የሉቃስ ወንጌል 4
4
የኢየሱስ መፈተን
(ማቴ. 4፥1-11፤ ማር. 1፥12-13)
1ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ወንዝ ተመለሰ፤ ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ወደ በረሓ ሄደ። 2እዚያም አርባ ቀን በዲያብሎስ ተፈተነ፤ በእነዚያም ቀኖች ምንም ስላልበላ በመጨረሻ ተራበ።
3ዲያብሎስም ኢየሱስን፦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ይህን ድንጋይ እንጀራ እንዲሆን እዘዝ” አለው።
4ኢየሱስም፦ “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት። #ዘዳ. 8፥3።
5ከዚህም በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ አንድ ከፍተኛ ቦታ ላይ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። 6“ይህን ሁሉ ሥልጣንና ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ይህ ሁሉ ለእኔ የተሰጠኝ ስለ ሆነ ለፈለግሁት መስጠት እችላለሁ፤ 7ስለዚህ አንተ ለእኔ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል፤” አለው።
8ኢየሱስም፦ “ለጌታ ለአምላክህ ብቻ ስገድ! እርሱንም ብቻ አምልክ! ተብሎ ተጽፎአል፤” ሲል መለሰለት። #ዘዳ. 6፥13።
9ከዚያም በኋላ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደው፤ በቤተ መቅደሱም ጣራ ጫፍ ላይ እንዲቆም አድርጎ፥ እንዲህ አለው፦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ፥ እስቲ ከዚህ ወደታች ዘለህ ውረድ፤ 10‘አንተን እንዲጠብቁህ እግዚአብሔር መላእክቱን ያዛል፤ #መዝ. 91፥11። 11እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል፥ በእጃቸው ደግፈው ይይዙሃል፥’ ተብሎ ተጽፎአልና፤” አለው። #መዝ. 91፥12።
12ኢየሱስም፦ “ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው፥’ ተብሎ ተጽፎአል፤” ሲል መለሰለት። #ዘዳ. 6፥16።
13ዲያብሎስ ኢየሱስን መፈተኑን ከጨረሰ በኋላ ለጊዜው ትቶት ሄደ።
ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ እንደ ጀመረ
(ማቴ. 4፥12-17፤ ማር. 1፥14-15)
14ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተሞልቶ ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አካባቢዎች ሁሉ ተሰማ። 15በምኲራቦቻቸውም ያስተምር ነበር፤ ሁሉም በትምህርቱ አመሰገኑት።
ኢየሱስ በናዝሬት የደረሰበት ተቃውሞ
(ማቴ. 13፥53-58፤ ማር. 6፥1-6)
16ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ አደገበት አገር ወደ ናዝሬት ሄደ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኲራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ፤ 17የነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ተሰጠው፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ፥ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ቦታ አገኘ፤
18“የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤
መልካም ዜናን ለድኾች እንዳበሥር ሾሞኛል፤
ለታሰሩት መፈታትን፥
ለዕውሮች ማየትን እንዳውጅና
የተጨቈኑትንም ነጻ እንዳወጣ ልኮኛል፤
19እንዲሁም ጌታ ሕዝቡን የሚያድንበትን
የጸጋ ዓመት እንዳስታውቅ ልኮኛል።” #ኢሳ. 61፥1-2።
20ኢየሱስ መጽሐፉን አጥፎ ለአስተናባሪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራቡ የነበሩትም ሁሉ ትኲር ብለው ወደ እርሱ ይመለከቱ ጀመር፤ 21እርሱም “እነሆ! ይህ አሁን ሲነበብ የሰማችሁት የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ዛሬ ተፈጸመ” አላቸው።
22ስለ እርሱ ሁሉም መልካም ይናገሩ ነበር፤ በሚናገረውም ጸጋን የተመላ ቃል ተደንቀው “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” አሉ።
23ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ ‘አንተ ሐኪም፥ እስቲ ራስህን አድን፥’ የሚለውን ምሳሌ እንደምትጠቅሱብኝ እርግጠኛ ነኝ፤ እንዲሁም ‘በቅፍርናሆም አድርገሃል ሲሉ የሰማነውን ሁሉ፥ እዚህም በገዛ አገርህ አድርግ’ ትሉኛላችሁ። 24በእውነት እላችኋለሁ፤ ነቢይ በገዛ አገሩ ሰዎች ዘንድ አይከበርም። #ዮሐ. 4፥44።
25“ስሙኝ እውነቱን ልንገራችሁ፤ በነቢዩ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናም ባለመዝነቡ በአገሩ ሁሉ ብርቱ ራብ ሆኖ ነበር፤ በዚያን ጊዜ በእስራኤል አገር ብዙ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ነበሩ። #1ነገ. 17፥8-16። 26ነገር ግን ኤልያስ፥ በሲዶና አገር ሰራጵታ በምትባል መንደር ወደምትገኘው ወደ አንዲት ባልዋ የሞተባት ሴት ብቻ ተላከ እንጂ ወደ ሌላ ወደ ማንም አልተላከም። 27እንዲሁም በነቢዩ በኤልሳዕ ጊዜ ብዙ ለምጻሞች በእስራኤል አገር ነበሩ፤ ነገር ግን ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር፥ ከእነርሱ አንድ እንኳ አልነጻም።” #2ነገ. 5፥1-14።
28በምኲራብ የነበሩትም ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። 29ተነሥተውም ኢየሱስን ጐትተው ከከተማ ውጪ አወጡት፤ ወደ ገደልም ገፍትረው ሊጥሉት ፈልገው ከተማቸው ወደ ተሠራችበት ኰረብታ አፋፍ ላይ ወሰዱት። 30እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።
ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው እንደ ዳነ
(ማር. 1፥21-28)
31ከዚህም በኋላ፥ ኢየሱስ በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ከተማ ወደ ቅፍርናሆም ሄደ፤ በዚያም፥ ሕዝቡን በሰንበት ቀን ያስተምር ነበር። 32በሥልጣን ቃል ይናገር ስለ ነበር ሁሉም በትምህርቱ ይደነቁ ነበር። #ማቴ. 7፥28-29። 33እዚያም በምኲራብ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ነበር፤ እርሱ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ ጮኸ፤ 34“የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኛ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? ልታጠፋን መጣህን? አንተ ማን እንደ ሆንክ እኔ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ።”
35ኢየሱስም ርኩሱን መንፈስ፥ “ዝም ብለህ ከእርሱ ውጣ!” ሲል ገሠጸው፤ ርኩሱ መንፈስ ሰውየውን በሕዝቡ ፊት ጣለውና ምንም ሳይጐዳው ወጣ።
36ሁሉም በመደነቅ እርስ በርሳቸው፥ “ይህ ምን ዐይነት ቃል ነው? በሥልጣንና በኀይል ርኩሳን መናፍስትን ያዛል፤ እነርሱም ታዘው ይወጣሉ፤” ተባባሉ። 37የኢየሱስም ዝና በዚያ አገር ዙሪያ ሁሉ ተሰማ።
ኢየሱስ ብዙ ሕመምተኞችን መፈወሱ
(ማቴ. 8፥14-17፤ ማር. 1፥29-34)
38ኢየሱስ ከምኲራብ ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ሄደ፤ እዚያም የስምዖን ዐማት በጣም አተኲሶአት ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለዚህ እንዲያድናት ኢየሱስን ለመኑት። 39ኢየሱስም ወደ እርስዋ ቀርቦ አጠገብዋ ቆመና ትኲሳቱ እንዲለቃት አዘዘ፤ ትኲሳቱም ለቀቃት፤ ወዲያውኑም ተነሥታ ታስተናግዳቸው ጀመር።
40ፀሐይ ስትጠልቅ ሰዎች በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙባቸውን ሕመምተኞች ሁሉ ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን በመጫን ፈወሳቸው። 41አጋንንትም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉ በመጮኽ ብዙ ሰዎችን እየለቀቁ ይወጡ ነበር፤ እርሱ መሲሕ መሆኑንም ዐውቀው ነበር፤
ኢየሱስ ግን ስለ እርሱ ምንም እንዳይናገሩ በመገሠጽ ይከለክላቸው ነበር።
ኢየሱስ በገሊላ ማስተማሩ
(ማቴ. 4፥23-25፤ ማር. 1፥35-39)
42በነጋም ጊዜ ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ሰው ወደሌለበት ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ሄደ፤ ሰዎቹም ይፈልጉት ነበር፤ ባገኙትም ጊዜ “ተለይተኸን አትሂድብን” ብለው ለመኑት። 43እርሱ ግን “እኔ የተላክሁት ለዚህ ስለ ሆነ ወደ ሌሎችም ከተሞች ሄጄ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል ማብሠር ይገባኛል፤” አላቸው።
44ስለዚህ በይሁዳም ምኲራቦች ሁሉ እየተዘዋወረ ይሰብክ ነበር።
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997