የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 1

1
የምሳሌዎች ጥቅም
1እነዚህ ምሳሌዎች የዳዊት ልጅ የሆነው፥ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን የተናገራቸው ናቸው። #1ነገ. 4፥32። 2ምሳሌዎቹም ጥበብንና መልካም ምክርን ለመገንዘብ፥ ጥልቅ አስተሳሰብ ያለውን የዕውቀት ቃል ለመረዳት የሚጠቅሙ ናቸው። 3እነርሱም እውነትን ፍትሕንና ቅንነትን በመከተል ሥርዓትንና ጥበብን ወደ ተሞላ ሕይወት ይመራሉ። 4በዕውቀት ላልበሰሉ ብልኅነትን ለወጣቶችም ዕውቀትንና ማስተዋልን እንዲያገኙ ያደርጋሉ። 5እነዚህ ምሳሌዎች ጠቢባን ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ፥ አስተዋዮችም ተጨማሪ መመሪያ የሚሆናቸውን ምክር እንዲያገኙ ያደርጋሉ። 6በዚህ ዐይነት ስውር የሆኑ የምሳሌዎችን ምሥጢር ጠቢባን የሚያቀርቡአቸውን እንቆቅልሾች መረዳት ያስችላሉ።
ምክር ለወጣቶች
7እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ሞኞች ግን ጥበብና ሥነ ሥርዓትን ይንቃሉ። #ኢዮብ 28፥28፤ መዝ. 111፥10፤ ምሳ. 9፥10።
8ልጄ ሆይ! የአባትህን ምክር ስማ፤ እናትህ የምታስተምርህንም ሁሉ አትናቅ። 9እነርሱም ለራስህ ክብርን እንደሚያቀዳጅ ዘውድ፥ ለአንገትህም ውበትን እንደሚሰጥ ሐብል ይሆኑልሃል።
10ልጄ ሆይ! ኃጢአተኞች እንድትከተላቸው ቢያባብሉህ እሺ አትበላቸው። 11ምናልባትም እንዲህ ይሉህ ይሆናል፦ “ከበደል ንጹሕ የሆነውን ሰው መንገድ ላይ አድብተን እንድንገድለው ከእኛ ጋር ና! 12መቃብር ሙታንን እንደሚውጥ፥ እኛም እነርሱን በሕይወት ሳሉ እንዋጣቸው! ወደ ጒድጓድ እንደሚወርዱም ሰዎች እናድርጋቸው! 13ውድ የሆኑ ብዙ ዐይነት ዕቃዎች እናገኛለን፤ ከቅሚያ በተገኘ ሀብት ቤቶቻችንን እንሞላለን፤ 14ና ከእኛ ጋር ተባበር፤ በስርቆትና በቅሚያ የምናገኘውን ሀብት በኅብረት እንጠቀምበታለን።”
15ልጄ ሆይ! እነዚህን ከመሰሉ ሰዎች ጋር አብረህ አትሂድ፤ ከእነርሱም ራቅ። 16እነርሱ ክፉ ነገርን ለማድረግ ይሮጣሉ፤ ሰውን ለመግደልም ፈጣኖች ናቸው። 17ልትይዘው የምትፈልገው ወፍ እያየህ የምታጠምደው ወጥመድ ዋጋ የለውም። 18ይህን የሚያደርጉ ሰዎች የሚሞቱበትን ወጥመድ ራሳቸው ይዘረጋሉ። 19በሕገ ወጥ መንገድ ሀብትን የሚሰበስቡ ሰዎች ያ የሰበሰቡት ሀብት ሕይወታቸውን ያጠፋዋል። በግፍም የሚበለጽጉ ሰዎች ዕድል ፈንታቸው ይኸው ነው።
ጥበብ የምታሰማው ጥሪ
20ጥበብ በመንገድ ላይ ትጮኻለች፤ በአደባባይም ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ታሰማለች። 21ሰው በሚበዛበት መንገድ ትጮኻለች፤ በከተማው መግቢያ የሕዝብ መሰብሰቢያ ላይ ንግግርዋን ታሰማለች። እንዲህም ትላለች፦ #ምሳ. 8፥1-3።
22“እናንተ ዕውቀት የጐደላችሁ! እስከ መቼ ድረስ የሞኝነትን መንገድ ትከተላላችሁ! እናንተስ ፌዘኞች! እስከ መቼ ድረስ በማፌዝ ትደሰታላችሁ! ሞኞችስ እስከ መቼ ድረስ ዕውቀትን ትጠላላችሁ! 23ተግሣጼን ብትቀበሉ ሐሳቤን በገለጥሁላችሁ ነበር፤ ቃሌንም እንድታውቁ ባደረግሁ ነበር። 24ወደ እኔ እንድትመጡ እጄን ዘርግቼ ጠራኋችሁ፤ እናንተ ግን ጥሪዬን አልተቀበላችሁም። 25ምክሬን ናቃችሁ፤ ተግሣጼንም አልተቀበላችሁም። 26ስለዚህም መከራ በእናንተ ላይ በሚደርስባችሁ ጊዜ እስቅባችኋለሁ፤ ችግር በሚደርስባችሁም ጊዜ አፌዝባችኋለሁ። 27ድንጋጤ እንደ ሞገደኛ ነፋስ ሲመታችሁ፥ መከራም እንደ ዐውሎ ነፋስ ሲጠርጋችሁ፥ ጭንቀትና ችግር ሲደርስባችሁ አፌዝባችኋለሁ። 28በዚያን ጊዜ እኔን ጥበብን ትጣራላችሁ፤ እኔ ግን አልመልስላችሁም፤ በየቦታውም ትፈልጉኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙኝም። 29ዕውቀትን ጠላችሁ፤ እግዚአብሔርንም መፍራት አልወደዳችሁም። 30ምክሬን አልፈለጋችሁም፤ ተግሣጼንም ንቃችኋል። 31ስለዚህ የሚገባችሁን ቅጣት ትቀበላላችሁ፤ የተንኰላችሁንም ውጤት ታገኛላችሁ። 32ዕውቀት የጐደላቸው ሰዎች ከጥበብ በመራቃቸው ምክንያት ይሞታሉ፤ ሞኞችም ከቸልተኛነታቸው የተነሣ ይጠፋሉ። 33እኔን የሚሰማ ግን ለሕይወቱ ዋስትና ይኖረዋል፤ ምንም የሚያስፈራው ነገር ሳይደርስበት በሰላም ይኖራል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ