ኦሪት ዘኊልቊ 11
11
ታብዔራ
1እስራኤላውያን ስለ ደረሰባቸው ችግር ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ማጒረምረም ጀመሩ፤ እግዚአብሔርም የማጒረምረም ጩኸታቸውን ሰምቶ እጅግ በመቈጣት የሚባላ እሳት ላከባቸው፤ ያም እሳት ከሰፈሩ አንዱን ክፍል አወደመ። 2ሕዝቡም ያማልዳቸው ዘንድ ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እሳቱም ተገታ። 3የእግዚአብሔር እሳት በዚያ ስፍራ በመካከላቸው ስለ ነደደ ያ ስፍራ “ታብዔራ” ተብሎ ተጠራ።
ሙሴ ሰባ የሕዝብ አለቆችን ለመሪነት መምረጡ
4ከእስራኤላውያን ጋር የሚጓዙ የውጪ አገር ሰዎች ሥጋ ለመብላት የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነበር፤ እስራኤላውያንም እንዲህ እያሉ ማልቀስ ጀመሩ፦ “የምንበላውን ሥጋ ከየት እናገኛለን! 5በግብጽ ሳለን ምንም ዋጋ ሳንከፍል የፈለግነውን ያኽል ዓሣ እንበላ እንደ ነበረ እናስታውሳለን፤ በዚያ ሳለን እንበላ የነበረውን ዱባ፥ (ኪያር) ሀብሀብ (በጢኽ)፥ ኲራት (ድንች መሳይ ምግብ) ቀዩንና ነጩን ሽንኩርት፥ #11፥5 ታብዔራ፦ በዕብራይስጥ “የእሳት ቃጠሎ” ማለት ነው። 6አሁን ግን ሰውነታችን ደርቆ ኀይላችን ደከመ፤ የምንመገበው ምንም ነገር የለም፤ በየቀኑ ከዚህ መና በቀር ሌላ የምናየው የለም።”
7መና እንደ ድንብላል ዘር ትንንሽ ሆኖ እንደ ሙጫ ነጣ ያለ ቢጫ መልክ ነበረው፤ 8ሰዎቹም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፤ በወፍጮም ይፈጩት ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ያፈሉትና ይጋግሩት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ ቂጣ ነበር፤ #ዘፀ. 16፥31። 9ሌሊት ጠል በሰፈሩ ላይ በሚወርድበት ጊዜ መናውም አብሮት ይወርድ ነበር። #ዘፀ. 16፥13-15።
10ሕዝቡ ሁሉ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ በየቤተሰባቸው ቆመው ሲያለቅሱ ሙሴ ሰማቸው፤ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቈጥቶ ስለ ነበረ ሙሴ በጣም ተጨነቀ። 11እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ “ይህን ከባድ ነገር በእኔ በአገልጋይህ ላይ ስለምን አመጣህብኝ? ለምንስ በፊትህ ሞገስን አላገኘሁም? የዚህን ሁሉ ሕዝብስ ከባድ ኀላፊነት ለምን በእኔ ላይ ጫንከው? 12ጡት የሚጠባውን ሕፃን አንዲት ሞግዚት እንደምትታቀፈው እኔም እነርሱን ታቅፌ አንተ ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባህላቸው ምድር እንዳደርሳቸው የምታደርገኝ እነዚህን ሰዎች እኔ ፀነስኳቸውን? ወይስ እኔ ወለድኳቸውን? 13የምንበላውን ሥጋ ስጠን እያሉ ወደ እኔ መጥተው ስለሚያለቅሱ ለእነዚህ ሰዎች ሁሉ የሚሆን ሥጋ ከወዴት አመጣለሁ? 14እኔ ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን መምራት አልችልም፤ ይህ ኀላፊነት ለእኔ እጅግ ከባድ ነው፤ 15በዚህ ሁኔታ እንድሠቃይ ከምታደርገኝ ይልቅ መከራ እንዳላይ ብትራራልኝና አሁኑኑ ብትገድለኝ ይሻላል።”
የሰባ ሽማግሌዎች መመረጥ
16እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለሕዝብ አመራር በመስጠት የታወቁ ሰባ ሽማግሌዎችን ምረጥ፤ እነርሱንም ሰብስበህ ወደ መገናኛው ድንኳን አምጣቸውና በአጠገብህ ይቁሙ፤ 17እኔም ወደዚያ ወርጄ ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፤ ለአንተም ከሰጠሁህ መንፈስ ከፍዬ ለእነርሱ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእነዚህ ሕዝብ ላይ ያለህን ኀላፊነት በመሸከም ይረዱሃል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ይህን ሁሉ ኀላፊነት ብቻህን አትሸከምም። 18አሁንም ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ለነገ ራሳችሁን አንጹ፤ የምትበሉትም ሥጋ ይኖራችኋል፤ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል ብላችሁ ማልቀሳችሁንና የግብጽ ምድር ይሻለን ነበር ማለታችሁን እግዚአብሔር ሰምቶአል፤ እነሆ፥ አሁን እግዚአብሔር ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እርሱንም ትበላላችሁ። 19የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ለአምስት፥ ለዐሥር ወይም ለኻያ ቀን ብቻ አይደለም፤ 20እስኪያንገፈግፋችሁና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ ድረስ አንድ ወር ሙሉ ትመገቡታላችሁ፤ ይህም የሚሆነው እዚህ በመካከላችሁ ያለውን ጌታ ስለ ናቃችሁና፦ ከግብጽ ባልወጣን ኖሮ መልካም ነበር በማለት ስላለቀሳችሁ ነው።’ ”
21ሙሴም ለእግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ እኔ ስድስት መቶ ሺህ ሕዝብ በመምራት ላይ እገኛለሁ፤ ለአንድ ወር የሚበቃ ሥጋ ልትሰጣቸው ቃል ገብተሃል፤ 22ታዲያ ምን ያኽል የከብትና የበግ መንጋ ቢታረድ እነርሱን ሊያጠግብ ይችላል? በባሕር ውስጥ ያለው ዓሣ ሁሉ ቢሰበሰብ ለእነርሱ በቂ ሊሆን ይችላልን?”
23እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የእኔ የእግዚአብሔር ኀይል ውሱን ነውን? ቃሌ በእናንተ ዘንድ የሚፈጸም ወይም የማይፈጸም መሆኑን አሁን ታያለህ!”
24ስለዚህ ሙሴ ወጥቶ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ከሕዝቡ መሪዎች ሰባውን በአንድነት ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። 25እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ተናገረው፤ ለሙሴ ከሰጠው መንፈስ ከፊሉን ወስዶ በሰባዎቹ መሪዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈስ በወረደባቸውም ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ፤ ይህን ያደረጉት ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነበር።
26ከተመዘገቡት ከሰባው መሪዎች መካከል ሁለቱ ኤልዳድና ሜዳድ የተባሉት ወደ ድንኳኑ ሳይሄዱ በሰፈር ቈይተው ነበር፤ እዚያው በሰፈር እንዳሉ መንፈስ ወረደባቸውና እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ። 27አንድ ወጣት ወደ ሙሴ ሲሮጥ ሄዶ “ኤልዳድና ሜዳድ በሰፈር ውስጥ ትንቢት እየተናገሩ ናቸው” ሲል ነገረው።
28ከጐልማሳነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ! ከልክላቸው!” አለው።
29ሙሴም “አንተ ስለ እኔ ትቈረቈራለህን? እኔስ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሁሉ ላይ መንፈሱን ቢያወርድና ሁሉም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ቢናገሩ ደስታዬ ነው!” አለው። 30ሙሴና ሰባዎቹ የእስራኤል መሪዎችም ወደ ሰፈር ተመለሱ።
እግዚአብሔር ድርጭቶችን እንደ ሰጠ
31በድንገትም እግዚአብሔር ድርጭቶችን ከባሕር እየነዳ የሚያመጣ ነፋስ ላከ፤ ድርጭቶችም ከምድር አንድ ሜትር ያኽል ከፍ ብለው እየበረሩ መጡ፤ በሰፈሩና በሰፈሩ ዙሪያ የተከማቹበት ስፍራ የአንድ ቀን መንገድ ያኽል ነው፤ 32ስለዚህ በዚያን ቀንና ሌሊት፥ እንዲሁም በማግስቱ ሕዝቡ ድርጭት እያሳደዱ በመያዝ ደከሙ፤ ከዐሥር ኪሎ ግራም ያነሰ የሰበሰበ አልነበረም፤ እንዲደርቁም በሰፈር ዙሪያ አሰጡአቸው። 33የሚበሉት ሥጋ ገና በብዛት ሳለ፥ እግዚአብሔር በሕዝቡ እጅግ ተቈጣ፤ ብርቱ መቅሠፍትም በሕዝቡ መካከል አመጣ፤ 34በሥጋ አምሮት የሞቱትን ሕዝብ እዚያ ቀብረዋቸው ስለ ነበር የዚያ ስፍራ ስም “የምኞት መቃብር” ተባለ፤
35ከዚያም ሕዝቡ ወደ ሐጼሮት ተጒዘው በዚያ ሰፈሩ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997