መጽሐፈ ኢያሱ 6
6
የኢያሪኮ አወዳደቅ
1እስራኤላውያንን ከመፍራት የተነሣ የኢያሪኮ ቅጽር በሮች ተዘግተው ነበር፤ ወደ ከተማይቱ መግባትም ሆነ መውጣት የሚችል ማንም አልነበረም፤ 2እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ኢያሪኮን ከንጉሥዋና ከወታደሮችዋ ጋር በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ 3አንተና ወታደሮችህ እስከ ስድስት ቀን ድረስ በቀን አንድ ጊዜ የከተማይቱን ቅጽር በሰልፍ ትዞሩአታላችሁ። 4እያንዳንዳቸው እምቢልታ የያዙ ሰባት ካህናት ከቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ቀድመው ይሂዱ፤ በሰባተኛው ቀን ካህናቱ እምቢልታ እየነፉ አንተና ወታደሮችህ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ትዞሩአታላችሁ፤ 5ከዚያን በኋላ ካህናቱ በእምቢልታቸው ከፍተኛ ድምፅ እንዲሰማ ያድርጉ፤ እርሱንም እንደ ሰማችሁ ወዲያውኑ ሰዎቹ ሁሉ በከፍተኛ ድምፅ ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጽር ይፈርሳል፤ ከዚህም በኋላ መላው ሠራዊት ወደ ከተማይቱ ሰተት ብሎ በቀጥታ ይግባ።”
6ኢያሱም ካህናቱን ጠርቶ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ከእናንተም ሰባታችሁ እምቢልታ ይዛችሁ ከታቦቱ ፊት ቅደሙ።” 7ሕዝቡንም እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “ሂዱ፤ ከተማይቱን ዙሩ፤ ወታደሮቹም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ”።
8ኢያሱ ሕዝቡን ባዘዘው መሠረት በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀንደ መለከት የያዙ ሰባት ካህናት ቀንደ መለከቱን እየነፉ ወደፊት ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ተከተላቸው። 9ወታደሮቹም ቀንደ እምቢልታ ከሚነፉት ካህናት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱ እምቢልታውን ሳያቋርጡ እየነፉ ሕዝቡ ከታቦቱ በኋላ ይከተል ነበር። 10ኢያሱ ግን፦ “ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ እንዳትጮኹ፤ ወይም ድምፃችሁ እንዳይሰማ፤ እንዲያውም አንዲት ቃል እንኳ እንዳትናገሩ፤ ጩኹ ስላችሁ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ” ብሎ ሕዝቡን አዘዘ። 11በዚህ ዐይነት የእግዚአብሔር ታቦት ከተማዋን አንድ ጊዜ እንዲዞር አደረገ፤ ከዚያ በኋላ ሕዝቡ፥ ወደ ሰፈሩ ተመልሶ በዚያ ዐዳር ሆነ። 12በማግስቱ ኢያሱ በማለዳ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። 13ሰባቱን እምቢልታ የያዙት ሰባት ካህናት እምቢልታቸውን ሳያቋርጡ እየነፉ ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት ለፊት ሄዱ፤ መለከቱ ሳያቋርጥ እየተነፋ ወታደሮቹ ከካህናቱ ቀድመው ሌላው ሕዝብ ደግሞ ከታቦቱ በኋላ ይከተል ነበር። 14በዚህም በሁለተኛው ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ እስከ ስድስት ቀንም በዚሁ ዐይነት አደረጉ።
15በሰባተኛው ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሥተው በዚሁ ተመሳሳይ ሁኔታ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩአት፤ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ የዞሩበት ቀን ይህ ብቻ ነበር። 16በሰባተኛው ዙር ካህናቱ እምቢልታ ሊነፉ በሚዘጋጁበት ጊዜ ኢያሱ ሕዝቡን፦ “እግዚአብሔር ከተማይቱን ስለ ሰጣችሁ ጩኹ!” ብሎ አዘዘ። 17“በከተማይቱና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር የተረገመ ሆኖ መደምሰስ አለበት፤ ሴትኛ ዐዳሪዋ ግን የላክናቸውን ሰላዮች ደብቃ ስላዳነች መትረፍ የሚገባቸው እርስዋና ከእርስዋ ጋር በቤትዋ ያሉት ብቻ ናቸው። 18እናንተ ግን በእስራኤል ሰፈር ችግርንና ጥፋትን እንዳታስከትሉ መደምሰስ ከሚገባቸው ነገሮች ማናቸውንም ጓጒታችሁ ከመውሰድ ራሳችሁን ጠብቁ፤ 19ብርና ወርቅ፥ ከነሐስ ወይም ከብረት የተሠራ ማናቸውም ነገር ለእግዚአብሔር የተለየ ይሁን፤ እርሱም በእግዚአብሔር የዕቃ ግምጃ ቤት መቀመጥ አለበት።”
20ስለዚህ እምቢልታ ተነፋ፤ ሕዝቡም የእምቢልታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ከፍተኛ የጩኸት ድምፅ አሰሙ የከተማይቱም ቅጽሮች ፈረሱ፤ ከዚህም በኋላ ሠራዊቱ ኮረብታውን ወጥቶ ሰተት ብሎ ወደ ከተማይቱ በመግባት በቊጥጥሩ ሥር አደረጋት፤ 21ሰይፋቸውንም መዘው በከተማይቱ የተገኘውን ወንዱንም ሴቱንም ወጣቱንና ሽማግሌውን ሁሉ ገደሉ፤ የከብት፥ የበግና የአህያውን መንጋ ሁሉ ፈጁ።
22ኢያሱ ሰላዮች ሆነው የተላኩትን ሁለት ሰዎች “ወደ ጋለሞታይቱ ረዓብ ቤት ሄዳችሁ በገባችሁላት የተስፋ ቃል መሠረት እርስዋንና ቤተሰብዋን አውጡ” አላቸው። 23እነርሱም ሄደው ረዓብን ከአባትዋና ከእናትዋ ከወንድሞችዋና ከሌሎችም የእርስዋ ወገን ከሆኑት ሰዎች ሁሉ ጋር አውጥተው ከእስራኤላውያን ሰፈር ውጪ አኖሩአቸው። 24ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ዕቃ ግምጃ ቤት ካስቀመጡአቸው ከብሩና ከወርቁ እንዲሁም በነሐስና በብረት ከተሠሩት ዕቃዎች በቀር ከተማይቱንና በእርስዋ ያሉትን ነገሮች ሁሉ አቃጠሉ። 25ነገር ግን ጋለሞታይቱ ረዓብ ኢያሱ ወደ ኢያሪኮ የላካቸውን ሁለቱን ሰላዮች ደብቃ ከሞት ስላዳነች እርሱ እርስዋን፥ ቤተ ዘመዶችዋንና ከእርስዋ ጋር ያሉትን ሌሎች ሰዎች ሁሉ ከሞት አተረፈ፤ የእርስዋም ዘሮች እስከ አሁን ድረስ በእስራኤል ምድር ይኖራሉ። #ዕብ. 11፥31።
26በዚያን ጊዜ ኢያሱ፦ “ይህቺን የኢያሪኮን ከተማ ለመገንባት የሚነሣ የተረገመ ይሁን፤
መሠረቱን ሲጥል የበኲር ልጁ ይጥፋ፤
መዝጊያውን ሲያቆም የመጨረሻ ልጁ ይጥፋ፤” ብሎ ረገመ። #1ነገ. 16፥34።
27በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የኢያሱ ዝና በአገሪቱ ሁሉ ተሰማ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997