ኦሪት ዘኊልቊ 31
31
በምድያማውያን ላይ የተደረገ ጦርነት
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“በእስራኤል ሕዝብ ላይ ስለ ፈጸሙት በደል ምድያማውያንን ቅጣ፤ ይህንንም ካደረግህ በኋላ አንተ ትሞታለህ።”
3ስለዚህ ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ምድያማውያን በእግዚአብሔር ላይ ስለ ፈጸሙት በደል አደጋ ጥላችሁ ትበቀሉአቸው ዘንድ ለጦርነት ተዘጋጁ፤ 4ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንዳንድ ሺህ ወንዶችን መርጣችሁ ወደ ጦርነቱ ላኩ።”
5ስለዚህ ከብዙ ሺህ እስራኤላውያን መካከል ከያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሺህ ተውጣጥቶ ዐሥራ ሁለት ሺህ የታጠቀ ሠራዊት ለጦርነት ተዘጋጀ። 6ሙሴም ከየነገዱ አንዳንድ ሺህ ሰው በካህኑ በአልዓዛር ልጅ በፊንሐስ መሪነት ወደ ጦርነት ላካቸው፤ ፊንሐስም ከመቅደሱ አንዳንድ ንዋየ ቅድሳትንና ለጦርነት መቀስቀሻ (ክተት) የሚሆን መለከት በእጁ ይዞ ነበር። 7እነርሱም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በምድያማውያን ላይ አደጋ ጥለው ወንዶቹን በሙሉ ገደሉ። 8አምስቱንም የምድያም ነገሥታት ኤዊን፥ ሬቄምን፥ ጹርን፥ ሑርንና ሬባዕን ገደሉ፤ የቢዖርን ልጅ በለዓምንም ገደሉት።
9የእስራኤል ሕዝብ ምድያማውያን ሴቶችንና ሕፃናትን ማረኩ፤ የከብት፥ የበግና የፍየል መንጋዎቻቸውን ወሰዱ፤ ሀብታቸውን ሁሉ በዘበዙ፤ 10ከተሞቻቸውንና የሰፈሩበትን ቦታ ሁሉ አቃጠሉ፤ 11እስረኞችንና እንስሶችን ሳይቀር የማረኩትን ነገር ሁሉ ሰብስበው 12ከዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ ትይዩ በሞአብ ሜዳ ላይ ሰፍረው ወደነበሩት ወደ ሙሴና ወደ አልዓዛር እንዲሁም ወደ መላው ማኅበር አመጡአቸው።
የሠራዊቱ መመለስ
13ሙሴ፥ አልዓዛርና ሌሎቹም የማኅበሩ መሪዎች ሠራዊቱን ለመቀበል ከሰፈር ወጡ፤ 14ሙሴ ግን ከጦርነት በተመለሱት በጭፍራ አለቆች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ፤ 15እንዲህም ሲል ጠየቃቸው፦ “ሴቶችን በሙሉ በሕይወት ያስቀራችሁት ለምንድን ነው? 16በፔዖር ሳለን የበለዓምን ምክር ተቀብለው ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንዲተዉ ያደረጉ ሴቶች መሆናቸውን ዘነጋችሁን? በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የአባር ቸነፈር መቅሠፍት ያመጣም ያ ስሕተት ነበር። #ዘኍ. 25፥1-9። 17ስለዚህ አሁን እያንዳንዱን ወንድ ልጅና እያንዳንዲቱን ከወንድ ጋር የተገናኘች ሴት ግደሉ። 18ነገር ግን ከወንድ ጋር ያልተገናኙትን ልጃገረዶቹን በሕይወት እንዲኖሩ አድርጋችሁ ለራሳችሁ አስቀሩ። 19ከእናንተ መካከል ሰው የገደለ ወይም ሬሳ የነካ ሁሉ ለሰባት ቀን ከሰፈር ውጪ ይቈይ፤ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሳችሁንና የማረካችኋቸውን ሴቶች አንጹ። 20እንዲሁም ማንኛውንም ልብስ ወይም ከቈዳ፥ ከፍየል ጠጒር ወይም ከእንጨት የተሠራ ነገር ሁሉ አጽዱ።”
21ካህኑ አልዓዛር ከዘመቻ ለተመለሱት ወንዶች እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው የሕጉ ሥርዓት መመሪያዎች እነዚህ ናቸው፦ 22-23እንደ ወርቅ፥ ብር፥ ነሐስ፥ ብረት፥ ቆርቆሮ ወይም እርሳስ የመሳሰሉ እሳት የማይጐዳቸው ነገሮች በእሳት ውስጥ አልፈው መጥራት ይኖርባቸዋል፤ እሳት መቋቋም የማይችለውን ነገር ሁሉ ለመንጻት ሥርዓት በተመደበው ውሃ ታጠሩታላችሁ። 24በሰባተኛው ቀን ልብሳችሁን ታጥባላችሁ፤ ከዚያም በኋላ የነጻችሁ ስለምትሆኑ ወደ ሰፈር መግባት ይፈቀድላችኋል።”
የምርኮ ክፍያ
25እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 26“አንተና አልዓዛር ከቀሩት የማኅበሩ መሪዎች ጋር በመሆን እስረኞችንና እንስሶችን ጭምር በምርኮ የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ቊጠሩ። 27በሁለት መድባችሁም አንደኛውን ክፍል ወደ ጦርነት ለሄዱ ወታደሮች፥ ሁለተኛውን ክፍል ለቀሩት የማኅበሩ አባላት ስጡ። 28ለወታደሮቹ ከተመደበው ክፍል፥ ከአምስት መቶ እስረኞች አንዱን፥ እንዲሁም ከከብቱ፥ ከአህዮቹ፥ ከበጎቹና ከፍየሎቹ ከአምስት መቶው አንዱን እጅ ለእኔ ለእግዚአብሔር መባ አድርጋችሁ ለዩ፤ 29ለእኔ ለእግዚአብሔር ልዩ ስጦታ በማድረግም ለካህኑ ለአልዓዛር ስጡት። 30ለቀሩት የማኅበሩ አባላት ከተሰጠውም ክፍል ከኀምሳ እስረኞች አንዱን፥ በዚሁ መጠን ከከብቱ፥ ከአህዮቹ፥ ከበጎቹና ከፍየሎቹ ለይታችሁ ለተቀደሰው ድንኳን ኀላፊዎች ለሆኑት ሌዋውያን ስጡ።” 31ሙሴና አልዓዛርም እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ አደረጉ።
32-35ለራሳቸው ካስቀሩት ጭምር ወታደሮቹ የማረኩት ንብረት ዝርዝር የሚከተለው ነው፦ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥ ሰባ ሁለት ሺህ የቀንድ ከብቶች፥ ሥልሳ አንድ ሺህ አህዮችና፥ ሥልሳ ሁለት ሺህ ከወንድ ጋር ግንኙነት ያላደረጉ ሴቶች። 36ከጠቅላላው ምርኮ ግማሹ፥ ወደ ጦርነት ዘምተው ለተመለሱ ሰዎች የተከፈለ ሲሆን፥ እነኚህም ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበሩ። 37ከእነዚህም ስድስት መቶ ሰባ አምስቱ ለእግዚአብሔር መባ ሆነው የተሰጡ ነበሩ፤ 38ለወታደሮቹ የተሰጡት የቀንድ ከብቶች ብዛት ሠላሳ ስድስት ሺህ ሲሆን ከእነርሱም ሰባ ሁለቱ ለእግዚአብሔር መባ ሆነው የተሰጡ ነበሩ፤ 39ለወታደሮቹ የተሰጡት አህዮች ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ሲሆኑ ከእነዚህም ሥልሳ አንዱ ለእግዚአብሔር መባ ሆነው የተሰጡ ነበሩ፤ 40ለወታደሮቹ የተሰጡት ከወንድ ጋር ግንኙነት ያላደረጉ ሴቶች ዐሥራ ስድስት ሺህ ሲሆኑ፥ ከእነዚህም ሠላሳ ሁለቱ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለዩ ነበሩ። 41ስለዚህም ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት መባውን ለእግዚአብሔር ልዩ ስጦታ በማድረግ ለአልዓዛር ሰጠው።
42የማኅበሩ አባሎች ድርሻ ከወታደሮቹ ድርሻ ጋር ተመሳሳይና እኩል ነበር፤ 43ይኸውም ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥ 44ሠላሳ ስድስት ሺህ የቀንድ ከብቶች፥ 45ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮችና፥ 46ዐሥራ ስድስት ሺህ ከወንድ ጋር ያልተገናኙ ሴቶች ነበሩ። 47ከዚህም ድርሻ ሙሴ ከኀምሳው አንድ እስረኛ፥ ከኀምሳው አንድ እንስሳ ወስዶ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በእግዚአብሔር ድንኳን ላይ ኀላፊነት ላላቸው ለሌዋውያን ሰጠ።
48ከዚህ በኋላ የሠራዊቱ አዛዦች የነበሩት የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች ወደ ሙሴ ቀርበው እንዲህ አሉ፤ 49“እኛ አገልጋዮችህ፥ በእኛ ትእዛዝ ሥር የነበሩትን ወታደሮች ሁሉ ቈጥረናል፤ ከእነርሱ አንድም የጐደለ የለም። 50ስለዚህ እያንዳንዳችን ያገኘነውን የወርቅ ጌጣጌጥ ማለትም የእግር አልቦውን፥ የእጅ አንባሩን፥ የጣት ቀለበቱን፥ የጆሮ ጒትቻውንና የአንገት ድሪውን ሁሉ ለኃጢአታችን ማስተስረያ ለእግዚአብሔር ቊርባን ይሆን ዘንድ ይዘን መጥተናል።” 51ሙሴና አልዓዛር በጌጣጌጥ መልክ ተሠርቶ የነበረውን ወርቅ ሁሉ ተቀበሉ። 52ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች ለጌታ የቀረበው የወርቅ መባ ክብደት ሁለት መቶ ኪሎ ያኽል ነበር። 53የጦር ሹማምንት ያልሆኑት ወታደሮች ግን ያመጡትን ምርኮ ለራሳቸው አስቀሩ። 54ስለዚህ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች ተቀብለው ለእስራኤላውያን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን አመጡት።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኊልቊ 31: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997