍንት 1
1
የይሁዳና የስምዖን ነገዶች አዶኒቤዜቅን መማረካቸው
1ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ “በከነዓናውያን ላይ አደጋ ለመጣል ከነገዶቻችን መካከል ተቀዳሚ ሆኖ ማን ይዝመት?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ።
2እግዚአብሔርም “የይሁዳ ነገድ ተቀዳሚ ሆኖ ይዝመት፤ እኔ ምድሪቱን ለእነርሱ አሳልፌ እሰጣለሁ” አለ።
3የይሁዳ ነገድ ሕዝቦች ወንድሞቻቸውን የስምዖንን ነገድ ሕዝቦች “ለእኛ ወደ ተደለደለው ርስት በከነዓናውያን ላይ ለመዝመት ከእኛ ጋር አብረን እንሂድ እኛም ለእናንተ ወደተደለደለው ርስት አብረን እንሄዳለን” አሉአቸው። የስምዖን ነገድ ሕዝቦች ከእነርሱ ጋር ሄዱ። 4ከዚያ በኋላ የይሁዳ ሕዝብ አብሮ ዘመተ። እግዚአብሔርም በከነዓናውያንና በፈሪዛውያን ላይ ድልን አቀዳጃቸው፤ እነርሱም በቤዜቅ ዐሥር ሺህ ሠራዊትን መቱ። 5በዚያም አዶኒቤዜቅን በቤዜቅ አግኝተው ከእርሱ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከነዓናውያንንና ፈሩዛውያንን ድል አደረጉአቸው። 6አዶኒቤዜቅም ከፊታቸው ሸሸ፤ እነርሱ ግን አባረው ከያዙት በኋላ የእጆቹንና የእግሮቹን አውራ ጣቶች ቈረጡ፤ 7አዶኒቤዜቅም “የእጆቻቸውና የእግሮቻቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡባቸው ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ ሥር ፍርፋሪ እየለቀሙ ይበሉ ነበር፤ በእነርሱ ላይ የፈጸምኩትን ግፍ ዛሬ እግዚአብሔር በእኔ ላይ መልሶ አመጣብኝ” ሲል ተናገረ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተወስዶ በዚያው ሞተ።
የይሁዳ ነገድ ኢየሩሳሌምንና ኬብሮንን እንደ ያዘ
8የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን በጦርነት ያዙአት፤ ሕዝብዋንም በሰይፍ ፈጁ፤ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉ። 9ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሰዎች በተራራማው አገር፥ በኔጌብና በቈላማው አገር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ዘመቱ። 10የይሁዳ ሰዎች በኬብሮን በሚኖሩ ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ኬብሮን ቀድሞ ኪርያት አርባዕ ትባል ነበር፤ እነርሱም የሼሻይን፥ የአሒማንንና የታልማይን ጐሣዎች አሸነፉ።
ዖትኒኤል የደቢርን ከተማ ማሸነፉ
(ኢያሱ 15፥13-19)
11ከዚያም የይሁዳ ሰዎች በደቢር ኗሪዎች ላይ ዘመቱ፤ በዚያን ጊዜ ከተማይቱ “ቂርያት ሴፌር” ተብላ ትጠራ ነበር። 12ካሌብም “ቀድሞ ቂርያት ሴፌርን ለሚይዝ ሰው ሴት ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” አለ። 13የካሌብ ታናሽ ወንድም የቀናዝ ልጅ ዖትኒኤል ከተማይቱን ቀድሞ ያዘ፤ ስለዚህም ካሌብ ሴት ልጁን ዓክሳን ዳረለት። 14በጋብቻቸውም ቀን ዖትኒኤል ዓክሳን “አባትሽ የእርሻ መሬት እንዲሰጥሽ ጠይቂ” አላት፤ እርስዋም ካሌብን ስታይ ከበቅሎዋ ላይ ወረደች፤ ካሌብም “ምን እንድሰጥሽ ትፈልጊአለሽ” ብሎ ጠየቃት። #1፥14 ጠይቂ አላት፦ በዕብራይስጥ “ጠይቅ” አለችው ይላል። (ኢያ. 15፥18) ተመልከት። 15እርስዋም “የሰጠኸኝ መሬት በረሓማ ላይ ስለ ሆነ ጥቂት የውሃ ምንጮች እንድትሰጠኝ እለምንሃለሁ፤” አለችው፤ ስለዚህ ካሌብ የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።
የይሁዳና የብንያም ነገዶች የተቀዳጁት ድል
16የሙሴ ዐማት የነበረው የቄናዊው ዘሮች ከይሁዳ ሕዝብ ጋር በመሆን የተምር ዛፎች ከሞሉባት ከኢያሪኮ ከተማ ተነሥተው፥ በይሁዳ ካለችው ከዐራድ በስተደቡብ ወዳለው ደረቅ ምድር ተጓዙ፤ እዚያም በዐማሌቃውያን መካከል ተቀመጡ። 17የይሁዳ ሕዝብ ከስምዖን ሕዝብ ጋር በአንድነት ዘምተው በጸፋት ከተማ ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያንን ድል አደረጉ፤ ከተማይቱንም ፈጽመው ካጠፉአት በኋላ “ሖርማ” ብለው ሰየሙአት፤ 18የይሁዳም ነገድ ጋዛንና አስቀሎናን፥ አቃሮንንና አካባቢዎቻቸውን ያዙ። 19እግዚአብሔር ከይሁዳ ሕዝብ ጋር ስለ ነበረ የተራራማውን አገር አሸንፈው ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳማው ሜዳ አገር የነበሩት ኗሪዎች የብረት ሠረገሎች ስለ ነበሩአቸው ሊያስወጡአቸው አልቻሉም። 20ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠ፤ ርሱም ሦስቱን የዐናቅ ጐሣዎች ከዚያ አስወጣ። 21የብንያም ነገድ ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን አላስወጡም ነበር፤ ከዚያን ጊዜም ጀምሮ ኢያቡሳውያን ከብንያም ሕዝብ ጋር እስከ ዛሬ ድረስ አብረው መኖርን ቀጠሉ። #ኢያሱ 15፥63፤ 2ሳሙ. 5፥6፤ 1ዜ.መ. 11፥4።
የኤፍሬምና የምናሴ ነገዶች ቤትኤልን መያዛቸው
22የዮሴፍ ዘሮች ደግሞ በቤቴል ላይ ዘመቱ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበር፤ 23የዮሴፍ ልጆች ቤቴልን የሚሰልሉ ሰዎች ላኩ፤ የከተማይቱ ስም አስቀድሞ ሎዛ ይባል ነበር። 24ሰላዮቹም ከከተማይቱ የሚወጣ አንድ ሰው አግኝተው “ወደ ከተማይቱ እንዴት መግባት እንደሚቻል ብትነግረን መልካም እናደርግልሃለን” አሉት። 25እርሱም የከተማይቱን መግቢያ አሳያቸው፤ እነርሱም የከተማይቱን ሕዝብ በሰይፍ ፈጁአቸው፤ ያን ሰውና ወገኖቹን ሁሉ ግን በነጻ ለቀቁአቸው። 26ያም ሰው ዘግይቶ ወደ ሒታውያን ምድር ሄዶ ከተማ ሠራና “ሎዛ” ብሎ ሰየማት፤ እስከ ዛሬም የምትጠራበት ስም ይኸው ነው።
እስራኤላውያን ያላባረሩት ሕዝብ
27የምናሴ ነገድ ቤትሻን፥ በታዕናክ በዶርን የዪብልዓምንና በመጊዶና በአካባቢያቸው የሚኖሩትን ሰዎች አላስወጡም ነበር፤ ከነዓናውያንም በዚያው መኖርን ቀጠሉ፤ 28እስራኤላውያን ብርታት ባገኙ ጊዜ ከነዓናውያን ለእነርሱ የጒልበት ሥራ እንዲሠሩላቸው ያስገድዱአቸው ነበር፤ ሆኖም ሁሉንም አላስወጡም ነበር። #ኢያሱ 17፥11-13።
29የኤፍሬም ነገድም በጌዜር ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያንን አላባረሩም ነበር፤ ስለዚህ ከነዓናውያን እዚያው ከእነርሱ ጋር ኗሪዎች ሆኑ። #ኢያሱ 16፥10።
30የዛብሎን ነገድ በቂትሮንና በናህላል ይኖሩ የነበሩትን ኗሪዎች አላስወጡም ነበር፤ ስለዚህ ከነዓናውያን እዚያው ከእነርሱ ጋር ኗሪዎች ሆኑ፤ ሆኖም ለዛብሎናውያን የጒልበት ሥራ ለመሥራት ይገደዱ ነበር።
31የአሴር ነገድ በዓኮ፥ በሲዶና፥ በአሕላብ፥ በአክዚብ፥ በሔልባ፥ በአፌቅና በረሖብ ይኖሩ የነበሩትን ኗሪዎች አላባረሩም ነበር። 32ከነዓናውያንንም ሳያስወጡ በመቅረታቸው የአሴር ሕዝብ በዚያው ከእነርሱ ጋር አብረው ይኖሩ ነበር።
33የንፍታሌም ነገድ በቤትሼሜሽና በቤትዓናት ይኖሩ የነበሩትን ሰዎች አላስወጡም፤ ስለዚህም የንፍታሌም ሕዝብ ከከነዓናውያን ጋር እዚያው አብረው መኖርን ቀጠሉ፤ ሆኖም የጒልበት ሥራ እንዲሠሩላቸው ከነዓናውያንን ያስገድዱአቸው ነበር።
34አሞራውያን የዳንን ነገድ ሕዝብ ወደ ኮረብታማው አገር አባረሩአቸው፤ ወደ ሜዳማውም ምድር እንዲወርዱ አልፈቀዱላቸውም፤ 35አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በአያሎን፥ በሻዓልቢም መኖርን ቀጠሉ፤ ነገር ግን የዮሴፍ ልጆች (የኤፍሬምና የምናሴ ነገዶች) የእነርሱ ተገዢዎች አድርገው የጒልበት ሥራ እንዲሠሩላቸው ያስገድዱአቸው ነበር። 36የአሞራውያን ድንበር ከዐቅራቢም አቀበት ከሴላዕ ጀምሮ ወደ ላይ ይወጣ ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997