ሰቈቃወ ኤርምያስ 4

4
በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚደርሰው ቅጣት
1ቤተ መቅደስ የታነጸባቸው ድንጋዮች በየመንገዱ ተበታተኑ።
ወርቁ እንዴት ደበዘዘ!
ንጹሑስ ወርቅ እንዴት ተለወጠ!
2የከበሩ የጽዮን ልጆች እንደ ንጹሕ ወርቅ ያኽል ውድ ነበሩ፤
እንዴት አሁን የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው
እንደ ሸክላ ዕቃ ተቈጠሩ!
3ቀበሮዎች እንኳን የወለዱአቸውን ከጡታቸው ይመግባሉ፤
ሕዝቤ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጎኖች ጨካኞች ሆነዋል።
4በውሃ ጥም ምክንያት የሕፃናት ምላስ ከትናጋቸው ጋር ተጣበቀ፤
ልጆቻቸው ምግብ ይለምናሉ፤
ነገር ግን ምንም ነገር የሚሰጣቸው ሰው የለም።
5ቀደም ብለው ምርጥ ምግብ ይመገቡ የነበሩት፥
አሁን በመንገድ ላይ ወድቀዋል።
ሐምራዊ ልብስ ለብሰው ያደጉት
አሁን በዐመድ ክምር ላይ ተጋደሙ።
6በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት
የማንም እጅ ሳያርፍበት በቅጽበት ከተገለበጠችው
ከሰዶም ቅጣት የበለጠ ነው። #ዘፍ. 19፥24።
7ልዑላን መሳፍንታችን ርኲሰት የማይገኝባቸው፥
ከበረዶ ይልቅ የጠሩ፥ ከወተትም ይልቅ የነጡ ነበሩ፤
መልካቸውም እንደ ሰንፔር ያማረ ነበር፤
8አሁን ግን ፊታቸው እንደ ጥላሸት ስለ ጠቈረ፥
በየመንገዱ ወድቀው ሲገኙ የሚያውቃቸው የለም፤
እንደ እንጨት የደረቀ ቆዳቸው በአጥንታቸው ላይ ተጣብቆአል።
9የምድር ምርትን በማጣት ቀስ በቀስ በራብ ከመሞት ይልቅ
በጦርነት የሚሞቱት የተሻሉ ነበሩ።
10የርኅሩኅ ሴቶች እጆች የገዛ ልጆቻቸውን ቀቀሉ፤
ከተማዋ በተደመሰሰች ጊዜ
እነዚያ የተቀቀሉ ልጆች ለሰዎች ምግብ ሆኑ። #ዘዳ. 28፥57፤ ሕዝ. 5፥10።
11እግዚአብሔር ኀይለኛ ቊጣውን ገለጠ፤
የጽዮንን መሠረት የሚያጠፋ፥
የተቀጣጠለ እሳት የመሰለ መዓቱን አወረደ።
12የምድር ነገሥታትም ሆኑ የዓለም ሕዝቦች
በኢየሩሳሌም የቅጽር በሮች
ጠላት ይገባል ብለው አላመኑም።
13ይህም የሆነው በመካከልዋ የንጹሓንን ደም ባፈሰሱት
በካህናትዋ በደልና በነቢያትዋ ኃጢአት ምክንያት ነው።
14እነርሱ በደም የረከሱ ስለ ሆኑ
ሰው ልብሳቸውን እንኳ ለመንካት አይደፍርም፤
እነርሱ ግን እንደ ዕውሮች በመንገድ ላይ ይንከራተታሉ።
15ስለዚህም ሕዝቡ “ወዲያ ሂዱ!
ስለ ረከሳችሁም አትንኩን!” እያሉ ይጮኹባቸዋል።
ስለዚህ እነርሱ ስደተኞችና ተንከራታቾች ሆኑ
ሕዝቦችም “ከእንግዲህ በመካከላችን አይቈዩም” አሉ።
16እግዚአብሔር ራሱ የበተናቸው ስለ ሆነ፥
ከእንግዲህ ወዲህ ስለ እነርሱ አያስብም፤
ለካህናቱ ክብር አይሰጣቸውም፤
ሽማግሌዎችም ልዩ አስተያየት አይደረግላቸውም።
17በከንቱ ረዳት በመጠበቅ ዐይናችን ደከመ
ሊታደግ ከማይችል ሕዝብ በጒጒት ርዳታ ጠበቅን።
18ጠላትም በየመንገዱ መዘዋወር እንዳንችል
በዐይነ ቊራኛ ይጠባበቀን ነበር፤
ዘመናችን ቀርቦአል፤ ዘመናችን አልቆአል፤
ፍጻሜውም ደርሶአል።
19አሳዳጆቻችን በሰማይ ከሚበርሩ ንስሮች የፈጠኑ ነበሩ፤
በተራሮች ላይ አሳደዱን፤
በበረሓም ሸመቁብን።
20በሕዝቦች መካከል በእርሱ ጥላ ሥር እንኖራለን
ብለን ያሰብነውን እግዚአብሔር የቀባውን
የሕይወት እስትንፋሳችን አጠመዱብን።
21እናንተ በዑፅ ምድር የምትኖሩ የኤዶም ሕዝብ ሆይ
ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ!
ይሁን እንጂ የእናንተም ጽዋ
ተራውን ጠብቆ በመምጣት ላይ ነው፤
እናንተም ሰክራችሁ ትራቈታላችሁ።
22የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! የበደላችሁ ቅጣት አብቅቶአል፤
ከእንግዲህ ወዲህ በስደት እንድትኖሩ አያደርጋችሁም፤
ነገር ግን የኤዶም ሕዝብ ሆይ! የእናንተን በደል ይቀጣል፤
ኃጢአታችሁንም ያጋልጣል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ