መጽሐፈ መሳፍንት 13
13
የሶምሶን መወለድ
1የእስራኤል ሕዝብ እንደገና እግዚአብሔርን በደሉ፤ ስለዚህም አርባ ዓመት ሙሉ እንዲገዙአቸው እግዚአብሔር ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ሰጣቸው።
2በዚያን ዘመን ጾርዓ በምትባል ከተማ የሚኖር ማኑሄ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ትውልዱ ከዳን ነገድ ነበር፤ ሚስቱ መኻን ስለ ነበረች ልጆች አልወለደችም፤ 3ለእርስዋም የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ እንዲህ አላት፤ “አንቺ መኻን ነሽ፤ ልጆችም የሉሽም፤ ነገር ግን ትፀንሺአለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ 4የወይን ጠጅም ሆነ ማንኛውንም የሚያሰክር መጠጥ ከመጠጣትና ማንኛውንም ርኩስ ምግብ ከመብላት ተጠንቀቂ። 5በእርግጥ ትፀንሺአለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከተወለደበት ቀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ስለሚሆን የራስ ጠጒሩን ፈጽሞ አይላጭ፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።” #13፥5 ናዝራዊ፦ የተቀደሰ ወይም የተለየ ማለት ነው። #ዘኍ. 6፥1-5።
6ከዚህ በኋላ ሴቲቱ መጥታ ለባልዋ እንዲህ አለችው፤ “አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጥቶ ነበር፤ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤ እኔ ከወዴት እንደ መጣ አልጠየቅሁትም፤ እርሱም ስሙን አልነገረኝም፤ 7ነገር ግን እርሱ ‘እነሆ ትፀንሺአለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ’ ብሎ ነገረኝ፤ እንዲሁም የሚወለደው ልጅ ከተወለደበት ቀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በናዝራዊነት ለእግዚአብሔር የተለየ ስለሚሆን፥ የወይን ጠጅም ሆነ ማንኛውንም የሚያሰክር መጠጥ ከመጠጣትና ማንኛውንም ርኩስ ምግብ ከመብላት እንድጠነቀቅ ነግሮኛል።”
8ከዚህ በኋላ ማኑሄ “እግዚአብሔር ሆይ! ሕፃኑ ሲወለድ ምን ማድረግ እንደሚገባን ይነግረን ዘንድ ያ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደገና ተመልሶ ወደ እኛ እንዲመጣ አድርግልን” ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
9እግዚአብሔርም የማኑሄን ጸሎት ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደገና ወጥቶ ሴቲቱ በእርሻ ውስጥ እንደ ተቀመጠች ተገለጠላት፤ ባልዋ ማኑሄ ከእርስዋ ጋር አልነበረም፤ 10ስለዚህ በፍጥነት ወደ እርሱ ሮጣ በመሄድ “እነሆ! ያ ከዚህ በፊት ወደ እኔ መጥቶ የነበረው ሰው ዛሬም እንደገና ተገለጠልኝ” አለችው።
11ማኑሄም ከተቀመጠበት ተነሥቶ ሚስቱን ተከትሎ ሄደ፤ ወደ ሰውየውም ቀርቦ “ከሚስቴ ጋር ተነጋግረህ የነበርከው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።
ሰውየውም “አዎ! እኔ ነኝ” ሲል መለሰ።
12ቀጥሎም ማኑሄ “የተናገርከው ቃል ሲፈጸም ለሚወለደው ልጅ ምን መደረግ አለበት?” ሲል ጠየቀው።
13መልአኩም እንዲህ ሲል መለሰ፥ “ሚስትህ የነገርኳትን ሁሉ ነገር ለማድረግ ትኲረት መስጠት አለባት። 14ከወይን ተክል የሚገኝ ምንም ነገር መመገብ አይኖርባትም፤ የወይን ጠጅም ሆነ ማንኛውንም የሚያሰክር መጠጥ አትጠጣ፤ ማንኛውንም ርኩስ ምግብ አትበላም፤ በአጠቃላይ እኔ ያዘዝኳትን ሁሉ መፈጸም አለባት።”
15ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ “አንድ የፍየል ጠቦት ዐርደን እስክናዘጋጅልህ ድረስ እባክህ ቈይልን!” አለው። 16የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን “ምንም አንተ ብታቈየኝ ምግብህን አልበላም፤ የሚቃጠል መሥዋዕት ማዘጋጀት ብትፈልግ ግን ለእግዚአብሔር አቅርበው” አለው። ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር።
17ማኑሄም “የተናገርከው ቃል ሲፈጸም ምስጋና እናቀርብልህ ዘንድ ስምህ ማን ነው?” አለው።
18መልአኩም “ስሜን ለማወቅ የፈለግኸው ለምንድን ነው? ስሜ ድንቅ ነው” ሲል መለሰለት። #ዘፍ. 32፥29።
19ከዚህ በኋላ ማኑሄ አንድ የፍየል ጠቦትና የእህል ቊርባን ወስዶ በአለቱ መሠዊያ ላይ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ ማኑሄና ሚስቱም እየተመለከቱ ሳለ እግዚአብሔር አስደናቂ ነገር አደረገ። 20ነበልባሉ ከመሠዊያው ወደ ሰማይ ሲወጣ ማኑሄና ሚስቱ እየተመለከቱ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ በነበልባሉ ውስጥ ሆኖ ወደ ላይ ወጣ፤ እነርሱም በግንባራቸው በመሬት ላይ ተደፉ። 21የእግዚአብሔር መልአክ ለማኑሄና ለሚስቱ ዳግመኛ አልተገለጠም ከዚያ በኋላ ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ዐወቀ።
22ማኑሄ ሚስቱን “እግዚአብሔርን ስላየን በእርግጥ እንሞታለን!” አላት።
23ሚስቱ ግን “እግዚአብሔር ሊገድለን ቢፈልግ ኖሮ የሚቃጠል መሥዋዕታችንንና የእህል ቊርባናችንን ባልተቀበለም ነበር፤ ይህን ሁሉ አሁን ባላሳየንና እንዲህ ያለውን ነገር ሁሉ ባልነገረንም ነበር” ስትል መለሰችለት።
24ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፤ ልጁም አደገ፤ እግዚአብሔርም ባረከው፤ 25በጾርዓና በኤሽታኦል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ በነበረበት ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ ያበረታው ጀመር።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 13: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997