የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 24

24
ስለ ቤተ መቅደስ መፍረስ የኢየሱስ ትንቢት
(ማር. 13፥1-2ሉቃ. 21፥5-6)
1ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። 2እርሱ ግን “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? በእውነት እላችኋለሁ፤ አንዳችም ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ ሳይፈርስ የሚቀር የለም” አላቸው።
ከጌታ መምጣት በፊት የሚደርስ ስደትና መከራ
(ማር. 13፥3-13ሉቃ. 21፥7-19)
3ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ይህ ሁሉ ነገር የሚሆነው መቼ ነው? የመምጫህና የዘመኑ መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
4ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም ሰው እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ! 5ብዙዎች ‘እኔ መሲሕ ነኝ!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታሉ። 6የጦርነትን ድምፅና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ ይህ ሁሉ መሆን ስላለበት አትደንግጡ፤ መጨረሻው ግን ገና ነው። 7ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ በጦርነት ይነሣል፤ በልዩ ልዩ ስፍራ ራብና የምድር መናወጥ ይሆናል። 8ይህም ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቅ መጀመሪያ ይሆናል። 9በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋል፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። #ማቴ. 10፥22። 10በዚያን ጊዜ ብዙዎች ሃይማኖታቸውን በመካድ ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። 11ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤ 12ከክፋት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። 13እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል። 14ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል በመላው ዓለም ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል።
አሠቃቂው መከራ
(ማር. 13፥14-23ሉቃ. 21፥20-24)
15“ነቢዩ ዳንኤል በተናገረው መሠረት የሚያረክሰውን አጸያፊ ነገር በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ባያችሁ ጊዜ አንባቢው ያስተውል! #ዳን. 9፥27፤ 11፥31፤ 12፥11። 16በዚያን ጊዜ በይሁዳ አገር ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ። 17በጣራ ላይ ያለ ከቤቱ አንዳች ነገር ለመውሰድ አይውረድ። #ሉቃ. 17፥31። 18በእርሻም ያለ ልብሱን ለመውሰድ ወደ ኋላው አይመለስ፤ 19በዚያን ጊዜ ለነፍሰጡሮችና ለሚያጠቡ እመጫቶች ወዮላቸው! 20ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ! 21በዚያን ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ፥ ወደፊትም እርሱን የሚመስል ከቶ የማይሆን፥ ታላቅ መከራ ይሆናል። 22እነዚያ ቀኖች ባያጥሩማ ኖሮ አንድም ሰው መዳን ባልቻለ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ተመረጡት ሰዎች እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ።
23“በዚያን ጊዜ ማንም ሰው ‘እነሆ፥ መሲሕ እዚህ አለ!’ ወይም ‘እዚያ አለ!’ ቢላችሁ አትመኑ። 24ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የእግዚአብሔርን ምርጦች እንኳ ለማሳሳት ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያሳያሉ። #ዳን. 12፥1፤ ራዕ. 7፥14።
25“እንግዲህ ይህን ሁሉ ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ 26ስለዚህ ‘እነሆ፥ በበረሓ አለ!’ ቢሉአችሁ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በስውር ቦታ አለ!’ ቢሉአችሁ አትመኑ። #ሉቃ. 17፥23-24። 27መብረቅ በሰማይ ብልጭ ብሎ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል። 28በድን ወደአለበት ቦታ አሞሮች ይሰበሰባሉ። #ሉቃ. 17፥37።
የክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት
(ማር. 13፥24-27ሉቃ. 21፥25-28)
29“ከነዚያ ከመከራ ቀኖች በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኀይሎችም ይናወጣሉ። #ኢሳ. 13፥10፤ 34፥4፤ ሕዝ. 32፥7፤ ኢዩ. 2፥10፤31፤ 3፥15፤ ራዕ. 6፥12-13፤ ዳን. 7፥13፤ ዘካ. 12፥10-14፤ ራዕ. 1፥7። 30ከዚህም በኋላ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ያለቅሳሉ። የሰው ልጅም በኀይልና በታላቅ ክብር በደመና ላይ ሆኖ ሲመጣ ያዩታል፤ 31ታላቅ የእምቢልታ ድምፅ የሚያሰሙ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱ በአራቱም የዓለም ማዕዘኖች ሄደው ከሰማይ ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ ያሉትን የእርሱን ምርጥ ሰዎች ይሰበስባሉ።”
የበለስ ዛፍ ምሳሌ
(ማር. 13፥28-31ሉቃ. 21፥29-33)
32“የበለስ ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ፤ ቅርንጫፎችዋ ሲያቈጠቊጡና ቅጠሎችዋም ሲለመልሙ፥ ያ ጊዜ በጋ መቅረቡን ታውቃላችሁ። #24፥32 በጋ፦ ይህ ገለጻ የሚያመለክተው በእነርሱ አገር ዛፎች የሚያቈጠቊጡትና ቅጠሎችም የሚለመልሙት በጋ ሲቃረብ በመሆኑ ነው። 33እንዲሁም እናንተ ይህን ሁሉ ስታዩ የሰው ልጅ የሚመጣበት ጊዜ እንደ ቀረበ ዕወቁ። 34በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። 35ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።”
ጌታ የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ማንም የማያውቅ ስለ መሆኑ
(ማር. 13፥32-37ሉቃ. 17፥26-3034-36)
36“ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ በቀር የሰማይ መላእክት ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም የሚያውቅ የለም። 37በኖኅ ዘመን እንደ ነበረው ዐይነት፥ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜም እንዲሁ ይሆናል። #ዘፍ. 6፥5-8። 38በዚያን ዘመን፥ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፥ ሲያጋቡና ሲያጋቡ ነበር። 39የጥፋት ውሃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከ ወሰዳቸው ድረስ አላወቁም ነበር፤ የሰው ልጅ አመጣጥም ልክ እንዲሁ ይሆናል። 40በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ቦታ አብረው ይሠራሉ። አንደኛው ይወሰዳል ሌላው ይቀራል። 41ሁለት ሴቶች አብረው ይፈጫሉ፤ አንደኛዋ ትወሰዳለች፤ ሌላይቱ ትቀራለች። 42እንግዲህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ። 43ነገር ግን ይህን ዕወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ ነቅቶ በጠበቀ ነበር፤ ቤቱም እንዲቆፈር ባልተወም ነበር። 44እንዲሁም የሰው ልጅ በማታስቡት ሰዓት ስለሚመጣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ።” #ሉቃ. 12፥39-40።
የታማኙና የክፉው አገልጋይ ምሳሌ
(ሉቃ. 12፥41-48)
45“ለቤተሰቦቹ ምግባቸውን በጊዜው እንዲሰጣቸው፥ ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ብልኅ አገልጋይ ማን ነው? 46ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ አገልጋይ የተባረከ ነው። 47በእውነት እላችኋለሁ፤ ያን አገልጋይ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 48ያ ክፉ አገልጋይ ግን፥ ‘ጌታዬ አሁን አይመጣም ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብና 49የሥራ ጓደኞቹን መደብደብ ቢጀምር፥ ከሰካራሞችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ 50የዚያ አገልጋይ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላወቀው ሰዓት ይመጣል፤ 51ያንን አገልጋይ ጌታው ይቀጣዋል፤ ዕጣ ክፍሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ