የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 19

19
ኃጢአትን ለማስተስረይ የሚፈጸም ሥርዓት
1እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2“ይህ እኔ ያዘዝኩት የሕጉ ሥርዓት ነው፦ ነውር የሌለባትና በጫንቃዋ ላይ ቀንበር ተጭኖባት የማታውቅ አንዲት ቀይ ጊደር እንዲያመጡ ለእስራኤላውያን ንገሩአቸው። 3ጊደርዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ስጡት፤ ከሰፈርም ወጥታ በእርሱ ፊት ትታረድ፤ 4ካህኑ አልዓዛርም ከደሙ ጥቂቱን ወስዶ በጣቱ እያጠቀሰ ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው፤ 5እንስሳዪቱ በሙሉ ማለትም ቆዳዋ፥ ሥጋዋ፥ ደምዋና የሆድ ዕቃዋ ሁሉ በካህኑ ፊት ይቃጠል፤ 6ካህኑ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት፥ የሂሶጵ ቅርንጫፍና ቀይ ክር ወስዶ ጊደርዋ በምትቃጠልበት በእሳት ውስጥ ይጣለው፤ 7ከዚህ በኋላ ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም በውሃ ይታጠብና ወደ ሰፈሩ ይመለስ፤ ነገር ግን ያልነጻ ሆኖ እስከ ማታ ድረስ ይቈይ፤ 8ጊደርዋን ያቃጠለውም ሰው ልብሱን አጥቦ ገላውንም በውሃ ይታጠብ፤ እርሱም እስከ ማታ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል። 9ከዚህ በኋላ ንጹሕ የሆነ ሌላ ሰው የጊደርዋን ዐመድ ሰብስቦ በመውሰድ ከሰፈሩ ውጪ ንጹሕ በሆነ ቦታ ያስቀምጠዋል፤ እዚያም ለእስራኤላውያን ጉባኤ ርኲሰትን ለማንጻት የሚያገለግለውን ውሃ ለማዘጋጀት የሚጠቅም ይሆናል፤ ይህም ሥርዓት የሚፈጸመው ኃጢአትን ለማስወገድ ነው። #ዕብ. 9፥13። 10ዐመዱን የሰበሰበው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ነገር ግን እስከ ማታ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤ ይህ የሥርዓት መመሪያ ለእስራኤላውያንና በመካከላቸው ለሚኖሩ መጻተኞች ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ የጸና ሕግ ሆኖ ይኖራል።
በድን ስለ መንካት
11“የማንኛውንም ሰው አስከሬን የሚነካ ለሰባት ቀን ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤ 12በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ለማንጻት በተመደበው ውሃ ራሱን ያነጻል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል፤ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሱን የማያነጻ ከሆነ ሊነጻ አይችልም። 13ለማንጻት የተመደበው ውሃ በእርሱ ላይ ስላልፈሰሰ በድን ነክቶ ራሱን የማያነጻ፥ እንደ ረከሰ ይቈያል፤ እንዲህ ያለው ሰው ድንኳኑን ያረክሳል፤ ስለዚህም ከእስራኤል ሕዝብ ይለይ።
14“አንድ ሰው በድንኳኑ ውስጥ በሚሞትበት ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆነው ሕግ ይህ ነው። እርሱ በሞተበት ጊዜ በዚያ ድንኳን ውስጥ ያለ ሰው ወይም ወደዚያ የሚገባ ሰው ለሰባት ቀን ያልነጻ ሆኖ ይቈያል። 15በድንኳኑ ውስጥ የሚገኝ ክዳን የሌለው ማንኛውም እንስራም ሆነ ማሰሮ የረከሰ ይሆናል። 16ሰው የገደለውን ወይም በሕመም የሞተውን ሰው በውጭ ወድቆ ሳለ ሬሳውን የሚነካ ሰው፥ ወይም የሰው ዐፅም፥ ወይም መቃብር የሚነካ ሰው ለሰባት ቀን የረከሰ ይሆናል።
17“ርኲሰቱንም ለማስወገድ፥ ለኃጢአት ማስተስረያ ከተቃጠለችው ጊደር ዐመድ ጥቂት ተወስዶ በማሰሮ ውስጥ ይከተት፤ ንጹሕ የምንጭ ውሃም ይጨመርበት፤ 18ቀጥሎም ንጹሕ የሆነ ሰው የሂሶጵ ቅርንጫፍ ወስዶ በውሃው ውስጥ እየነከረ በድንኳኑና በውስጡ በሚገኙት ዕቃዎች ሁሉ ላይ እንዲሁም በድንኳኑ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ይርጨው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ የሆነ ሰው ዐፅም ወይም ሬሳ ወይም መቃብር በነካው ሰው ላይ ውሃ ይርጭበት፤ 19በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን የነጻው ሰው ባልነጻው ሰው ላይ ውሃ ይርጭበት፤ በሰባተኛው ቀን ሰውየውን ያነጻዋል፤ ያም ሰው ልብሱንና ገላውን ካጠበ በኋላ ፀሐይ ስትጠልቅ የነጻ ይሆናል።
20“ያልነጻና ራሱንም ያላነጻ ሰው ለማንጻት የተመደበው ውሃ በላዩ ስላልፈሰሰ የረከሰ ሆኖ ይቈያል፤ እንደዚህ ያለው ሰው የእግዚአብሔርን ድንኳን ስለሚያረክስ ከማኅበሩ ይለይ። 21ይህን ሕግ ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ መጠበቅ ይኖርባችኋል፤ ለማንጻት የሚያገለግለውን ውሃ በላዩ የሚረጨው ሰው ልብሱን ማጠብ ይኖርበታል፤ ውሃውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤ 22ያልነጻ ሰው የሚነካው ነገር ሁሉ የረከሰ ይሆናል፤ ያንንም ዕቃ የሚነካ ሌላ ሰው እስከ ማታ እንደ ረከሰ ይቈያል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ