የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢያሱ 9

9
የገባዖን ሰዎች ኢያሱን ማታለላቸው
1ከዮርዳኖስ ማዶ በተራራማውና በቈላማው አገሮች፥ በሜዲቴራኒያን ባሕር ጠረፍ፥ እስከ ሊባኖስ ድረስ ያሉት የሒታውያን፥ የአሞራውያን፥ የከነዓናውያን፥ የፔሩዛውያን የኤዊያውያንና የኢያቡሳውያን ነገሥታት ይህን በሰሙ ጊዜ፥ 2ኀይላቸውን በአንድነት አስተባብረው በኢያሱና በእስራኤላውያን ላይ ለመዝመት መጡ።
3የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በዐይ ከተማዎች ላይ ያደረገውን ሁሉ ስለ ሰሙ፤ 4እርሱን ለማታለል ወሰኑ፤ እነርሱም ስንቃቸውን አዘጋጅተው፥ አሮጌ ስልቻና ቀዳዳው ተለጥፎ የተሰፋ የወይን ጠጅ አቁማዳ በአህዮች ጫኑ፤ 5ተቀዳዶ ያለቀ አሮጌ ልብስ ለብሰው፥ የተጠጋገነ እላቂ ጫማ አደረጉ፤ ለስንቅ የያዙትም እንጀራ ደረቅና የሻገተ ነበር። 6ይህን ሁሉ ካደረጉ በኋላ በጌልገላ ወደሚገኘው ሰፈር ሄደው ኢያሱንና እስራኤላውያንን፦ “እኛ የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ የመጣነውም ከእናንተ ጋር የቃል ኪዳን ውል ለማድረግ ነው” አሉአቸው።
7የእስራኤል ሰዎች ግን የገባዖንን ሰዎች “ከእናንተ ጋር እንዴት ውል እናደርጋለን? ምናልባትም እናንተ በእኛ መካከል የምትኖሩ ልትሆኑ ትችላላችሁ” አሉአቸው። #ዘፀ. 23፥32፤ 34፥12፤ ዘዳ. 7፥2።
8የገባዖንም ሰዎች ኢያሱን “እኛ አገልጋዮችህ ነን” አሉት።
ኢያሱም “እናንተ እነማን ናችሁ? የመጣችሁትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
9እነርሱም ይህን ታሪክ ነገሩት፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር በግብጽ ያደረገውን ሁሉ ስለ ሰማን እኛ የመጣነው በጣም ሩቅ ከሆነ አገር ነው፤ 10እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ በስተምሥራቅ በነበሩት በሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት ላይ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል፤ እነዚህም ሁለቱ ነገሥታት በዐስታሮት ይኖሩ የነበሩት የሐሴቦን ንጉሥ ሲሖንና የባሳን ንጉሥ ዖግ ናቸው። #ዘኍ. 21፥21-35። 11መሪዎቻችንና በምድራችን የሚኖሩት ሕዝቦች ሁሉ ለመንገዳችን የሚሆነንን ስንቅ አዘጋጅተን መጥተን ከእናንተ ጋር እንድንገናኝ ልከውናል፤ ለእናንተ የምንታዘዝ አገልጋዮች እንድንሆንና እናንተም ከእኛ ጋር የሰላም ውል እንድታደርጉ እንጠይቃችሁ ዘንድ አዘውናል። 12የያዝነውን ስንቅ ተመልከቱ! ከቤት ተነሥተን ከእናንተ ጋር ለመገናኘት ጒዞ ስንጀምር ገና ትኩስ እንጀራ ነበር፤ አሁን ግን ደረቅና የሻገተ መሆኑን ተመልከቱ! 13እነዚህንም የወይን አቁማዳዎች በሞላናቸው ጊዜ ገና አዲስ ነበሩ፤ አሁን ግን የተቀደዱ መሆናቸውን ተመልከቱ! ከጒዞው ርቀት የተነሣ እነሆ፥ ልብሳችንም ጫማችንም አልቆአል።”
14የእስራኤልም ሰዎች ከመንገደኞቹ ስንቅ ጥቂት ወሰዱ፤ ስለ ሁኔታው ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ አልጠየቁም። 15ስለዚህም ኢያሱ ከእነርሱ ጋር ለሕይወታቸው ዋስትና ቃል ኪዳን በመግባት የሰላም ስምምነት አደረገ። የእስራኤል ሕዝብ መሪዎችም ስምምነቱን ለመጠበቅ ቃል ገቡላቸው።
16ስምምነቱ በተደረገ በሦስተኛውም ቀን እነዚህ ሰዎች ጐረቤቶቻቸው መሆናቸውንና በመካከላቸውም እንደሚኖሩ ሰሙ፤ 17ስለዚህም የእስራኤል ሕዝብ ጒዞ ጀምረው ከሦስት ቀን በኋላ እነዚህ ሕዝብ ወደሚኖሩባቸው ከተሞች ደረሱ፤ ከተሞቻቸውም ገባዖን፥ ከፊራ፥ በኤሮትና ቂርያትይዓሪም ተብለው ይጠሩ ነበር፤ 18የሕዝቡ መሪዎች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ምለውላቸው ስለ ነበረ እስራኤላውያን እነርሱን አልገደሉአቸውም። ስለዚሁም ጉዳይ እስራኤላውያን ሁሉ በመሪዎቻቸው ላይ አጒረመረሙ፤ 19መሪዎቹ ግን እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ቃል ገብተንላቸዋል፤ ስለዚህም አሁን ጒዳት ልናደርስባቸው አይገባም፤ 20ለእነርሱ የምናደርገው እንደዚህ ነው፦ ለእነርሱ ስለማልንላቸው መሐላ የእግዚአብሔር ቊጣ እንዳይደርስብን በሕይወት እንዲኖሩ እንተዋቸው። 21መሪዎቹም ስለ እነርሱ በወሰኑት መሠረት፦ ይኑሩ፤ ነገር ግን ለመላው ማኅበር እንጨት በመልቀምና ውሃ በመቅዳት ያገልግሉ” አሉ።
22ኢያሱም የገባዖንን ሕዝብ ወደ እርሱ ፊት እንዲቀርቡ አድርጎ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “በዚሁ በቅርብ የምትኖሩ ሲሆን፥ በጣም ሩቅ ከሆነ አገር የመጣን ነን ብላችሁ ስለምን አታለላችሁን? 23ይህን በማድረጋችሁ ምክንያት እግዚአብሔር ፈርዶባችኋል፤ ስለዚህም የእናንተ ሕዝብ እንጨት በመቊረጥና ውሃ በመቅዳት ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለዘለዓለም አገልጋዩ ይሆናል።”
24እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ጌታችን ሆይ! እኛ አገልጋዮችህ በእርግጥ ይህን አድርገናል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እናንተ በውስጧ የሚኖሩትን ሕዝብ በመግደል ምድሪቱን ያወርሳችሁ ዘንድ አገልጋዩን ሙሴን ያዘዘው መሆኑን ዐውቀናል፤ ይህንንም ያደረግነው እናንተን ከመፍራታችን የተነሣ ሕይወታችንን ለማትረፍ ፈልገን ነው። 25እነሆ፥ አሁን በእናንተ ሥልጣን ሥር ነን፤ መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግብን።” 26ስለዚህም ኢያሱ፥ ከእስራኤል ሕዝብ ወገን ማንም እንዳይገድላቸውና ተጠብቀው እንዲኖሩ አደረገ። 27ነገር ግን በዚሁ ጊዜ እንጨት በመቊረጥና ውሃ በመቅዳት ለእስራኤል ሕዝብና ለእግዚአብሔር መሠዊያ አገልጋዮች እንዲሆኑ አደረገ። እነርሱም እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ቦታ፥ ይህንኑ አገልግሎት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ