ኦሪት ዘኊልቊ 28
28
የዘወትር መሥዋዕት
(ዘፀ. 29፥38-46)
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ለእስራኤል ሕዝብ የምትሰጣቸው ትእዛዝ ይህ ነው፦ መዓዛው ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቃጠል የምግብ ቊርባን እንዲያቀርቡልኝ ንገራቸው።”
3“ለእኔ የሚቀርበውም በእሳት የሚቃጠል የምግብ ቊርባን የሚከተለው ነው፦ በየቀኑ ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ዓመት የሞላቸውና ምንም ነውር የሌለባቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች ይሁኑ፤ 4የመጀመሪያው ጠቦት ጠዋት፥ ሁለተኛውም ጠቦት ማታ እንዲቀርብ አድርጉ፤ 5ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር ምርጥ በሆነ፥ በአንድ ሊትር የወይራ ዘይት የተለወሰ፥ አንድ ኪሎ ዱቄት የእህል ቊርባን ሆኖ ይቅረብ፤ 6ይህም በፍጹም የሚቃጠለው የዘወትር መሥዋዕት ነው፤ የዚህ ዐይነቱ መሥዋዕት መዓዛው እኔን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን ሆኖ በመጀመሪያ የቀረበው በሲና ተራራ ላይ ነበር። 7ከመጀመሪያው ጠቦት ጋር የመጠጥ መባ ሆኖ እንዲቀርብ አንድ ሊትር ጠንካራ መጠጥ በመሠዊያው ላይ አፍስሱበት። 8ሲመሽም ሁለተኛውን ጠቦት ልክ የመጀመሪያው በቀረበበት ሁኔታ የመጠጡንም መባ ጨምራችሁ አቅርቡ፤ እርሱም መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን ይሆናል።
የሰንበት መሥዋዕት
9“በሰንበት ቀን አንድ ዓመት የሞላቸውና ምንም ነውር የሌለባቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ በወይራ ዘይት የተለወሰ ሁለት ኪሎ ምርጥ ዱቄት ለእህል ቊርባን አቅርቡ፤ እንዲሁም የመጠጡንም መባ አቅርቡ፤ 10ከመጠጡ መባና ከሚቀርበው ከዘወትር መሥዋዕት ጋር ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በየሰንበቱ ይቅረብ።
ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የሚቀርብ መሥዋዕት
11“በእያንዳንዱ ወር መጀመሪያ ቀን የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ይኸውም ነውር የሌለባቸውን ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ። 12ለእህልም ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት አቅርቡ፤ ይኸውም ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥ 13ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር በዘይት የተለወሰ የእህል ቊርባን አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ ይህም የሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ መባ ሆኖ ይቀርባል። 14ተገቢ ለሆነው የመጠጥ መባ ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሁለት ሊትር መጠጥ፥ ከአውራው በግ ጋር አንድ ተኩል ሊትር መጠጥ፥ ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር አንድ ሊትር የወይን ጠጅ አቅርቡ፤ በዓመቱ ሙሉ፥ ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ስለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት የተሰጠው የሥርዓት መመሪያ ይኸው ነው። 15በየቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር የመጠጥ መባ በመጨመር አንድ ተባዕት ፍየል ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።
በፋሲካና በቂጣ በዓል የሚቀርብ መሥዋዕት
(ዘሌ. 23፥5-14)
16“የጌታ የፋሲካ በዓል የሚከበረው የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ይሁን። #ዘፀ. 12፥1-13፤ ዘዳ. 16፥1-2። 17በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ነው፤ ለሰባት ቀኖች መበላት ያለበት እርሾ ያልነካው ቂጣ ብቻ ነው፤ 18በበዓሉ መጀመሪያ ቀን ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ፤ በእርሱ ምንም ሥራ አትሠሩበትም። 19የምግብ ቊርባን አድርጋችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ ይኸውም ነውር የሌለባቸው ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ 20ተገቢ የሆነውንም የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት አቅርቡ፤ ይኸውም ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥ 21ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ። 22ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ ይህም የኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት ነው። 23እነዚህም ሁሉ የሚቀርቡት በየቀኑ ጠዋት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ተጨማሪ ሆነው ነው። 24መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም የምግብ ቊርባን በተመሳሳይ ሁኔታ በሰባቱም ቀኖች ውስጥ ታቀርባላችሁ፤ ይህንንም የምታቀርቡት በቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የመጠጥ መባ ጋር ተጨማሪ በማድረግ ነው። 25በሰባተኛው ቀን ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ፤ በእርሱ ምንም ሥራ አትሠሩም። #ዘፀ. 12፥14-20፤ 23፥15፤ 34፥18፤ ዘዳ. 16፥3-8።
በመከር በዓል ጊዜ የሚቀርብ መሥዋዕት
(ዘሌ. 23፥15-22)
26“በመከር በዓል መጀመሪያ ቀን አዲስ እህል ለእግዚአብሔር መባ አድርጋችሁ በምታቀርቡበት ጊዜ ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ፤ ሥራም አትሠሩም፤ 27ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፥ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ። 28ተገቢ የሆነውንም የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ ይኸውም ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥ 29ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ 30ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዚህም ዐይነት ለሕዝቡ የኃጢአት ስርየት ሥርዓት ትፈጽማላችሁ። 31ይህን ሁሉ መሥዋዕትና የመጠጥ መባ በቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን ጋር ተጨማሪ በማድረግ ታቀርባላችሁ፤ እንስሶቹም ነውር የሌለባቸው መሆናቸውን አረጋግጡ። #ዘፀ. 23፥16፤ 34፥22፤ ዘዳ. 16፥9-12።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 28: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997