መጽሐፈ መሳፍንት 11
11
1ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ከአንዲት ጋለሞታ ሴት የተወለደ ጀግና ወታደር ነበር፤ አባቱም ገለዓድ ይባል ነበር። 2የእርሱ አባት ገለዓድ ቀደም ብሎ ያገባት ሚስቱ የወለደችለት ሌሎች ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ወንድማቸውን ዮፍታሔን “አንተ ከሌላ ሴት የተወለድክ ስለ ሆንክ ከአባታችን ርስት ምንም ነገር መውረስ አይገባህም” ብለው ከቤት እንዲባረር አደረጉት። 3ዮፍታሔም ከወንድሞቹ ሸሽቶ ጦብ ተብላ በምትጠራ ምድር ኖረ፤ እዚያ ጥቂት ወሮበሎች ተሰብስበው ተከተሉት።
4ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዐሞናውያን በእስራኤላውያን ላይ ዘመቱ። 5ይህም በሆነ ጊዜ የገለዓድ መሪዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር መልሰው ለማምጣት ሄዱ። 6ዮፍታሔንም፦ “ዐሞናውያንን መውጋት እንችል ዘንድ መጥተህ መሪያችን ሁን” አሉት።
7ዮፍታሔ ግን “እኔን ጠልታችሁ ከአባቴ ቤት ያባረራችሁኝ እናንተ አይደላችሁምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ወደ እኔ መምጣታችሁ ስለምንድነው?” አላቸው።
8እነርሱም ዮፍታሔን “አሁን እኛ ወደ አንተ ተመልሰናል፤ ከእኛ ጋር ዘምተህ ዐሞናውያንን እንድትወጋልንና የገለዓድ ሕዝብ ሁሉ መሪ እንድትሆን እንፈልጋለን” አሉት።
9ዮፍታሔም የገልዓድን ሽማግሌዎች፦ “እንግዲህ ወደ ቤት ከመለሳችሁኝ በኋላ እግዚአብሔር በዐሞናውያን ላይ ድልን በሚያጐናጽፈኝ ጊዜ እኔ የእናንተ መሪ እሆናለሁ” አላቸው።
10እነርሱም “እግዚአብሔር ምስክራችን ነው፤ አንተ እንዳልከው እናደርጋለን” ብለው መለሱለት፤ 11ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ መሪዎች ጋር ሄደ። ሕዝቡም ገዢአቸውና መሪያቸው አደረጉት፤ ዮፍታሔም በምጽጳ በእግዚአብሔር ፊት በዚህ ጉዳይ መስማማቱን ገለጠ።
12ከዚህ በኋላ ዮፍታሔ ወደ ዐሞን ንጉሥ መልእክተኞችን ልኮ “ከእኛ ጋር የተጣላህበት ምክንያት ምንድን ነው? አገራችንንስ የወረርከው ለምንድነው?” ብለው እንዲጠይቁት አደረገ።
13የዐሞንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች መልስ ሲሰጥ “እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ ከአርኖን ወንዝ እስከ ያቦቅ ወንዝ ያለውን ምድሬንና የዮርዳኖስንም ወንዝ ወሰዱብኝ፤ አሁን ግን በሰላም መመለስ ይኖርባችኋል” አላቸው።
14ዮፍታሔ እንደገና መልእክተኞችን ወደ ዐሞን ንጉሥ ላከ፤ 15እንዲህ በማለትም መልስ ሰጠው፤ “እስራኤላውያን የሞአብንም ሆነ የዐሞንን ምድር አልወሰዱም፤ 16እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ ጊዜ በበረሓው አቋርጠው ወደ ቀይ ባሕር ደረሱ፤ ከዚያም ወደ ቃዴስ አለፉ፤ 17ከዚያ በኋላ በምድሩ አልፈው እንዲሄዱ ይፈቅድላቸው ዘንድ ወደ ኤዶም ንጉሥ መልእክተኞች ላኩ፤ ነገር ግን የኤዶም ንጉሥ አልፈቀደላቸውም፤ የሞአብንም ንጉሥ እንዲሁ ጠየቁ፤ እርሱም ቢሆን በምድሩ አልፈው እንዲሄዱ አልፈቀደላቸውም፤ ስለዚህ እስራኤላውያን በቃዴስ ቈዩ፤ #ዘኍ. 20፥14-21። 18በረሓውንም በማቋረጥ ጒዞ ቀጥለው የኤዶምንና የሞአብን ምድር በመዞር ከሞአብ በስተምሥራቅና ከአርኖን ወንዝ ባሻገር ወዳለው ስፍራ መጥተው ሰፈሩ፤ ነገር ግን የሞአብ ወሰን ስለ ነበር የአርኖንን ወንዝ አልተሻገሩም፤ #ዘኍ. 21፥4። 19ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን በሐሴቦን ሆኖ ወደሚገዛው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሲሖን መልእክተኞች ልከው በአገሩ በኩል አልፈው ወደ አገራቸው እንዲሄዱ አስጠየቁት፤ 20ሲሖን ግን እስራኤላውያን አልፈው እንዲሄዱ አልፈቀደላቸውም፤ እንዲያውም መላ ሠራዊቱን ሰብስቦ በያሐጽ በመስፈር ከእስራኤል ጋር ተዋጋ። 21ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እስራኤላውያን በሠራዊቱ ላይ ድልን እንዲቀዳጁ አደረገ። በዚህም ዐይነት እስራኤላውያን በዚያ አገር ይኖሩ የነበሩትን የአሞራውያንን ግዛት በሙሉ ወስደው የራሳቸው ርስት አደረጉት፤ 22በደቡብ ከአርኖን ወንዝ አንሥቶ በሰሜን እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ፥ እንዲሁም በምሥራቅ ከበረሓው አንሥቶ በምዕራብ እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ መላውን የአሞራውያን ግዛት ያዙ፤ #ዘኍ. 21፥21-24። 23ስለዚህ ለሕዝቡ ለእስራኤላውያን ሲል አሞራውያንን አባሮ ያስወጣ ራሱ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ፥ አንተ መልሰህ ልትወስድ ታስባለህን? 24አንተ አምላክህ ከሞሽ የሰጠህን ይዘህ ዐርፈህ አትቀመጥምን? እኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር የሰጠንን ሁሉ ወርሰን እንኖራለን። 25ለመሆኑ አንተ የሞአብ ንጉሥ ከነበረው ከጺጶር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? እርሱ እንኳ እስራኤልን ከቶ አልተቋቋመም፤ እኛንም ይወጋ ዘንድ ወደ ጦርነት ለመውጣት አልደፈረም። #ዘኍ. 22፥1-6። 26ስለዚህ ሦስት መቶ ዓመት ሙሉ እስራኤል ሐሴቦንና መንደሮችዋን ዓሮዔርንና መንደሮችዋን፥ እንዲሁም በአርኖን ወንዝ ዳርቻ ያሉትን ከተሞች በሙሉ ወርሰው ኖረዋል፤ ታዲያ በነዚህ ዘመናት ሁሉ ስለምን መልሳችሁ አልወሰዳችኋቸውም ነበር? 27እኔ በበኩሌ ምንም አልበደልኩም፤ በእኔ ላይ ጦርነት በመክፈት ልትበድለኝ የተነሣሣህ አንተ ነህ፤ እንግዲህ ፈራጅ እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ ዛሬ በእስራኤላውያንና በዐሞናውያን መካከል ውሳኔ ይሰጣል።” 28የዐሞን ንጉሥ ግን የዮፍታሔን መልእክት ከቁም ነገር አልቈጠረውም።
29በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ዮፍታሔም በገለዓድና በምናሴ ግዛቶች መካከል አቋርጦ ሄደ፤ በገለዓድ ወደምትገኘው ወደ ምጽጳ አለፈ፤ ከዚያም ወደ ዐሞን ጒዞውን ቀጠለ። 30ለእግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተሳለ፤ “በዐሞናውያን ላይ ድልን ብታቀዳጀኝ 31ድል አድርጌ ከዘመቻ ወደ ቤቴ በደኅና ስመለስ ከቤት ወጥቶ ሊቀበለኝ የሚመጣው ለአንተ ይሆናል፤ እርሱንም ለአንተ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።”
32ከዚህም በኋላ ዮፍታሔ ዐሞናውያንን ለመውጋት ወንዙን ተሻግሮ ሄደ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ድልን አጐናጸፈው። 33ከዓሮዔር ጀምሮ በሚኒት ዙሪያ እስካለው ስፍራ በአጠቃላይ ኻያ ከተሞችን፥ እንዲሁም እስከ አቤል ከራሚም ድረስ ያሉትን ሁሉ ደመሰሳቸው፤ በዚህም ዐይነት ዐሞናውያን በእስራኤላውያን ፊት ተዋረዱ።
የዮፍታሔ ሴት ልጅ
34ዮፍታሔ በምጽጳ ወዳለው ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ሴት ልጁ አታሞ ይዛ እየጨፈረች ልትቀበለው ወጣች፤ ያለ እርስዋም ሌላ ወንድ ወይም ሴት ልጅ አልነበረውም። 35ባያትም ጊዜ በሐዘን ልብሱን በመቅደድ “ወዮ ልጄ! ልቤን በሐዘን ሰበርሽው! ለታላቅ ጭንቀትም ዳረግሽኝ፤ ለእግዚአብሔር ቃል ገብቼአለሁና ስለቴን ልመልሰውም አልችልም፤” አለ። #ዘኍ. 30፥2።
36እርስዋም “አባቴ ሆይ! ለእግዚአብሔር ቃል ገብተህ ከሆነስ፥ እግዚአብሔር ጠላቶችህን ዐሞናውያንን ስለ ተበቀለልህ በእኔ ላይ ልታደርግ ለእግዚአብሔር ቃል የገባኸውን ፈጽም!” አለችው። 37ነገር ግን አባትዋን እንዲህ ስትል ጠየቀችው፤ “ይህን አንድ ነገር ፍቀድልኝ፤ እንግዲህ አግብቼ ልጅ መውለድ ስለማልችል ከጓደኞቼ ጋር በተራራው ላይ ተዘዋውሬ ለድንግልናዬ እንዳለቅስ የሁለት ወር ጊዜ ፍቀድልኝ።” 38እርሱም እንድትሄድ ፈቅዶ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርስዋና ጓደኞችዋም ወደ ተራራዎች ወጡ፤ ከዚያም ባል አግብታ ልጆች የማትወልድ በመሆንዋ አለቀሱላት። 39ከሁለት ወር በኋላ ወደ አባትዋ ቤት ተመልሳ መጣች፤ እርሱም ለእግዚአብሔር ቃል የገባውን ስለት ፈጸመባት፤ እርስዋም ወንድ ያላወቀች ድንግል ነበረች።
ከዚያም ጊዜ አንሥቶ፥ 40የእስራኤላውያን ወጣት ሴቶች ልጆች በየዓመቱ ለአራት ቀን ያኽል ከቤታቸው ርቀው እየሄዱ ለገለዓዳዊው ለዮፍታሔ ሴት ልጅ ማዘናቸውና ማልቀሳቸው የተለመደ ሆነ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997