የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 11

11
የኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባት
(ማቴ. 21፥1-11ሉቃ. 19፥28-40ዮሐ. 12፥12-19)
1ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረቡ ጊዜ በቤተ ፋጌና በቢታንያ አድርገው ወደ ደብረ ዘይት ደረሱ፤ ከዚያም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፦ 2“በፊታችሁ ወዳለው መንደር ቀድማችሁ ሂዱ፤ እዚያም እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ ማንም ሰው ገና ያልተቀመጠበት የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፍቱትና ወዲህ አምጡት። 3ማንም ሰው ‘ለምን ይህን ታደርጋላችሁ?’ ቢላችሁ፥ ‘ጌታ ስለሚያስፈልገው ነው፤ ወዲያውኑ መልሶ ይልከዋል፤’ በሉት።”
4እነርሱም ሄደው ውርንጫውን በመንገድ ዳር በቤት ደጃፍ ታስሮ አገኙትና ፈቱት። 5በዚያም ጊዜ እዚያ ቆመው ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ፦ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው።
6እነርሱም ኢየሱስ ያላቸውን ነገሩአቸው፤ ሰዎቹም ተዉአቸው። 7ደቀ መዛሙርቱም የአህያውን ውርንጫ ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ ልብሳቸውን በውርንጫው ጀርባ ላይ አድርገው ኢየሱስ ተቀመጠበት። 8ብዙ ሰዎች ሸማቸውን በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፤ ሌሎችም ከዱር የዛፍ ዝንጣፊ እየቈረጡ በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር። 9ከፊት የቀደሙትና ከኋላ የሚከተሉትም ሁሉ፥ “ሆሳዕና! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! #መዝ. 118፥25-26። 10የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሳዕና በአርያም!” እያሉ ይጮኹ ነበር።
11ኢየሱስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያውም ያለውን ነገር ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም መሽቶ ስለ ነበር ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ወደ ቢታንያ ሄደ።
ኢየሱስ የረገማት የበለስ ዛፍ
(ማቴ. 21፥18-19)
12በማግስቱም ከቢታንያ ሲመለሱ ኢየሱስ ተራበ። 13ቅጠልዋ የለመለመ የበለስ ዛፍም በሩቅ አይቶ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ በማለት ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ወደ እርስዋ በቀረበ ጊዜ በለስ የሚያፈራበት ወራት ስላልነበረ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። 14ስለዚህ ኢየሱስ የበለስዋን ዛፍ፥ “ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ!” አላት።
ይህንንም ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ሰሙ።
ኢየሱስ በቤተ መቅደስ የሚገበያዩትን ማስወጣቱ
(ማቴ. 21፥12-17ሉቃ. 19፥45-48ዮሐ. 2፥13-22)
15ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በውስጡ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ያስወጣ ጀመር፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ 16ማንም ሰው ምንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ እንዲተላለፍ አልፈቀደም። 17እንዲህም ሲል አስተማራቸው፤ “ ‘ቤቴ ለሕዝብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል!’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት።” #ኢሳ. 56፥7፤ ኤር. 7፥11።
18የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ይህን ሲናገር ሰሙት፤ ሕዝቡም ሁሉ በትምህርቱ ይደነቁ ስለ ነበር ፈሩት፤ ስለዚህ እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ዘዴ ይፈልጉ ነበር።
19በመሸም ጊዜ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከከተማ ወጡ።
ከበለሲቱ ዛፍ የተገኘ ትምህርት
(ማቴ. 21፥20-22)
20በማግስቱ ማለዳ በመንገድ ሲያልፉ የበለሲቱ ዛፍ ከነስርዋ ደርቃ አዩአት። 21ጴጥሮስም ነገሩ ትዝ ብሎት ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ! እነሆ፥ የረገምሃት ዛፍ ደርቃለች” አለው።
22ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ 23በእውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ሰው በልቡ ሳይጠራጠር የሚፈልገው ነገር እንደሚፈጸምለት አምኖ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር፤’ ቢል ይሆንለታል። #ማቴ. 17፥20፤ 1ቆሮ. 13፥2። 24ስለዚህ በጸሎት ማናቸውንም ነገር ብትለምኑ፥ እንደ ተፈጸመላችሁ አድርጋችሁ እመኑ፤ የምትለምኑትም ሁሉ ይሰጣችኋል። 25በሰማይ ያለው አባታችሁ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲልላችሁ እናንተም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ ሰው በአንዳች ነገር አስቀይሞአችሁ ከሆነ ይቅርታ አድርጉለት። #ማቴ. 6፥14-15። 26እናንተ የሌሎችን በደል ይቅር ባትሉ ግን በሰማይ ያለው አባታችሁ የእናንተንም ኃጢአት ይቅር አይልላችሁም።” #11፥26 አንዳንድ የብራና ጽሑፎች ቊ. 26 ይጨምራሉ፤ ቃሉም በማቴ 6፥15 ያለውን ይመስላል።
ኢየሱስ በምን ሥልጣን እንደሚሠራ የቀረበ ጥያቄ
(ማቴ. 21፥23-27ሉቃ. 20፥1-8)
27እንደገናም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲዘዋወር ሳለ የካህናት አለቆች፥ የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጡና 28“እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ወይስ እነዚህን ነገሮች እንድታደርግ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።
29ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተ መልስ ከሰጣችሁኝ፥ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። 30የዮሐንስ ጥምቀት ከእግዚአብሔር ነበረ ወይስ ከሰው? እስቲ መልሱልኝ፤” አላቸው።
31እነርሱም “እንግዲህ ምን እንበል?” በማለት እርስ በርሳቸው ተመካከሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው፥’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ 32‘ከሰው ነው፥’ ብንልሳ?” ይህን እንዳይሉ ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን በእርግጥ ነቢይ ነው ይሉ ስለ ነበር ፈሩ። 33ስለዚህ “እኛ አናውቅም።” ሲሉ መለሱለት።
ኢየሱስም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም፤” አላቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ