የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 105

105
እግዚአብሔርና ሕዝቡ
(1ዜ.መ. 16፥8-22)
1እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ስሙንም ጥሩ
ያደረገውንም ሁሉ ለአሕዛብ ንገሩ።
2ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፤
ያደረገውንም አስደናቂ ነገር ሁሉ ተናገሩ።
3በቅዱስ ስሙ ደስ ይበላችሁ!
እግዚአብሔርን የሚፈልግ ሰው ሁሉ ሐሴት ያድርግ!
4በእግዚአብሔርና
በኀያል ሥልጣኑ ተማመኑ፤
ዘወትርም እርሱን ፈልጉ።
5-6አገልጋዮች የሆናችሁ የእስራኤል ልጆች ሆይ!
የእግዚአብሔር ምርጥ የሆናችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ!
እግዚአብሔር ያደረጋቸውን ድንቅ ነገሮች፥ የሰጠውን ፍርድና
ያደረጋቸውን ተአምራት አስታውሱ።
7እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤
ፍርዱም በዓለም ሁሉ ነው።
8ቃል ኪዳኑን ወይም የሰጠውን ተስፋ እስከ ሺህ ትውልድም ሆነ
ለዘለዓለም አይረሳም።
9ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ይጠብቃል፤
ለይስሐቅ የሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸናል። #ዘፍ. 12፥7፤ 17፥8፤ 26፥3።
10ለያዕቆብ ሥርዓት፥
ለእስራኤልም ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን አድርጎ አጸናው።
11ይህም ቃል ኪዳን “የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ፤
ለአንተም የተመደበ ርስት ይሆናል” የሚል ነው። #ዘፍ. 28፥13።
12ይህም የሆነው እነርሱ በቊጥር አነስተኞች
ለሀገሩም እንግዶች ሆነው ሳለ ነው።
13ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላ ሕዝብ፥
ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ተንከራተቱ።
14እግዚአብሔር ግን ማንም እንዲጨቊናቸው አልፈቀደም፤
ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።
15“የተመረጡ አገልጋዮቼን አትንኩ፤
ነቢያቴንም አትጒዱ” በማለት አስጠነቀቃቸው። #ዘፍ. 20፥3-7።
16እግዚአብሔር ራብን በአገራቸው ላይ አመጣ፤
ምግባቸውንም ሁሉ አጠፋ። #ዘፍ. 41፥53-57።
17ነገር ግን ከእነርሱ አንዱን ሰው አስቀድሞ ላከ፤
እርሱም እንደ ባሪያ የተሸጠው ዮሴፍ ነበር። #ዘፍ. 37፥28፤ 45፥5።
18እግሮቹ በእግር ብረት ታስረው ነበር፤
በአንገቱም የብረት ቀለበት ነበር።
19ዮሴፍ ራሱ አስቀድሞ የተናገረው
እስኪፈጸም ድረስና
የእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛነቱን እስኪያረጋግጥለት ድረስ ነው። #ዘፍ. 39፥20—40፥23።
20ከዚያ በኋላ የግብጽ ንጉሥ
ዮሴፍን ነጻ አደረገው። #ዘፍ. 41፥14።
21በመንግሥቱ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው፤
በምድሩም ሁሉ ላይ ገዢ አደረገው፤ #ዘፍ. 41፥39-41።
22በንጉሡ ባለሥልጣኖች ላይ አዛዥ ሆነ፤
ለንጉሡም አማካሪዎች ጥበብን ያስተምራቸው ዘንድ ሥልጣን ተሰጠው።
23ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ወደ ግብጽ ሄደ፤
በዚያም አገር ስደተኛ ሆኖ ኖረ። #ዘፍ. 46፥6፤ 47፥11።
24እግዚአብሔር ወገኖቹን አበዛቸው፤
ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው።
25እግዚአብሔር ግን ወገኖቹን እንዲጠሉና፥
በአገልጋዮቹም ላይ በተንኰል እንዲነሡ ግብጻውያንን አስጨከነ። #ዘፀ. 1፥7-14።
26ከዚህ በኋላ አገልጋዩን ሙሴንና
የመረጠውን አሮንን ላከ። #ዘፀ. 3፥1—4፥17።
27እነርሱ በግብጽ ምድር የእግዚአብሔርን ድንቅ ነገሮችና ተአምራትን
አደረጉ።
28እግዚአብሔር በአገሩ ላይ ጨለማ እንዲሆን አደረገ፤
ይሁን እንጂ ግብጻውያን ትእዛዞቹን አልፈጸሙም። #ዘፀ. 10፥21-23።
29የወንዞቻቸውንም ውሃ ወደ ደም ለወጠ፤
ዓሣዎቻቸውንም ሁሉ ገደለ። #ዘፀ. 7፥17-21።
30አገራቸው በእንቁራሪት ተሸፈነች፤
ቤተ መንግሥቱ እንኳ ሳይቀር ሁሉ ቦታ በእንቁራሪት ተሞላ። #ዘፀ. 8፥1-6።
31ተናካሽ ዝንቦችና ተናካሽ ትንኞች በአገሩ ሁሉ ላይ
እንዲርመሰመሱ አዘዘ። #ዘፀ. 8፥16-17፤20-24።
32እግዚአብሔር በአገራቸው ላይ በዝናብ ፈንታ
የበረዶ ናዳንና መብረቅን አወረደ።
33የወይን ተክሎቻቸውንና የበለስ ዛፎቻቸውን አጠፋ፤
ሌሎቹንም ዛፎቻቸውን ሁሉ ሰባበረ። #ዘፀ. 9፥22-25።
34እርሱ ባዘዘው መሠረት ሊቈጠር የማይችል
የአንበጣና የኲብኲባ መንጋ መጣ።
35በምድሩ ላይ ያለውን ለምለም ተክልና
ሰብል ሁሉ በልተው እንዲጨርሱ አደረገ፤ #ዘፀ. 10፥12-15።
36የእያንዳንዱን ግብጻዊ ቤተሰብ የበኲር ልጅ ገደለ። #ዘፀ. 12፥29።
37ከዚህ በኋላ እስራኤላውያንን መርቶ አወጣ፤
ሲወጡም ብርና ወርቅ ይዘው ነበር፤
ከነገዶቻቸውም መካከል ወደ ኋላ የቀረ ማንም አልነበረም።
38ግብጻውያንም እጅግ ፈርተዋቸው ስለ ነበር፤
በመውጣታቸው ተደሰቱ። #ዘፀ. 12፥33-36።
39በሚሄዱበትም ጊዜ በደመና ጋረዳቸው፤
በሌሊትም፥ ብርሃን የሚሰጣቸውን እሳት አዘጋጀላቸው። #ዘፀ. 13፥21-22።
40ምግብ በጠየቁት ጊዜ ድርጭቶችን ላከላቸው።
ከሰማይ እንጀራን ልኮ አጠገባቸው። #ዘፀ. 16፥2-15።
41አለቱን ሰነጠቀ፤ ውሃም ወጣ፤
በበረሓውም ውስጥ እንደ ወንዝ ውሃ ፈሰሰ። #ዘፀ. 17፥1-7፤ ዘኍ. 20፥2-13።
42ለአገልጋዩ ለአብርሃም የሰጠውን
ቅዱስ ቃል ኪዳን አሰበ።
43ስለዚህ የተመረጠውን ሕዝቡን መርቶ አወጣ፤
እነርሱም በደስታ ዘመሩ፤ እልልም አሉ።
44የሌሎች ሕዝቦችን ምድር ሰጣቸው፤
ሌሎች የደከሙባቸውንም እርሻዎች አወረሳቸው። #ኢያሱ 11፥16-23።
45ይህንንም ሁሉ ማድረጉ ሕዝቡ ድንጋጌውን እንዲጠብቁና
ሕጉንም እንዲፈጽሙ ነው።
እግዚአብሔር ይመስገን!

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ