የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 44

44
የመማጠኛ ጸሎት
1አምላክ ሆይ!
በጥንት ዘመን ያደረግኸውን ሁሉ
በጆሮአችን ሰማን፤
የቀድሞ አባቶቻችንም በዘመናቸው
ስላደረግሃቸው ድንቅ ነገሮች ሁሉ ነግረውናል።
2በቀድሞ ዘመን እጆችህ ያደረጉትን ድርጊት ሁሉ
አባቶቻችን ነግረውናል፤
ይኸውም፥ እነርሱን ለመትከል
ሕዝቦችን አባረሃል፤
እነርሱን ለማደላደል ነዋሪዎቹን አጥፍተሃል።
3እነርሱ ምድርን የወረሱት በሰይፋቸው አይደለም፤
ድል አድርገው የወሰዱትም በራሳቸው ኀይል አይደለም፤
ይህን ሁሉ ያደረጉት አንተ ስለ ወደድካቸውና
ከእነርሱም ጋር በመሆን በኀይልህና በብርታትህ
ስለ ረዳሃቸው ነው።
4አንተ ንጉሤና አምላኬ ነህ፤
የያዕቆብ ዘር ለሆነው ሕዝብህ፥
ድልን የምታጐናጽፍ አንተ ነህ።
5በአንተ ርዳታ ጠላቶቻችንን ድል እንነሣለን፤
በስምህም ተቃዋሚዎቻችንን እንረግጣለን።
6በቀስቴ አልተማመንም፤
ሰይፌም አያድነኝም።
7ከጠላቶቻችን የምታድነን አንተ ነህ፤
የሚጠሉንንም የምታሳፍርልን አንተ ነህ።
8አምላክ ሆይ! ዘወትር በአንተ እንመካለን፤
ስምህንም ለዘለዓለም እናመሰግናለን።
9አሁን ግን ጣልከን፤ አዋረድከንም፤
ከሚዘምተው ሠራዊታችን ጋር
አብረህ መውጣትን ትተሃል።
10ከጠላቶቻችን ፊት እንድንሸሽ አደረግኸን፤
ጠላቶቻችንም ያለንን ሀብት ሁሉ ዘረፉን።
11እንደሚታረዱ በጎች አደረግኸን፤
በአሕዛብ ምድር በተንከን።
12ሕዝብህን በአነስተኛ ዋጋ ሸጥከው፤
እርሱንም በመሸጥ ምንም አላተረፍክም።
13በጐረቤቶቻችን የምንነቀፍ አደረግኸን፤
በዙሪያችን ላሉትም መዘባበቻና መሳለቂያ አደረግኸን።
14በሕዝቦች መካከል መተረቻ አደረግኸን፤
እነርሱም ራሳቸውን ይነቀንቁብናል።
15ውርደቴ ዘወትር በፊቴ ነው፤
ፊቴንም ኀፍረት ሸፍኖታል።
16እንዲህም የሆንኩት
ጠላቶቼ በሚበቀሉኝ ጊዜ ሌሎች ሰዎች
ሲያፌዙብኝና ሲሳለቁብኝ በመስማቴ ነው።
17ይህም ሁሉ የደረሰብን
አንተን ሳንረሳና ቃል ኪዳንህንም ሳናፈርስ ነው።
18ልባችን ለአንተ እምነተቢስ አልሆነም፤
እግራችንም ከአንተ መንገድ አልወጣም።
19ነገር ግን አራዊት በሚኖሩበት ስፍራ ሰብረኸናል።
በድቅድቅ ጨለማም ሸፍነኸናል።
20የአምላካችንን ስም ረስተን ቢሆን፥
ወደ ባዕዳን አማልክት እጆቻችንን ዘርግተን ቢሆን፥
21አንተ የተሰወረውን ሐሳባችንን ስለምታውቅ
በደላችንን ገልጠህ ባየህብን ነበር።
22ነገር ግን ስለ አንተ በየቀኑ እንገደላለን፤
እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጥረናል። #ሮም 8፥36።
23ጌታ ሆይ! ንቃ! ስለምንስ ታንቀላፋለህ?
ተነሥ! ለዘለዓለም አትተወን!
24መጨቈናችንንና ችግራችንን ቸል በማለት
ስለምን ከእኛ ትሰወራለህ?
25መሬት እስክንነካ ድረስ አጐንብሰናል፤
በምድር ላይም ተዘርረናል።
26ተነሥ እኛን ለመርዳት ና!
ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህም ተቤዠን!

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ