የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ፊልሞና 1

1
1ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ ከሆንኩ ከእኔ ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፥
ለተወደደው ወንድማችንና የሥራ ጓደኛችን ለሆነው ለፊልሞና፥ 2ለእኅታችን ለአፍብያ፥ ከእኛ ጋር የክርስቶስ ወታደር ለሆነው ለአርኪጳስ፥ እንዲሁም በቤትህ ለሚሰበሰቡ ምእመናን። #1፥2 “ከቤትህ ለሚሰበሰቡ ምእመናን”፦ በግሪኩ “በቤትህ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን” ይላል። #ቆላ. 4፥17።
3ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
የፊልሞና ፍቅርና እምነት
4በጸሎቴ አንተን እያሰብኩ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ 5በጌታ በኢየሱስ ያለህን እምነትና ለምእመናንም ያለህን ፍቅር ሰምቼአለሁ፤ 6የክርስቶስ በመሆናችን ያለን መልካም ነገር ሁሉ በይፋ ይታወቅ ዘንድ እምነትህን ለሌሎች ለማካፈል እንድትተጋ እጸልያለሁ። 7ወንድሜ ሆይ! በአንተ ምክንያት የምእመናን ልብ ስለ ታደሰ ፍቅርህ ታላቅ ደስታንና መጽናናትን ሰጥቶኛል።
ጳውሎስ ስለ ኦኔሲሞስ ያቀረበው ምልጃ
8ስለዚህ ተግባርህን ፈጽም ብዬ አንተን ለማዘዝ በክርስቶስ ድፍረት ነበረኝ፤ 9ሆኖም እንደዚያ ከማድረግ ይልቅ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንኩት እኔ ሽማግሌው ጳውሎስ በፍቅር መለመንን እመርጣለሁ። 10እኔ እስር ቤት እያለሁ ልጄ ስለ ሆነው ስለ ኦኔሲሞስ አንተን እለምንሃለሁ። #ቆላ. 4፥9። 11አናሲሞስ ከዚህ በፊት አይጠቅምህም ነበር፤ አሁን ግን ለአንተም ሆነ ለእኔ ጠቃሚ ነው።
12እነሆ እርሱን ወደ አንተ መልሼ ልኬዋለሁ፤ እርሱን ወደ አንተ ስልከውም የገዛ ራሴን ልብ እንደ ላክሁ አድርጌ እቈጥረዋለሁ። 13በወንጌል ምክንያት እዚህ ታስሬ ሳለሁ በአንተ ምትክ ሆኖ እንዲያገለግለኝ እርሱ ከእኔ ጋር ቢሆን ደስ ባለኝ ነበር፤ 14ነገር ግን የአንተ መልካም ሥራ በግዴታ ሳይሆን በውዴታ እንዲሆን ብዬ አንተን ሳላስፈቅድ ምንም ማድረግ አልፈለግሁም።
15ኦኔሲሞስ እስከ አሁን ለጥቂት ጊዜ የተለየህ ምናልባት ከእንግዲህ ወዲህ ለሁልጊዜ ከአንተ ጋር እንዲኖር ይሆናል። 16ከእንግዲህ ወዲህ ከአንተ ጋር የሚኖረውም እንደ ባሪያ ሳይሆን ከባሪያ የበለጠ ሆኖ እንደ ውድ ወንድም ነው፤ እርሱ ለእኔ ውድ ወንድም ነው፤ ይሁን እንጂ በሥጋ እርሱ በአገልግሎቱ ስለሚጠቅምህ በመንፈሱ ደግሞ በክርስቶስ ወንድምህ ስለ ሆነ ለአንተ ይበልጥ ተወዳጅ ነው።
17እንግዲህ እኔን እንደ ወንድም አድርገህ ከቈጠርከኝ ልክ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። 18ያደረሰብህ በደል ቢኖር ወይም ዕዳ ቢኖርበት ዕዳውን በእኔ ላይ አድርገው። 19እነሆ እኔ ጳውሎስ “ዕዳውን እከፍልሃለሁ” ብዬ በገዛ እጄ ጽፌ አረጋግጥልሃለሁ፤ ሆኖም ስለ ሕይወትህ አንተ ራስህ እንኳ የእኔ ባለዕዳ መሆንክን እኔ ላስታውስህ አያስፈልግም። 20እንግዲህ ወንድሜ ሆይ! ይህን መልካም ነገር እንድታደርግልኝ በጌታ እለምንሃለሁ፤ እባክህ ልቤን በክርስቶስ አድስልኝ።
21ይህን የጻፍኩልህ እንደምትታዘዘኝ በመተማመን ነው፤ እንዲያውም እኔ ከምጠይቅህ በላይ እንደምታደርግ ዐውቃለሁ። 22በዚያውም እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ሰምቶ ወደ እናንተ እንድመጣ እንደሚያደርገኝ ተስፋ ስላለኝ የማርፍበትን ቤት አዘጋጅልኝ።
የመጨረሻ ሰላምታ
23በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ከእኔ ጋር የታሰረው ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብልሃል፤ #ቆላ. 1፥7፤ 4፥12። 24እንዲሁም የሥራ ጓደኞቼ የሆኑት ማርቆስ፥ አርስጥሮኮስ፥ ዴማስና፥ ሉቃስ ሰላምታ ያቀርቡልሃል። #ሐ.ሥ. 12፥12፤25፤ 13፥13፤ 15፥37-39፤ 19፥29፤ 27፥2፤ ቆላ. 4፥10፤14፤ 2ጢሞ. 4፥10፤11።
25የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ