የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 4

4
ዲቦራና ባራቅ
1ኤሁድ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንደገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፤ 2ስለዚህም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በሐጾር ከተማ ይኖር ለነበረው ለከነዓናዊው ንጉሥ ለያቢን አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ የአሕዛብ ይዞታ በሆነችው በሐሮሼት ከተማ ይኖር የነበረው ሲሣራ ነበር። 3ያቢን ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎች ነበሩት፤ የእስራኤል ሕዝብ በጭካኔና በዐመፅ ለኻያ ዓመት ገዛቸው፤ ከዚያም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንዲረዳቸው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
4በዚያን ጊዜ የላፒዶት ሚስት የሆነች “ዲቦራ” የምትባል ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም በዚያን ጊዜ የእስራኤል መሪ ነበረች። 5ይህችም ነቢይት በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤትኤል መካከል በሚገኘው የዲቦራ የተምር ዛፍ ሥር ተቀምጣ ትፈርድ ስለ ነበር የእስራኤል ሕዝብ ፍርድ ለማግኘት ወደ እርስዋ ይሄዱ ነበር። 6የአቢኒዓምን ልጅ ባራቅን የንፍታሌም ድርሻ ከሆነችው ከቃዴስ ከተማ አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይህን ትእዛዝ ሰጥቶሃል፦ ‘ከንፍታሌምና ከዛብሎን ነገዶች ዐሥር ሺህ ሰዎች መርጠህ ወደ ታቦር ተራራ ውሰዳቸው፤ 7የያቢን ሠራዊት አዛዥ የሆነው ሲሣራ በቂሾን ወንዝ አንተን ለመውጋት እንዲመጣ አደርጋለሁ፤ እርሱም ሠረገሎቹንና ወታደሮቹን አሰልፎ ይመጣል፤ እኔም በእርሱ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አደርግሃለሁ።’ ”
8ከዚህ በኋላ ባራቅ “አንቺ ከእኔ ጋር ከሄድሽ እሄዳለሁ፤ አብረሽኝ ካልሄድሽ ግን እኔም አልሄድም” አላት።
9እርስዋም “እሺ፥ እኔም ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲሣራን ለሴት አሳልፎ ስለሚሰጥ ድሉ ለአንተ ክብር አይሆንም” አለችው፤ ስለዚህ ዲቦራ ከባራቅ ጋር ወደ ቃዴስ ዘመተች። 10ባራቅም የንፍታሌምንና የዛብሎንን ነገዶች ወደ ቃዴስ አስጠራ፤ ከእነርሱም ዐሥር ሺህ ሰዎች ተከተሉት፤ ዲቦራም አብራው ዘመተች።
11ቀኔናዊው ሔቤር የሙሴ ዐማት ከነበረው ከሆባብ ልጆች ከቄናውያን ተለየ፤ ወደ ቃዴስ ቀረብ ብሎ በጸእናይም በሚገኘው በታላቁ ዛፍ አጠገብ ድንኳኑን ተከለ።
12የአቢኒዓም ልጅ ባራቅ ወደ ታቦር ተራራ መሄዱ ለሲሣራ ተነገረው። 13ሲሣራም ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎችንና ከእርሱ ጋር የነበረውን ሠራዊት ሁሉ የአሕዛብ ይዞታ ከነበረችው ከሐሮሼት ወደ ቂሶን ወንዝ ሰበሰበ።
14ዲቦራም ባራቅን “እግዚአብሔር አንተን በሲሣራ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ የሚያደርግበት ቀን ዛሬ ስለ ሆነ ተነሥ! እነሆ! እግዚአብሔር ይመራሃል” አለችው፤ ባራቅም ዐሥር ሺህ ወታደሮች ተከትለውት ከታቦር ተራራ ወረደ። 15ባራቅ ከሠራዊቱ ጋር አደጋ በጣለ ጊዜ እግዚአብሔር ሲሣራን ከሠረገሎቹና ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በአደናጋሪ ሁከት ላይ እንዲወድቅ አደረገው፤ ሲሣራም ከሠረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ። 16ባራቅም ሠረገሎቹንና ሠራዊቱን የአሕዛብ ይዞታ እስከ ሆነችው እስከ ሐሮሼት ድረስ አሳደዳቸው፤ የሲሣራም ሠራዊት በሙሉ በሰይፍ ተገደሉ፤ አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም።
17የሐጾር ንጉሥ ያቢን ከሔቤር ቤተሰብ ጋር ሰላም መሥርቶ ይኖር ስለ ነበር ሲሣራ ሸሽቶ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ያዔል ድንኳን ገባ። 18ያዔልም ሲሣራን ልትቀበለው ወጥታ “ጌታዬ ና፥ ወደ ድንኳኔ ግባ፤ ከቶ አትፍራ” አለችው፤ እርሱም ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ በልብስ ሸፈነችው፤ 19ሲሣራም “እባክሽ የምጠጣው ውሃ ስጪኝ፤ በጣም ጠምቶኛል” አላት፤ እርስዋም ከቈዳ የተሠራውን የወተት ዕቃ ከፍታ አጠጣችውና እንደገና ሸፍና ደበቀችው። 20ከዚህ በኋላ እርሱ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ አንድ ሰው መጥቶ ከዚህ ሌላ ሰው እንዳለ ቢጠይቅሽ ማንም የለም በይው” አላት።
21ሲሣራ በጣም ደክሞት ስለ ነበር ከባድ እንቅልፍ ወሰደው፤ ከዚህ በኋላ የሔቤር ሚስት ያዔል መዶሻና የድንኳን ካስማ ወስዳ በቀስታ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ካስማውንም በጆሮ ግንዱ ጠልቆ መሬት እስኪነካ ድረስ ቸነከረችው፤ እርሱም ሞተ። 22ባራቅ ሲሣራን እያሳደደ ሲመጣ ያዔል ልትቀበለው ወጥታ “ወደዚህ ና! አንተ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው። ስለዚህም ከእርስዋ ጋር ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ የድንኳኑ ካስማ በሲሣራ ጆሮ ግንድ ላይ እንደ ተቸነከረ ሬሳውን በመሬት ላይ ተጋድሞ አየ።
23እግዚአብሔርም በዚያን ቀን እስራኤላውያን በከነዓናዊው ንጉሥ በያቢን ላይ ድልን እንዲቀዳጁ አደረገ። 24እነርሱም እርሱን ፈጽመው እስከሚያጠፉ ድረስ የእስራኤል ሕዝብ በያቢን ላይ እየበረቱ ሄዱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ