ኦሪት ዘኊልቊ 16
16
ቆሬ፥ ዳታንና አቤሮን የፈጸሙት ዐመፅ
1ከሌዊ ነገድ የሆነው የቀዓት ጐሣ የይስዓር ልጅ ቆሬ፥ ከሮቤል ነገድ የሆኑት የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን፥ የፋሌትም ልጅ ኦን ዐመፁ፤ #ይሁዳ 11። 2ከእነርሱም ጋር በእስራኤላውያን ዘንድ ዝናቸው የታወቀና ለሕዝብ መሪነት የተመረጡ ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎችን ወስደው በሙሴ ላይ ተነሡ፤ 3እነርሱም በሙሴና በአሮን ፊት ተሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ “እናንተ ከልክ አልፋችኋል! የዚህ ጉባኤ አባላት የሆኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለዩ ናቸው፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ሁሉ ጋር ነው፤ ታዲያ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይ ራሳችሁን ከፍ ከፍ የምታደርጉት ስለምንድን ነው?”
4ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ በግንባሩ ወድቆ ጸለየ፤ 5ቆሬንና ተከታዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “ነገ ጠዋት እግዚአብሔር ለእርሱ የተለየ ማን እንደ ሆነ ለይቶ ያሳየናል፤ ይኸውም የእርሱ የሆነውንና የመረጠውን በመሠዊያው ላይ ያገለግለው ዘንድ ወደ እርሱ እንዲቀርብ ይፈቅድለታል። 6ነገ ጠዋት አንተና ተባባሪዎችህ ሁሉ ጥናዎችን ይዛችሁ ኑ! 7በእነርሱም ላይ የከሰል ፍምና ዕጣን አድርጋችሁ ወደ መሠዊያው አቅርቡአቸው፤ ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ማንኛችንን መርጦ ለራሱ እንደ ለየ እናያለን፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ሌዋውያኑ ናችሁ።”
8ሙሴ ከቆሬ ጋር መነጋገሩን እንዲህ ሲል ቀጠለ፦ “እናንተ ሌዋውያን አድምጡ! 9ወደ እርሱ ቀርባችሁ በማደሪያው ድንኳን አገልግሎታችሁን እንድትፈጽሙና በፊታቸውም ቆማችሁ የእስራኤልን ጉባኤ እንድታገለግሉ የእስራኤል አምላክ ከሌላው የእስራኤል ማኅበር መካከል መርጦ እናንተ የተለያችሁ እንድትሆኑ ማድረጉን እንደ ቀላል ነገር ታዩታላችሁን? 10እርሱ እናንተና ሌሎቹም ሌዋውያን ይህ ክብር እንዲኖራችሁ አድርጎአል፤ አሁን ደግሞ የካህናቱን ቦታ ለመያዝ ፈልጋችኋል፤ 11ስለዚህ አንተና ተባባሪዎችህ የተሰበሰባችሁት በእግዚአብሔር ላይ ነው፤ በአሮን ላይ የምታጒረመርሙት እርሱ ማን ነው?”
12ከዚህ በኋላ ሙሴ የኤልያብ ልጆች የሆኑትን ዳታንንና አቤሮንን ልኮ አስጠራ፤ እነርሱ ግን “አንመጣም!” አሉ። 13“በምድረ በዳ እንድንሞት በማርና በወተት ከበለጸገችው ምድር ያስወጣኸን አንሶ አሁን ደግሞ በእኛ ላይ አለቃ ልትሆን ትፈልጋለህን? 14ለም ወደሆነችው ምድር እንዳላመጣኸን ወይም የእርሻና የወይን ተክል ቦታ እንዳላወረስከን የተረጋገጠ ነው፤ አሁን ደግሞ ልታታልለን ትፈልጋለህ፤ እንግዲህስ ወደ አንተ አንመጣም!”
15ሙሴም እጅግ ተቈጥቶ እግዚአብሔርን እንዲህ አለ፦ “እነዚህ ሰዎች የሚያቀርቡልህን መባ አትቀበል፤ እኔ ከእነርሱ አንዱን እንኳ አልበደልኩም፤ ሌላው ቀርቶ ከአህዮቻቸው አንዱን እንኳ አልወሰድኩም።”
16ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፦ “ነገ አንተና ሁለት መቶ ኀምሳ ተባባሪዎችህ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን እንድትመጡ፤ አሮንም እዚያው ይገኛል። 17እያንዳንዳችሁ ጥናችሁን ይዛችሁ ኑ፤ በውስጡም ዕጣን ጨምሩበት፤ ከሁለት መቶ ኀምሳ ጥናዎች ጋር ወደ እግዚአብሔር ፊት ዕጣናችሁን ታቀርባላችሁ፤ አንተና አሮንም ዕጣናችሁን ታቀርባላችሁ።” 18ስለዚህም እያንዳንዳቸው ጥናቸውን ይዘው የእሳት ፍምና ዕጣን በመጨመር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሙሴና ከአሮን ጋር ቆሙ፤ 19ከዚያም በኋላ ቆሬ መላውን ማኅበር በአንድነት ሰበሰበ፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ መጥተው በሙሴና በአሮን ፊት ለፊት ቆሙ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለመላው ማኅበር በድንገት ታየ። 20እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 21“ከእነዚህ ሕዝብ ራቅ ብላችሁ ቁሙ፤ እኔም እነርሱን በአንድ ጊዜ እደመስሳቸዋለሁ።” 22ሙሴና አሮን በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው እንዲህ አሉ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነህ፤ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ በመላው ማኅበር ላይ ትቈጣለህን?” 23-24እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “ከቆሬ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች እንዲርቁ ለሕዝቡ ንገር” አለው።
25ከዚህ በኋላ ሙሴ የእስራኤልን መሪዎች አስከትሎ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤ 26ሕዝቡንም እንዲህ አለ፦ “ከእነዚህ ዐመፀኞች ሰዎች ድንኳኖች ርቃችሁ ቁሙ፤ የእነርሱ ንብረት የሆነውን ማናቸውንም ዕቃ አትንኩ፤ አለበለዚያ በእነርሱ ኃጢአት ምክንያት ሁላችሁም ከእነርሱ ጋር ተጠራርጋችሁ ትጠፋላችሁ።” 27ስለዚህ ሕዝቡ ከቆሬ፥ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች ፈቀቅ አሉ።
ዳታንና አቤሮንም ወጥተው ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በድንኳናቸው ደጃፍ ቆመው ነበር። 28በዚያን ጊዜ ሙሴ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “ይህን ሁሉ ሥራ እንዳከናውን እግዚአብሔር እኔን የላከኝ መሆኑን የምታውቁትና እኔ ይህን ሁሉ ሥራ የማከናውነው በራሴ ፈቃድ እንዳልሆነ የምትገነዘቡት በዚህ ነው፤ 29እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ቅጣት ሳይደርስባቸው እንደማንኛውም ሰው ከሞቱ፥ እኔን እግዚአብሔር አላከኝም፤ 30ነገር ግን እግዚአብሔር ተሰምቶ የማይታወቅ አዲስ ነገር በመፍጠር በሕይወታቸው ሳሉ ወደ ሙታን ዓለም ይወርዱ ዘንድ ምድር ተከፍታ እነርሱንና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ ብትውጥ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን የተቃወሙ መሆናቸውን ታውቃላችሁ።”
31ሙሴ ይህን ተናግሮ እንዳበቃ፥ ዳታንና አቤሮን የቆሙበት ምድር ተከፍታ 32እነርሱንና ቤተሰቦቻቸውን፥ የቆሬን ተከታዮችና ያላቸውን ንብረት ሁሉ ዋጠች። 33ስለዚህ በሕይወት ሳሉ ከነንብረታቸው ወደ ሙታን ዓለም ወረዱ፤ ምድርም በላያቸው ተከድና ጠፉ። 34በዚያ የነበሩት የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የእነዚያን ሰዎች ጩኸት በሰሙ ጊዜ ሸሹ፤ “ምድር እኛንም ልትውጠን ስለምትችል እንሩጥ!” እያሉም ጮኹ።
35ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር እሳት ልኮ ዕጣን ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎች አቃጠለ።
36ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 37“የአሮን ልጅ አልዓዛር ከነሐስ የተሠሩትን ጥናዎች ከተቃጠሉት ሰዎች ዘንድ እንዲወስድና ጥናዎቹ የተቀደሱ ስለ ሆኑ በውስጣቸው ያለውን ፍም ወደ ሌላ ስፍራ እንዲያፈስ ንገረው፤ 38ጥናዎቹም የተቀደሱት ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ በቀረቡ ጊዜ ነው፤ ስለዚህ በኃጢአታቸው የተገደሉትን የእነዚህን ሰዎች ጥናዎች ውሰድና በመቀጥቀጥ እንዲሳሱ አድርግ፤ ለመሠዊያውም መክደኛ እንዲሆኑ አድርገህ ሥራቸው፤ ለእስራኤል ሕዝብ የመቀጣጫ ማስጠንቀቂያ ይሆናል።”
39ስለዚህ አልዓዛር ጥናዎቹን ወስዶ ለመሠዊያው ክዳን ይሆኑ ዘንድ በስሱ ቀጠቀጣቸው። 40ይህም ሁኔታ የአሮን ዘር ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ዕጣን ያጥን ዘንድ ወደ መሠዊያው መቅረብ እንደማይገባው ለእስራኤላውያን ሁሉ ማስጠንቀቂያ ይሆናል፤ ይህ ካልሆነ ግን እንዲህ የሚያደርግ ሰው ሁሉ እንደ ቆሬና እንደ ተከታዮቹ ይጠፋል፤ ይህም ሁሉ የተፈጸመው እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነበር።
አሮን ሕዝቡን ማዳኑ
41በማግስቱ መላው የእስራኤል ማኅበር “የእግዚአብሔር ወገኖች የሆኑትን ሕዝብ ገድላችኋል” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ አጒረመረሙ። 42ሙሴንና አሮንን ለመቃወም ሁሉም በአንድነት ከተሰበሰቡ በኋላ ወደ መገናኛው ድንኳን ዞር ብለው ሲመለከቱ ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፍኖት የእግዚአብሔር ክብር ተገለጠ። 43ሙሴና አሮንም መጥተው በመገናኛው በድንኳን ፊት ለፊት ቆሙ። 44እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 45“ከእነዚህ ሰዎች ርቃችሁ ቁሙ፤ እኔ እነርሱን በአንድ ጊዜ እደመስሳቸዋለሁ!”
ሁለቱም በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፉ፤ 46ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፦ “የአንተን ጥና ወስደህ ከመሠዊያው የእሳት ፍም ጨምርበት፤ በፍሙም ላይ ዕጣን አድርግበት፤ ከዚያም ወደ ሕዝቡ በፍጥነት በመሄድ አስተስርይላቸው፤ ፍጠን! እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቊጣ ከመገለጡ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መቅሠፍት ጀምሮአል።” 47አሮንም በመታዘዝ ጥናውን ይዞ ወደ ተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ፈጥኖ ሄደ፤ መቅሠፍቱ እንደ ጀመረ በተመለከተ ጊዜ ዕጣኑን በፍሙ ላይ አድርጎ ለሕዝቡ አስተሰረየላቸው፤ 48በዚህም መቅሠፍቱ እንዲቆም አደረገ፤ አሮንም በሞቱትና በሕይወት ባሉት መካከል ቆሞ ነበር። 49በዚያን ጊዜ የሞቱት ሰዎች ቊጥር ከቆሬ ጋር ዐምፀው ያለቁትን ሳይጨምር ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበር፤ 50ቸነፈሩም በቆመ ጊዜ አሮን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደነበረው ወደ ሙሴ ተመለሰ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 16: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997