ትንቢተ ኤርምያስ 28
28
ኤርምያስና ነቢዩ ሐናንያ
1በዚሁ ዘመን፥ ማለትም ሴዴቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር የገባዖን ሰው የሆነው የዐዙር ልጅ ሐናንያ በቤተ መቅደስ ተናገረኝ፤ በካህናቱና በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ አለኝ፦ #2ነገ. 24፥18-20፤ 2ዜ.መ. 36፥11-13። 2“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎአል፥ ‘የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁ፤ 3ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚህ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን የቤተ መቅደስ ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደዚህ ስፍራ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ 4እንዲሁም የኢዮአቄምን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ወደ ባቢሎን ተሰደው ከሄዱት ከይሁዳ ሕዝብ ጋር መልሼ አመጣዋለሁ፤ አዎ! የባቢሎንን ንጉሥ የአገዛዝ ቀንበር እሰብራለሁ፤’ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
5እኔም በካህናቱና በቤተ መቅደስ በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ሐናንያን እንዲህ አልኩት፦ 6“አሜን! እግዚአብሔር እንዳልከው ያድርግ! የቤተ መቅደሱን ዕቃዎች በማምጣትና የተማረኩትን ምርኮኞች በመመለስ እግዚአብሔር አንተ የተናገርከውን ትንቢት ይፈጽም። 7ሆኖም ለአንተና ለሕዝቡ የምናገረውን ስማ፤ 8በጥንት ዘመን ከእኔና ከአንተ በፊት የተነሡ ነቢያት በብዙ ሕዝብና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ጦርነት፥ ራብና ቸነፈር እንደሚመጣ ትንቢት ተናግረዋል፤ 9ነገር ግን ስለ ሰላም የተናገረ ነቢይ ቢኖር ከእግዚአብሔር የተላከ ነቢይ መሆኑ የሚታወቀው ያ የተናገረው ትንቢት እውነት ሆኖ ሲገኝ ነው።”
10ከዚህ በኋላ ነቢዩ ሐናንያ በእኔ ጫንቃ ላይ የነበረውን ቀንበር ወስዶ ሰባበረው፤ 11በሕዝቡም ሁሉ ፊት ሲናገር፦ “በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን የአገዛዝ ቀንበር ከሕዝቡ ጫንቃ ላይ አውርዶ እንደዚህ የሚሰባብረው መሆኑን እግዚአብሔር ተናግሮአል” አለ፤ ከዚያም በኋላ እኔ ከዚያ ተነሥቼ ሄድኩ።
12ነቢዩ ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ ጫንቃ ላይ ከሰበረ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13“ሂድ! ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ‘እነሆ አንተ የእንጨቱን ቀንበር ለመስበር ችለሃል፤ እኔ ግን በእርሱ ፈንታ የብረት ቀንበር እተካለሁ፤ 14በእነዚህ ሕዝቦች ሁሉ ጫንቃ ላይ የብረት ቀንበር እጭናለሁ፤ እነርሱም ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ይገዙለታል፤ ሌላው ቀርቶ የምድረ በዳ እንስሶች ሁሉ እንዲገዙለት አደርጋለሁ፤’ እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ።”
15እኔም ይህንኑ ለሐናንያ እንዲህ ብዬ ነገርኩት፦ “ሐናንያ ሆይ! ስማ፤ አንተን እኮ እግዚአብሔር አላከህም፤ ይህንንም ሁሉ ሕዝብ ሐሰት በሆነ ነገር እንዲተማመን አድርገሃል። 16ስለዚህም እግዚአብሔር ‘አንተን ከምድረ ገጽ አስወግድሃለሁ ይህ ሕዝብ በእኔ በአምላካቸው ላይ እንዲያምፁ በማድረግህ ምክንያት ይህ ዓመት ከመፈጸሙ በፊት ትሞታለህ’ ይላል።”
17ነቢዩ ሐናንያም በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 28: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997