የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 14

14
የሶምሶን ጋብቻ
1አንድ ቀን ሶምሶን ወደ ቲምና ወረደ፤ በዚያም አንዲት ፍልስጥኤማዊት ሴት አየ፤ 2ወደ ቤቱም ተመልሶ ለአባቱና ለእናቱ “በቲምና ከፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች አንድዋን አይቼ ወድጃታለሁ፤ ስለዚህ እርስዋን አጭታችሁ አጋቡኝ” አላቸው።
3አባቱና እናቱ ግን “ሚስት ለማግኘት ወደ አልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን ዘንድ ሄደህ ሚስት የምትፈልገው ከወገንህ ወይም በሕዝባችን መካከል ሴት ልጅ የሌለች ሆኖ ነውን?” ሲሉ ጠየቁት።
ሶምሶን ግን አባቱን “እኔ እርስዋን በጣም ስለ ወደድኳት ከእርስዋ ጋር አጋባኝ” አለው።
4ሶምሶን ይህን እንዲያደርግ የሚመራው እግዚአብሔር እንደ ሆነ ወላጆቹ አላወቁም፤ በዚያም ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤላውያንን ይገዙ ስለ ነበር፥ እግዚአብሔር ፍልስጥኤማውያንን ለመቃወም ምክንያት ይፈልግ ነበር።
5ከዚህ በኋላ ሶምሶን ከአባቱና ከእናቱ ጋር ወደ ቲምና ወረደ፤ እዚያም በወይን ተክል ውስጥ አልፈው ሲሄዱ አንድ ደቦል አንበሳ እያገሣ መጣበት፤ 6በድንገትም የእግዚአብሔር መንፈስ ሶምሶንን አበረታው፤ ስለዚህም አንበሳውን እንደ አንድ የፍየል ጠቦት ያኽል በመቊጠር ያለ ምንም መሣሪያ በባዶ እጁ ገነጣጥሎ ጣለው፤ ያደረገውንም ነገር ለወላጆቹ አልነገራቸውም።
7ከዚህ በኋላ ወደ ሴቲቱ ሄዶ አነጋገራት፤ ወደዳትም፤ 8ከጥቂት ቀኖች በኋላ እርስዋን ለማግባት ወደዚያ ተመልሶ ሄደ፤ በጒዞም ላይ ሳሉ ያንን የገደለውን አንበሳ ሁኔታ ለማየት ከመንገድ ዞር አለ፤ በድኑን ንቦች ሰፍረውበት በውስጡም ማር. መኖሩን በተመለከተ ጊዜ እጅግ ተደነቀ፤ 9ከማሩም ጥቂት በእጁ ቈርጦ እየበላ መንገዱን ቀጠለ፤ ወደ አባቱና ወደ እናቱ ቀርቦ ከያዘው ማር. ሰጥቶአቸው በሉ፤ ነገር ግን ሶምሶን ያንን ማር. ያገኘው ከሞተው አንበሳ በድን ውስጥ መሆኑን አልነገራቸውም።
10አባቱ ወደ ሴቲቱ ቤት በሄደ ጊዜ፥ ሶምሶን በዚያ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ይህም ዐይነቱ ግብዣ በወጣቶች ዘንድ የተለመደ ነበር፤ 11ፍልስጥኤማውያን እርሱን ባዩት ጊዜ ከእርሱ ጋር እንዲቈዩ ሠላሳ ወንዶች ወጣቶችን መርጠው ላኩለት። 12ሶምሶንም እንዲህ አላቸው፤ “እስቲ ታውቁ እንደ ሆነ አንድ እንቆቅልሽ ልንገራችሁ፤ በሰባቱ የሠርጉ በዓል ቀኖች ውስጥ ይህን እንቆቅልሽ ፈትታችሁ ብትነግሩኝ፥ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ቅያሬ ልብስ እሰጣችኋለሁ፤ 13ፍቹን መንገር ባትችሉ ግን ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ቅያሬ ልብስ ትሰጡኛላችሁ።”
እነርሱም “እንቆቅልሽህን ንገረን፤ እስቲ እንስማው” አሉት።
14እርሱም
“ከበላተኛው መብል ተገኘ፤
ከብርቱውም ጣፋጭ ነገር ወጣ” አላቸው።
እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንቆቅልሹን መፍታት አልቻሉም።
15በአራተኛው ቀን የሶምሶንን ሚስት እንዲህ አሉአት፤ “ባልሽን አግባብተሽ የእንቆቅልሹን ፍች እንዲነግረን አድርጊ፤ ይህን ካላደረግሽ ግን የአባትሽን ቤት በእሳት አያይዘን አንቺንም በውስጡ በመጨመር እናቃጥልሻለን፤ ለካስ እናንተ ሁለታችሁም ወደ ግብዣችሁ የጠራችሁን ልትዘርፉን ኖሮአልን?”
16ስለዚህ የሶምሶን ሚስት እያለቀሰች ወደ እርሱ ቀርባ “ለካስ አንተ እኔን አትወደኝም! እንዲያውም በጣም ትጠላኛለህ! የአገሬን ልጆች እንቆቅልሽ ጠይቀህ ለእኔ እስከ አሁን ፍቺውን አልነገርከኝም!” አለችው።
እርሱም “እነሆ! እኔ ይህን ለአባቴና ለእናቴ እንኳ አልነገርኳቸውም፤ ታዲያ ለአንቺ የምነግርበት ምክንያት ምንድን ነው?” አላት። 17ከዚህም የተነሣ እርስዋ በሠርጉ በዓል ሰባት ቀን ሙሉ አለቀሰች፤ አጥብቃም ስለ ነዘነዘችው የእንቆቅልሹን ፍች በሰባተኛው ቀን ነገራት፤ እርስዋም ሄዳ ለፍልስጥኤማውያኑ ነገረቻቸው። 18ስለዚህ በሰባተኛው ቀን ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት፥ የከተማይቱ ሰዎች
“ከማር የጣፈጠ፥
ከአንበሳስ የበረታ ምን አለ?”
ሲሉ የእንቆቅልሹን ፍች ነገሩት።
ሶምሶንም
“በእኔ ጊደር ባታርሱ ኖሮ፥
መልሱን ማግኘት ባልቻላችሁም ነበር” አላቸው።
19የእግዚአብሔርም መንፈስ ለእርሱ ብርታትን ሰጠው፤ ወደ አስቀሎናም ወርዶ ሠላሳ ሰዎችን ገደለ፤ ውብ የሆነውንም ልብሳቸውን ሁሉ በመግፈፍ አምጥቶ የእንቆቅልሹን ፍች ላወቁት ሰዎች ሰጣቸው። በሆነውም ነገር ሁሉ እጅግ ተቈጥቶ ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሰ፤ 20ሚስቱም በሠርጉ ሚዜ ለነበረው ጓደኛው ተዳረች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ