የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 18

18
ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?
(ማር. 9፥33-37ሉቃ. 9፥46-48)
1በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “በመንግሥተ ሰማይ ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። #ሉቃ. 22፥24። 2ኢየሱስም አንድ ሕፃን ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ፤ 3እንዲህም አለ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፦ ካልተለወጣችሁና እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም። #ማር. 10፥15፤ ሉቃ. 18፥17። 4እንደዚህ ሕፃን ራሱን ዝቅ የሚያደርግ በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል። 5እንደዚህ ያለውን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል።
ለሰው መሰናክል ከመሆን መጠንቀቅ
(ማር. 9፥42-48ሉቃ. 17፥1-2)
6“ማንም ሰው በእኔ ከሚያምኑት ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያስት ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ቢጣልና ቢሰጥም ይሻለዋል።” 7ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሰዎች እንዲሰናከሉ በሚያደርጉት ነገሮች ምክንያት ለዓለም ወዮላት! መቼም የሚያሰናክሉ ነገሮች መምጣታቸው አይቀርም፤ ነገር ግን የመሰናከያው መምጫ ለሚሆነው ለዚያ ሰው ወዮለት! 8ስለዚህ እጅህ ወይም እግርህ ኃጢአት እንድትሠራ ቢያስትህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው! ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘለዓለም እሳት ከምትጣል ይልቅ ጒንድሽ ወይም አንካሳ ሆነህ ወደ ዘለዓለም ሕይወት መግባት ይሻልሃል። #ማቴ. 5፥30። 9ዐይንህም ኃጢአት እንድትሠራ ቢያስትህ አውጥተህ ወዲያ ጣለው! ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንድ ዐይና ሆነህ ወደ ዘለዓለም ሕይወት መግባት ይሻልሃል። #ማቴ. 5፥29። 10በሰማይ ያሉት መልአኮቻቸው ዘወትር በሰማይ ያለውን ያባቴን ፊት ስለሚያዩ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ። [ 11የሰው ልጅም የመጣው የጠፋውን ለማዳን ነው።”] #18፥11 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቊ. 11 ይጨምራሉ፤ ቃሉም በሉቃ. 10 ያለውን ይመስላል። #ሉቃ. 19፥10።
ጠፍቶ የተገኘው በግ ምሳሌ
(ሉቃ. 15፥3-7)
12ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እስቲ ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን አንዱን ለመፈለግ አይሄድምን? 13እውነት እላችኋለሁ፤ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ በተገኘው በግ ደስ ይለዋል። 14እንዲሁም በሰማይ ያለው አባታችሁ ከነዚህ ከታናናሾች አንዱም እንዲጠፋ አይፈልግም።
ለበደለ ሰው ምን ማድረግ እንደሚገባ
15“ወንድምህ ቢበድልህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ በደሉን ንገረው፤ ቢሰማህ እንደገና ወንድምህ እንዲሆን ታደርገዋለህ፤ #ሉቃ. 17፥3። 16ባይሰማህ ግን የሁለት ወይም የሦስት ሰዎች ምስክርነት ስለሚጸና ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ይዘህ ወደ እርሱ ሂድ። #ዘዳ. 19፥15። 17እነርሱንም አልሰማም ቢል ለቤተ ክርስቲያን ንገር፤ ቤተ ክርስቲያንንም የማይሰማ ከሆነ እንደ አረመኔና ተጸጽቶ እንደማይመለስ ኃጢአተኛ ቊጠረው።
18“በእውነት እላችኋለሁ፤ በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱትም በሰማይ የተፈታ ይሆናል። #ማቴ. 16፥19፤ ዮሐ. 20፥23። 19ደግሞም እላችኋለሁ፤ ከእናንተ ሁለቱ በምድር ላይ ማናቸውንም ነገር ለመለመን ተስማምተው ቢጸልዩ፥ በሰማይ ያለው አባቴ ይፈጽምላቸዋል። 20ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በስሜ በሚሰበሰቡበት ስፍራ እኔ በመካከላቸው እገኛለሁ።”
ይቅርታ ስለ ማድረግ
21በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፦ “ጌታ ሆይ! ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” ሲል ጠየቀው። #ሉቃ. 17፥3-4።
22ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም፤ #ዘፍ. 4፥24። 23ስለዚህ መንግሥተ ሰማይ ከአገልጋዮቹ ጋር ሊተሳሰብ የፈለገውን ንጉሥ ትመስላለች፤ 24ንጉሡ መተሳሰብ በጀመረ ጊዜ በብዙ ሺህ መክሊት የሚቈጠር ዕዳ ያለበት አንድ አገልጋይ ተይዞ መጣ። #18፥24 መክሊት፦ አንድ መክሊት በዚያን ጊዜ የዐሥራ አምስት ዓመት የቀን ሠራተኛ ከሚከፈለው ደመወዝ በላይ ነበር። 25ይህ አገልጋይ ዕዳውን መክፈል ስላልቻለ እርሱም፥ ሚስቱም፥ ልጆቹም፥ ያለውም ንብረት ሁሉ ተሸጦ ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። 26አገልጋዩ ግን በጌታው እግር ሥር ተንበርክኮ ‘ጌታ ሆይ! እባክህ ታገሠኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ!’ ሲል ለመነው። 27ጌታውም ራራለትና ለቀቀው፤ ዕዳውንም ተወለት።
28“ነገር ግን ያ አገልጋይ ከዚያ ወጥቶ ሲሄድ ሳለ መቶ ዲናር ያበደረውን የሥራ ጓደኛውን አገኘና አንገቱን አንቆ ይዞ፥ ‘ያበደርኩህን ገንዘብ ክፈለኝ!’ አለው። #18፥28 ዲናር፦ የአንድ የቀን ሠራተኛ የአንድ ቀን ደመወዝ ነው። 29አገልጋይ ጓደኛውም በእግሩ ሥር ወድቆ፥ ‘እባክህ ታገሠኝ፤ እከፍልሃለሁ!’ ሲል ለመነው። 30ሰውየው ግን እምቢ አለው። እንዲያውም ይዞት ሄደና ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወህኒ ቤት አሳሰረው። 31እንደርሱ ያሉ ሌሎች የሥራ ጓደኞቹ ይህን ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት። 32ጌትዮውም ያን አገልጋይ አስጠርቶ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ አገልጋይ! ስለ ለመንከኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውኩልህ፤ 33ታዲያ፥ እኔ ዕዳህን እንደ ተውኩልህ፥ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው አገልጋይ ዕዳውን ልትተውለት አይገባህም ነበርን?’ 34ስለዚህ ጌታው ተቈጥቶ ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍል ድረስ ለወህኒ ቤቱ ኀላፊዎች አሳልፎ ሰጠው።
35“እንግዲህ እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልብ ይቅር ባትሉ በሰማይ ያለው አባቴም እንዲሁ ያደርግባችኋል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ