የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 25

25
የዐሥሩ ልጃገረዶች ምሳሌ
1ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው፥ ሙሽራ ለመቀበል የወጡትን ዐሥር ልጃገረዶች ትመስላለች። #ሉቃ. 12፥35። 2ከእነርሱ አምስቱ ሞኞች፥ አምስቱ ብልኆች ነበሩ። 3ሞኞቹ ልጃገረዶች መብራታቸውን ቢይዙም ለመብራቱ የሚሆን ትርፍ ዘይት አልያዙም ነበር። 4ብልኆቹ ልጃገረዶች ግን ከመብራታቸው ጋር ትርፍ ዘይት በዕቃ ይዘው ነበር፤ 5ሙሽራው በመዘግየቱ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጭኖአቸው ተኙ።
6“እኩለ ሌሊት ሲሆን ግን ‘እነሆ፥ ሙሽራው መጣ! ውጡና ተቀበሉት!’ የሚል ውካታ ተሰማ። 7በዚያን ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። 8ሞኞቹ ልጃገረዶች ብልኆቹን መብራታችን መጥፋቱ ስለ ሆነ እባካችሁ ከዘይታችሁ ስጡን አሏቸው። 9ብልኆቹ ልጃገረዶች ግን ‘ለእኛና ለእናንተ የሚበቃ ዘይት የለንም። ይልቅስ ወደ ሱቅ ሂዱና ለእናንተ የሚሆን ዘይት ግዙ’ ሲሉ መለሱላቸው። 10ሞኞቹ ልጃገረዶች፥ ዘይት ለመግዛት በሄዱበት ወቅት ሙሽራው መጣ። ተዘጋጅተው የነበሩትም ልጃገረዶች ከሙሽራው ጋር ወደ ሠርጉ ግብዣ አዳራሽ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።
11“በኋላም የቀሩት ልጃገረዶች መጡና፦ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! እባክህ ክፈትልን!’ አሉት። 12እርሱ ግን፥ ‘በእውነት እላችኋለሁ፤ እኔ አላውቃችሁም!’ ሲል መለሰላቸው። #ሉቃ. 13፥25። 13ስለዚህ ቀኑንና ሰዓቱን ስለማታውቁ ተግታችሁ ጠብቁ።”
መክሊት የተሰጣቸው የሦስቱ አገልጋዮች ምሳሌ
(ሉቃ. 19፥11-27)
14ኢየሱስም እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦ “በዚያን ጊዜ ወደ መንግሥተ ሰማይ የመግባት ሁኔታ እንዲህ ይሆናል፦ አንድ ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው አገልጋዮቹን ጠርቶ ንብረቱን እንዳስረከባቸው ዐይነት ይሆናል። #ሉቃ. 19፥11-27። 15ጌትዮው ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በማካፈል፥ ለአንዱ አምስት መክሊት፥ ለአንዱ ሁለት መክሊት፥ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሰጠና ወደ ሌላ አገር ሄደ። #25፥15 መክሊት፦ አንድ መክሊት የአንድ የቀን ሠራተኛ የ 15 ዓመት ደመወዝ ነው። 16አምስት መክሊት የተቀበለው ወዲያውኑ ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ። 17ሁለት መክሊት የተቀበለውም እንዲሁ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፈ። 18አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄደና መሬት ቆፍሮ የጌታውን ገንዘብ ቀበረ።
19“ከብዙ ጊዜ በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ መጣና ከአገልጋዮቹ ጋር መተሳሰብ ጀመረ። 20አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ወደ ጌታው መጣና አምስት መክሊት አቅርቦ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ! ሌላ አምስት መክሊት አትርፌአለሁ!’ አለ። 21ጌታውም ‘መልካም አደረግህ፤ አንተ ታማኝና ደግ አገልጋይ! በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ና የጌታህን ደስታ ለመካፈል ግባ!’ አለው። 22ሁለት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ሌላ ሁለት መክሊት አትርፌአለሁ!’ አለ። 23ጌታውም ‘መልካም ነው! አንተ ታማኝና መልካም አገልጋይ በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ና የጌታህን ደስታ ለመካፈል ግባ!’ አለው። 24አንድ መክሊት የተቀበለውም ቀርቦ፥ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ፥ ካልበተንክበት የምትሰበስብ፥ ጨካኝ ሰው መሆንክን ዐውቃለሁ፤ 25ስለዚህ ፈራሁና ሄጄ ገንዘብህን በመሬት ውስጥ ቀበርኩት፤ ይኸውልህ ገንዘብህ!’ አለው። 26ጌታው ግን እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ! ካልዘራሁበት እንደማጭድ ካልበተንኩበት እንደምሰበስብ የምታውቅ ከሆነ፥ 27ገንዘቤን በባንክ ማስቀመጥ ነበረብህ፤ እኔም በመጣሁ ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እወስድ ነበር። 28በሉ ገንዘቡን ተቀበሉና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት። 29ላለው ሰው ሁሉ ይጨመርለታል ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። #ማቴ. 13፥12፤ ማር. 4፥25፤ ሉቃ. 8፥18። 30ይህን የማይረባ አገልጋይ ግን በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።’ #ማቴ. 8፥12፤ 22፥13፤ ሉቃ. 13፥28።
በዓለም መጨረሻ የሚሆነው ፍርድ
31“የሰው ልጅ በመላእክቱ ሁሉ ታጅቦ በክብር ሲመጣ በክብር ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል፤ #ማቴ. 16፥27፤ 19፥28። 32ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ እርሱም ሕዝቦችን እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል። 33ጻድቃንን በቀኙ፥ ኃጢአተኞችን በግራው ያቆማቸዋል። 34በዚያን ጊዜ ንጉሡ በቀኙ በኩል ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ! ኑ! ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ! 35ተርቤ ነበር፥ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ ነበር፥ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ መጣሁ፤ በቤታችሁ ተቀብላችሁኛል፤ 36ታርዤ ነበር፥ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ ነበር፥ ጠይቃችሁኛል፤ ታስሬ ነበር መጥታችሁ ጐብኝታችሁኛል።’ 37በዚያን ጊዜ ጻድቃን እንዲህ ሲሉ ይመልሱለታል፤ ‘ጌታ ሆይ፥ መቼ ተርበህ አየንህና አበላንህ? መቼ ተጠምተህ አየንህና አጠጣንህ? 38መቼ እንግዳ ሆነህ አየንህና በቤታችን ተቀበልንህ? መቼ ታርዘህ አየንህና አለበስንህ? 39መቼ ታመህ ወይም ታስረህ አየንህና መጥተን ጠየቅንህ?’ 40ንጉሡም ‘በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያደረጋችኹት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው!’ ሲል ይመልስላቸዋል። 41ከዚህ በኋላ በግራው በኩል ያሉትንም እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንተ የተረገማችሁ! ከእኔ ወዲያ ራቁ! ለዲያብሎስና ለተከታዮቹ መላእክት ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘለዓለም እሳት ሂዱ! 42ተርቤ ነበር አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ ነበር አላጠጣችሁኝም። 43እንግዳ ሆኜ መጥቼ ነበር፥ አልተቀበላችሁኝም፤ በቤታችሁ ታርዤ ነበር፥ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ ነበር፥ አልጠየቃችሁኝም፤’ 44እነርሱም ‘ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይም ተጠምተህ፥ እንግዳ ሆነህ ወይንም ታርዘህ፥ ታመህ ወይም ታስረህ መቼ አየንህና ሳንረዳህ ቀረን?’ ሲሉ ይመልሱለታል። 45ንጉሡም ‘በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያላደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል። 46ስለዚህ እነዚህ ወደ ዘለዓለም ቅጣት ሲሄዱ፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይሄዳሉ።” #ዳን. 12፥2።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ