የማርቆስ ወንጌል 14
14
በኢየሱስ ላይ የተደረገ ሤራ
(ማቴ. 26፥1-5፤ ሉቃ. 22፥1-2፤ ዮሐ. 11፥45-53)
1የአይሁድ የፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ቀርቶት ነበር፤ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስን በተንኰል ይዘው የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። #ዘፀ. 12፥1-7። 2ነገር ግን ሕዝቡ ሁከት ያነሣሣል በማለት “በበዓል ቀን ይህን አናደርግም፤” አሉ።
ኢየሱስን ሽቶ የቀባች ሴት
(ማቴ. 26፥6-13፤ ዮሐ. 12፥1-8)
3ኢየሱስ በቢታንያ ለምጻም በነበረው በስምዖን ቤት ነበር። በገበታም ቀርቦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነና የከበረ የናርዶስ ሽቶ የሞላበት፥ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች፤ ብልቃጡን ሰብራ ሽቶውን በኢየሱስ ራስ ላይ አፈሰሰችው። #ሉቃ. 7፥37-38። 4እዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው፦ “ይህ ሽቶ በከንቱ መባከኑ ለምንድን ነው? 5ይህ ሽቶ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ ገንዘቡ ለድኾች ሊሰጥ ይቻል ነበር!” ተባባሉ፤ ሴቲቱንም ነቀፉአት። #14፥5 ዲናር፦ አንድ ዲናር የአንድ የቀን ሠራተኛ የቀን ደመወዝ ነው።
6ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፦ “ተዉአት! ስለምን ታስቸግሩአታላችሁ? እርስዋ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች፤ 7ድኾች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ስለ ሆኑ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዱአቸው ትችላላችሁ፤ እኔን ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አታገኙኝም፤ #ዘዳ. 15፥11። 8ይህች ሴት የተቻላትን አድርጋለች፤ ሥጋዬም ከመቀበሩ በፊት አስቀድማ ለማዘጋጀት ሽቶ ቀባችው። 9በእውነት እላችኋለሁ፤ በዓለም ሁሉ ይህ ወንጌል በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ ይህ እርስዋ ያደረገችው ለመታሰቢያ ይነገርላታል።”
ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት መስማማቱ
(ማቴ. 26፥14-16፤ ሉቃ. 22፥3-6)
10ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ አስቆሮታዊው ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። 11እነርሱም ይህን ባወቁ ጊዜ ደስ አላቸው፤ ገንዘብም ሊሰጡት ቃል ገቡለት። እርሱም ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር።
ኢየሱስ የአይሁድን የፋሲካ ራት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ በላ
(ማቴ. 26፥17-25፤ ሉቃ. 22፥7-14፤21-23፤ ዮሐ. 13፥21-30)
12የፋሲካውን በግ በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን፥ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “የፋሲካን ራት ለመብላት ወዴት ሄደን እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት።
13እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እዚያም የውሃ እንሥራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከተሉት፤ 14ወደሚገባበትም ቤት ሂዱና የቤቱን ጌታ፥ ‘መምህር፥ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት ለእኔ የሚሆን የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው?’ ይላል በሉት። 15እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን የተዘጋጀውንና የተነጠፈውን ትልቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።”
16ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከዚያ ወጥተው ወደ ከተማው ሄዱ፤ ልክ ኢየሱስ እንዳላቸውም አገኙ፤ የፋሲካንም ራት በዚያ አዘጋጁ።
17በመሸ ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ፤ 18በገበታ ቀርበው ሲበሉ ኢየሱስ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል፤ እርሱም አሁን ከእኔ ጋር ራት በመብላት ላይ የሚገኘው ነው፤” አለ። #መዝ. 41፥9።
19እነርሱም በዚህ ነገር አዝነው “እኔ እሆንን?” እያሉ ተራ በተራ ጠየቁት።
20ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ያ ሰው ከዐሥራ ሁለታችሁ አንዱ የሆነው አሁን ከእኔ ጋር በዚህ ሳሕን ውስጥ ወጥ የሚያጠቅሰው ነው፤ 21የሰው ልጅ አስቀድሞ ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ወደ ሞት መሄዱ አይቀርም፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት! ያ ሰውስ ቀድሞውኑ ባይወለድ ይሻለው ነበር!”
የቅዱስ ቊርባን ሥርዓት
(ማቴ. 26፥26-30፤ ሉቃ. 22፥14-20፤ 1ቆሮ. 11፥23-25)
22እነርሱ በመብላት ላይ ሳሉ ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፥ ይህ ሥጋዬ ነው” ብሎ ሰጣቸው።
23ጽዋውንም አንሥቶ የምስጋና ጸሎት ካደረገ በኋላ ሰጣቸው፤ ሁሉም ከጽዋው ጠጡ። 24እንዲህም አላቸው፦ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የቃል ኪዳን ደሜ ነው፤ #ዘፀ. 24፥8፤ ኤር. 31፥31-34። 25በእውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ከአዲሱ ወይን እስክጠጣ ድረስ ከዚህ ወይን ፍሬ ጭማቂ ዳግመኛ አልጠጣም።”
26ከዚያም በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።
ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ እንደ ተናገረ
(ማቴ. 26፥31-35፤ ሉቃ. 22፥31-34፤ ዮሐ. 13፥36-38)
27ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ ‘እረኛውን መትቼ እገድላለሁ፤ በጎቹም ይበተናሉ፤’ ተብሎ ተጽፎአልና ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ፤ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ትታችሁኝም ትሸሻላችሁ፤ #ዘካ. 13፥7። 28ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” #ማቴ. 28፥16።
29በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ፥ እኔ ከቶ አልክድህም!” አለው።
30ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው።
31ጴጥሮስ ግን “መሞት እንኳ ቢያስፈልግ ከአንተ ጋር እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” እያለ አጠንክሮ ተናገረ።
የቀሩትም ደቀ መዛሙርት እንዲሁ ይሉ ነበር።
ኢየሱስ በጌቴሴማኒ እንደ ጸለየ
(ማቴ. 26፥36-46፤ ሉቃ. 22፥39-46)
32ከዚህም በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ፤” አላቸው። 33ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም አስከትሎ ሄደ፤ እዚያም እጅግ ያዝንና ይጨነቅ ጀመረ። 34እንዲህም አላቸው፦ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ አዝናለች፤ እዚህ ቈዩ፤ ተግታችሁም ጠብቁ።” 35ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደ፤ በመሬትም ላይ በግንባሩ ተደፍቶ የሚቻል ቢሆን ያቺ ሰዓት እንድታልፍለት ጸለየ። 36እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፥ ሁሉ ነገር ይቻልሃል፤ ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ ፈቃድ አይሁን።”
37ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ ጴጥሮስን፦ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት እንኳ ልትነቃ አልቻልክምን?” አለው። 38“ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አላቸው።
39እንደገናም ሄዶ፥ ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ጸለየ። 40ደግሞም ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር፥ ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር።
41ሦስተኛም ጊዜ ወደ እነርሱ መጥቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? አሁንም ዕረፍት ታደርጋላችሁን? እንግዲህስ በቃ! ሰዓቱ ደርሶአል! እነሆ! የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። 42በሉ ተነሡ! እንሂድ! አሳልፎ የሚሰጠኝ ይኸው ቀርቦአል!”
የኢየሱስ ተላልፎ መሰጠትና መያዝ
(ማቴ. 26፥47-56፤ ሉቃ. 22፥47-53፤ ዮሐ. 18፥3-12)
43ወዲያውም ኢየሱስ ይህን ሲናገር ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ሰይፍና ዱላ የያዙ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱ ከካህናት አለቆች፥ ከሕግ መምህራን፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ የተላኩ ነበሩ። 44አሳልፎ የሚሰጠውም ይሁዳ፥ “እናንተ የምትይዙት እኔ ሰላምታ ሰጥቼ የምስመውን ነው፤ እርሱን በጥንቃቄ ይዛችሁ ውሰዱት፤” ሲል ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።
45ይሁዳ ወዲያውኑ መጥቶ ወደ ኢየሱስ ቀረበና “መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው። 46ከዚህ በኋላ ሰዎቹ ኢየሱስን ያዙት። 47እዚያ ቆመው ከነበሩት ከኢየሱስ ተከታዮች አንዱ ሰይፉን መዝዞ የካህናት አለቃውን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ። 48ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይፍና ዱላ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን እንደ ወንበዴ ለመያዝ ነውን? 49በየቀኑ በቤተ መቅደስ እያስተማርኩ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም ነበር፤ ነገር ግን ይህ የሆነው የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል እንዲፈጸም ነው።” #ሉቃ. 19፥47፤ 21፥37።
50ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ትተውት ሸሹ።
51የበፍታ ነጠላ ብቻ የለበሰ አንድ ወጣት ግን ኢየሱስን ይከተል ነበር፤ ሰዎቹም በያዙት ጊዜ 52ነጠላውን ጥሎ ራቁቱን ሸሽቶ አመለጠ።
ኢየሱስ ወደ ፍርድ ሸንጎ መወሰዱ
(ማቴ. 26፥57-68፤ ሉቃ. 22፥54-55፤63-71፤ ዮሐ. 18፥13-14፤19-24)
53ኢየሱስን ግን ወደ ካህናት አለቃው ቤት ወሰዱት፤ እዚያ የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና የሕግ መምህራን ሁሉ ተሰበሰቡ። 54ጴጥሮስም እስከ የካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ይከተለው ነበር። እዚያም ከሎሌዎች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። 55የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች ሁሉ፥ ኢየሱስን ለማስገደል ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ግን አላገኙም። 56ብዙዎችም በሐሰት መስክረውበት ነበር፤ ሆኖም የምስክርነት ቃላቸው ሳይስማማ ቀረ።
57አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ 58“እኔ ይህን በሰው እጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ ሌላ በሰው እጅ ያልተሠራ እሠራለሁ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል።” #ዮሐ. 2፥19። 59ይህም ሆኖ ምስክርነታቸው አልተስማማም።
60የካህናት አለቃውም በመካከላቸው ቆሞ፥ “ምንም አትመልስምን? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ የሚያቀርቡብህ ክስ ምንድን ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው።
61ኢየሱስ ግን ዝም አለ እንጂ ምንም መልስ አልሰጠም። የካህናት አለቃውም “የቡሩክ እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ አንተ ነህን?” ሲል እንደገና ጠየቀው።
62ኢየሱስም “አዎ፥ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታያላችሁ! እንዲሁም በሰማይ ደመና ተመልሶ ሲመጣ ታያላችሁ” አለ። #ዳን. 7፥13። 63የካህናት አለቃውም በቊጣ ልብሱን ቀደደና “ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? 64እነሆ! ይህን የስድብ ቃል በእግዚአብሔር ላይ ሲሰነዝር ሰምታችኋል፤ ታዲያ ምን ይመስላችኋል?” አለ።
ሁሉም በአንድ ቃል፥ “ሞት ይገባዋል!” ብለው ፈረዱበት። #ዘሌ. 24፥16።
65አንዳንዶችም ምራቃቸውን እንትፍ ይሉበት ጀመር፤ ዐይኑንም በጨርቅ ሸፍነው “አንተ ነቢይ ከሆንክ እስቲ ማን እንደ መታህ ዕወቅ!” እያሉ በቡጢ ይመቱት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።
ጴጥሮስ ኢየሱስን መካዱ
(ማቴ. 26፥69-75፤ ሉቃ. 22፥56-62፤ ዮሐ. 18፥15-18፤25-27)
66ጴጥሮስ ከካህናት አለቃው ቤት በታች በግቢው ውስጥ እንዳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንድዋ መጣች፤ 67እርስዋ ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኲር ብላ ተመለከተችውና “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርክ፤” አለችው።
68እርሱ ግን “እኔ አላውቅም፤ አንቺ የምትዪውም አይገባኝም፤” ሲል ካደ። ይህንንም ብሎ ወደ ደጃፉ እንደ ወጣ ዶሮ ጮኸ።
69ገረዲትዋም ጴጥሮስን አይታ፥ በዚያ ለቆሙት “ይህም ከእነርሱ ወገን ነው!” ስትል እንደገና ትናገር ጀመር፤ 70እርሱ ግን እንደገና ካደ። ጥቂት ቈየት ብሎም በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፥ “የገሊላ ሰው መሆንህን በእርግጥ አነጋገርህ ያስረዳል፤ ስለዚህ በእርግጥ አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤” አሉት።
71እርሱ ግን “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም!” እያለ ራሱን መራገምና መማል ጀመረ።
72ወዲያውኑ ዶሮ ሁለተኛ ጊዜ ጮኸ፤ ጴጥሮስም “ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል ትዝ አለውና ምርር ብሎ አለቀሰ።
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 14: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997