የሉቃስ ወንጌል 24:13-35

የሉቃስ ወንጌል 24:13-35 አማ05

በዚያኑ ቀን ከኢየሱስ ተከታዮች ሁለቱ ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያኽል ርቃ ወደምትገኝ ኤማሁስ ተብላ ወደምትጠራ መንደር ይጓዙ ነበር። እነርሱም ይህን የሆነውን ነገር ሁሉ አንሥተው እርስ በእርሳቸው ይወያዩ ነበር። ይህንንም በሚያወሩበትና በሚወያዩበት ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ቀርቦ አብሮአቸው ይጓዝ ጀመር። ነገር ግን በዐይናቸው እያዩት ማን እንደ ሆነ ማወቅ አልቻሉም። እርሱም “በጒዞ ላይ ሳላችሁ የምትነጋገሩበት ይህ ነገር ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም እያዘኑ ቀጥ ብለው ቆሙ። ከእነርሱም አንዱ ቀለዮጳ የሚባለው፥ “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም ውስጥ የተፈጸሙትን ነገሮች የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” አለው። ኢየሱስም “ምንድን ነው እርሱ?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በናዝሬቱ ኢየሱስ ላይ ስለ ተፈጸመው ነገር ነዋ! እርሱ በእግዚአብሔርና በሰዎች ሁሉ ፊት በቃልና በሥራ ብርቱ የሆነ ነቢይ ነበር። የካህናት አለቆችና መሪዎቻችን ለሞት ፍርድ አሳልፈው ሰጡት፤ እንዲሁም ሰቀሉት። እኛ ግን ‘እስራኤልን የሚያድን እርሱ ነው’ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ነገር ከተፈጸመ እነሆ፥ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑ ነው። እንዲያውም ከእኛ መካከል ያሉ አንዳንድ ሴቶች አስገርመውናል፤ እነርሱ ዛሬ በማለዳ ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር፤ ነገር ግን የእርሱን አስከሬን አላገኙም፤ ‘ሕያው ሆኖአል!’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን እያሉም ተመልሰው መጡ። ከእኛም አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ ሄደው ልክ ሴቶቹ እንዳሉት ሆኖ አገኙ፤ ኢየሱስን ግን አላዩትም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉና ነቢያት የተናገሩትንም ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ! መሲሕ ይህን ሁሉ መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት መጻሕፍት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ስለ እርሱ የተነገረውን እየጠቀሰ አስረዳቸው። እነርሱ ወደሚሄዱበት መንደር በቀረቡ ጊዜ ኢየሱስ አልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን “ቀኑ መሽቶአል፤ ፀሐይም መጥለቅዋ ነው፤ ስለዚህ ከእኛ ጋር እዚህ ዕደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት፤ በዚህ ምክንያት ከእነርሱ ጋር ሊያድር ወደ ቤት ገባ። ከእነርሱም ጋር በማእድ ተቀመጠ፤ እንጀራ አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ቈርሶ ሰጣቸው። በዚያን ጊዜ ዐይናቸው ተከፈተና ኢየሱስ መሆኑን ዐወቁ፤ እርሱ ግን ወዲያው ከዐይናቸው ተሰወረ። እነርሱም እርስ በርሳቸው “በመንገድ ሳለን ሲነግረንና ቅዱሳት መጻሕፍትንም እየጠቀሰ ሲያስረዳን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠል አልነበረምን?” ተባባሉ። እነርሱም በዚያችው ሰዓት ተነሡና ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ፤ በዚያም ዐሥራ አንዱን ደቀ መዛሙርት አብረዋቸው ካሉት ጋር በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም “ጌታ ኢየሱስ በእርግጥ ተነሥቶአል! ለስምዖንም ታይቶአል!” ይሉ ነበር። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት በበኩላቸው በመንገድ ላይ የሆነውን ነገርና ጌታ ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁትም ተረኩላቸው።