የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 20

20
የወይን አትክልት ሠራተኞች አቀጣጠር ምሳሌ
1“መንግሥተ ሰማይ በወይኑ አትክልት ቦታ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ጠዋት በማለዳ የወጣውን የአትክልት ባለቤት ትመስላለች። 2እርሱ ለእያንዳንዱ በቀን አንድ ዲናር ሊከፍል ተዋውሎ፥ ሠራተኞችን ወደ ወይኑ ተክል ቦታ ላካቸው። #20፥2 ዲናር፦ የአንድ የቀን ሠራተኛ የአንድ ቀን ደመወዝ ነው። 3በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ፥ ሥራ ፈተው በአደባባይ የቆሙትን ሌሎች ሰዎች አየ፤ 4‘እናንተም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሄዳችሁ ሥሩ፤ የሚገባችሁንም ሒሳብ እከፍላችኋለሁ’ አላቸው። 5እነርሱም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሄዱ፤ ደግሞም በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። 6በዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎች ሰዎች ቆመው አገኘና ‘እናንተስ ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው?’ ሲል ጠየቃቸው። 7እነርሱም ‘የሚቀጥረን ሰው አጥተን ነው’ አሉት፤ እርሱም ‘እንግዲያውስ፥ እናንተም ወደ ወይኑ አትክልት ቦታ ሂዱና ሥሩ’ አላቸው።
8“በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ባለቤት የሥራ ኀላፊውን ‘ሠራተኞቹን ጥራና በመጨረሻ ከተቀጠሩት ጀምረህ በፊት እስከ ተቀጠሩት ድረስ የሥራ ዋጋቸውን ክፈላቸው’ አለው። #ዘሌ. 19፥13፤ ዘዳ. 24፥15። 9ስለዚህ በዐሥራ አንድ ሰዓት የተቀጠሩት ቀርበው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 10በፊት የተቀጠሩት በቀረቡ ጊዜ ይበልጥ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። 11ገንዘቡን ተቀበሉና በወይኑ አትክልት ባለቤት ላይ እንዲህ እያሉ አጒረመረሙ፤ 12‘እነዚህ በመጨረሻ መጥተው የሠሩት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ በፀሐይ ሙቀት እየተቃጠልን በሥራ ስንደክም ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግሃቸው።’ 13የወይኑ አትክልት ባለቤትም ከሠራተኞቹ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ወዳጄ ሆይ! ምንም አልበደልኩህም፤ የተዋዋልነው በቀን አንድ ዲናር ልከፍልህ አይደለምን? 14ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያኽል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈቀድኩ። 15በገዛ ገንዘቤ የፈለግኹትን ማድረግ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ ለጋሥ ስለ ሆንኩ አንተ ትመቀኛለህ?’ ”
16ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “እንዲሁም ኋለኞች የሆኑ ፊተኞች ፊተኞች የሆኑትም ኋለኞች ይሆናሉ፤” አለ። #ማቴ. 19፥30፤ ማር. 10፥31፤ ሉቃ. 13፥30።
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ከሞት ስለ መነሣቱ ለአምስተኛ ጊዜ መናገሩ
(ማር. 10፥32-34ሉቃ. 18፥31-34)
17ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ነበር፤ በመንገድም ሳሉ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወደ እርሱ ወስዶ እንዲህ አላቸው፤ 18“እነሆ፥ አሁን ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ በዚያም የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለሕግ መምህራን ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል። 19ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ እነርሱም ያላግጡበታል፤ ይገርፉታል፤ ይሰቅሉታልም፤ ግን በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።”
የዘብዴዎስ ልጆች እናት ልመና
(ማር. 10፥35-45)
20ከዚህ በኋላ የዘብዴዎስ ልጆች እናት፥ ከልጆችዋ ጋር ወደ ኢየሱስ ቀረበችና በፊቱም ተንበርክካ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው። 21ኢየሱስም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አላት። እርስዋም “በመንግሥትህ እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ፥ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ!” አለችው።
22ኢየሱስ ግን “እናንተ የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ በቅርብ ጊዜ የምጠጣውን የመከራ ጽዋ መጠጣት ትችላላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎ እንችላለን!” አሉ።
23ኢየሱስም “በእርግጥ እኔ የምጠጣውን የመከራ ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ ነገር ግን ሰዎችን በቀኜና በግራዬ እንዲቀመጡ የማደርገው እኔ አይደለሁም፤ ይህ ቦታ የሚሰጠው አባቴ ላዘጋጀላቸው ሰዎች ነው።”
24የቀሩት ዐሥሩ ደቀ መዛሙርት ይህን ልመና በሰሙ ጊዜ በሁለቱ ወንድማማች ላይ ተቈጡ። 25ኢየሱስ ግን ሁሉንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው። “የአሕዛብ አለቆች የሕዝቦቻቸው ገዢዎች ናቸው፤ መሪዎቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣን እንዳላቸው ታውቃላችሁ። 26በእናንተስ መካከል እንዲህ መሆን አይገባም። ነገር ግን ከእናንተ መካከል ታላቅ መሆን የሚፈልግ የእናንተ አገልጋይ ይሁን። #ሉቃ. 22፥25-26። 27እንዲሁም ከእናንተ የበላይ መሆን የሚፈልግ የእናንተ ባሪያ ይሁን። #ማቴ. 23፥11፤ ማር. 9፥35፤ ሉቃ. 22፥26። 28የሰው ልጅም ለማገልገልና ብዙዎችን ለማዳን ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት መጣ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።”
ኢየሱስ ሁለት ዐይነ ስውሮችን መፈወሱ
(ማር. 10፥46-52ሉቃ. 18፥35-43)
29ከዚህ በኋላ ከኢያሪኮ ወጥተው ሲሄዱ ብዙ ሕዝብ ኢየሱስን ተከተሉት። 30እነሆ፥ በመንገድ ዳር የተቀመጡ ሁለት ዕውሮች በዚያ በኩል የሚያልፈው ኢየሱስ መሆኑን በሰሙ ጊዜ፥ “ጌታ የዳዊት ልጅ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ ጮኹ።
31ሕዝቡም “ዝም በሉ!” ብለው ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ አብዝተው ጮኹ።
32ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
33እነርሱም “ጌታ ሆይ! ዐይኖቻችን እንዲከፈቱ አድርግልን!” አሉት።
34ኢየሱስም ራራላቸውና ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ፤ ወዲያውኑ ዐይኖቻቸው አዩ፤ እነርሱም ኢየሱስን ተከተሉት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ