የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 11

11
ከመጥምቁ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ የተላኩ መልእክተኞች
(ሉቃ. 7፥18-35)
1ኢየሱስ እነዚህን ትእዛዞች ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከሰጠ በኋላ ያን ቦታ ትቶ በአቅራቢያው ወደሚገኙት ከተሞች ሊሰብክና ሊያስተምር ሄደ።
2መጥምቁ ዮሐንስ በወህኒ ቤት ሳለ፥ የክርስቶስን ሥራ በመሰማቱ ሁለት ደቀ መዛሙርት ልኮ፥ 3“ያ ይመጣል የተባለው መሲሕ አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ብለው ኢየሱስን እንዲጠይቁት አደረገ። 4ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሂዱና ያያችሁትንና የሰማችሁትን ሁሉ ለዮሐንስ ንገሩት። 5እነሆ፥ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ቀጥ ብለው ይሄዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤ #ኢሳ. 35፥5-6፤ 61፥1። 6ስለ እኔ የማይጠራጠር የተባረከ ነው።”
7የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ፥ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤ “ለመሆኑ ምን ልታዩ ወደ በረሓ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸንበቆ ለማየት ነውን? 8ደግሞስ ምን ለማየት ወጣችሁ? የተዋበ ልብስ የለበሰውን ሰው ለማየት ነውን? የተዋበ ልብስ የሚለብሱማ በነገሥታት ቤት ይገኛሉ። 9ታዲያ፥ ስለምን ወጣችሁ? ነቢይ ለማየት ነውን? አዎ፥ እንዲያውም ከነቢይ በጣም የሚበልጠውን ለማየት ነው እላችኋለሁ። 10እርሱ ‘እነሆ፥ እፊት እፊትህ እየሄደ፥ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ በፊት እልካለሁ’ ተብሎ የተጻፈለት ነው። #ሚል. 3፥1። 11በእውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዷቸው ሰዎች መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም። ነገር ግን በመንግሥተ ሰማያት በጣም የሚያንሰው ይበልጠዋል። 12ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማይ በጣም ትገፋለች በብርቱ የሚታገሉም ያገኙአታል። #11፥12 ትገፋለች፦ መገፋትና መታገል የሚያመለክቱት የክፋት ኀይሎችን ተቃውሞና ፈተናውን ለማለፍ መንፈሳውያን ወገኖች የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ትግል ነው።
13“መላው የነቢያት ትምህርትና በሙሴ እጅ የተሰጠው ሕግ እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋል። #ሉቃ. 16፥16። 14እንግዲህ እነርሱ የተናገሩትን ለመቀበል ከፈቀዳችሁ፥ ያ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እነሆ፥ ይህ ዮሐንስ ነው። #ሚል. 4፥5፤ ማቴ. 17፥10-13፤ ማር. 9፥11-13። 15የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ!
16“ነገር ግን የዚህን ዘመን ሰዎች በምን አነጻጽራቸዋለሁ? በአደባባይ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እየጠሩ፥ 17‘ዋሽንት ነፋንላችሁ አልጨፈራችሁም! ሙሾ አወረድንላችሁ አላለቀሳችሁም!’ የሚሉትን ልጆች ይመስላሉ። 18እንዲሁም መጥምቁ ዮሐንስ በመጣ ጊዜ እህል ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፥ ‘ይህስ ጋኔን አለበት!’ አሉት፤ 19የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፥ ‘እነሆ! ይህ መብልና መጠጥ የሚወድ ነው! የቀራጮችና የኃጢአተኞችም ወዳጅ ነው!’ አሉት። ሆኖም የጥበብ ትክክለኛነት ግን በሥራዋ ይረጋገጣል።”
ባለማመናቸው የተወቀሱ ከተሞች
(ሉቃ. 10፥13-15)
20ቀጥሎም ኢየሱስ ከሌሎች ከተሞች ይበልጥ ብዙ ተአምራት ያደረገባቸውን ከተሞች፥ ንስሓ ስላልገቡ እንዲህ ሲል ይወቅሳቸው ጀመር፦ 21“ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት፥ በጢሮስና በሲዶና ከተሞች ተደርገው ቢሆን ኖሮ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሐዘን ልብስ ለብሰውና ዐመድ በላያቸው ላይ ነስንሰው ገና ዱሮ ንስሓ በገቡ ነበር! #ኢሳ. 23፥1-18፤ ሕዝ. 26፥1—28፥26፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥9-10፤ ዘካ. 9፥2-4። 22ስለዚህ በፍርድ ቀን፥ ከእናንተ ይልቅ በጢሮስና በሲዶና ይኖሩ ለነበሩት ቅጣቱ ይቀልላቸዋል እላችኋለሁ። 23አንቺም እስከ ሰማይ ከፍ ያልሽው ቅፍርናሆም! ወደ ሲኦል ትወርጂአለሽ! በአንቺ የተደረጉት ተአምራት፥ በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ ያቺ ከተማ ሳትጠፋ፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበር! #ኢሳ. 14፥13-15፤ ዘፍ. 19፥24-28። 24ስለዚህ በእውነት እልሻለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ቅጣቱ ይቀልላታል!” #ማቴ. 10፥15፤ ሉቃ. 10፥12።
በክርስቶስ ዕረፍት ማግኘት
(ሉቃ. 10፥21-22)
25በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህን ነገር ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለአላዋቂዎች ስለ ገለጥክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ 26አዎ! አባት ሆይ! ይህን ለማድረግ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኖአል። 27አባቴ ሁሉን ነገር ሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ ማንም የለም። እንዲሁም ከወልድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም፤ ማንም ወልድ ካልገለጠለት በቀር አብን ሊያውቅ አይችልም። #ዮሐ. 3፥35፤ 1፥18፤ 10፥5።
28“እናንተ በጉልበት ሥራ የደከማችሁ! ሸክምም የከበደባችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ! እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። 29ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህና ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። #ኤር. 6፥16። 30ቀንበሬ ልዝብ ነው፤ ሸክሜም ቀላል ነው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ