የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 9

9
ቅን ፈራጅ ለሆነው አምላክ የሚቀርብ ምስጋና
1አምላክ ሆይ! በሙሉ ልቤ አመሰግንሃለሁ፤
ያደረግኸውንም ድንቅ ነገር ሁሉ እናገራለሁ!
2በአንተ ደስ ይለኛል፤ ሐሴትም አደርጋለሁ፤
ልዑል እግዚአብሔር ሆይ!
ለስምህ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ።
3አንተ በምትገለጥበት ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላ ይመለሳሉ፤
ተሰናክለውም ከፊትህ ይጠፋሉ።
4በዙፋንህ ላይ ተቀምጠህ
ትክክለኛ ፍርድን ፈራጅ ነህ።
የእኔንም ጉዳይ በማየት መብቴን ጠብቀህ በቅን ትፈርድልኛለህ።
5አሕዛብን ገሠጽክ፤
ክፉዎችንም አጠፋህ፤
ስማቸውንም ለዘለዓለም ደመሰስህ።
6ጠላቶቻችን ለዘለዓለም ጠፍተዋል፤
ከተሞቻቸውንም ደምስሰሃል፤
መታሰቢያቸውም ጠፍቶአል።
7እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም ንጉሥ ሆኖ ይኖራል፤
ዙፋኑንም ለፍርድ አዘጋጅቶአል።
8ዓለምን በፍትሕ ያስተዳድራል፤
ሕዝቦችንም በትክክል ይዳኛል።
9እግዚአብሔር ለተጨቈኑት መጠጊያ ነው፤
በመከራ ጊዜም መከላከያ አምባ ነው።
10አምላክ ሆይ! በአንተ የሚተማመኑትን ሁሉ ስለማትተዋቸው
ስምህን የሚያውቁ ሁሉ ይተማመኑብሃል።
11በጽዮን ለሚኖር እግዚአብሔር
የምስጋና መዝሙር አቅርቡ!
ያደረገውንም ድንቅ ሥራ
ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ!
12እግዚአብሔር የተጨቈኑትን ያስታውሳል
ጩኸታቸውን አይረሳም
የሚበድሉአቸውንም ይቀጣል።
13እግዚአብሔር ሆይ!
ምሕረትን አድርግልኝ!
ጠላቶቼ የሚያደርሱብኝን መከራ ተመልከት!
ከሞትም አድነኝ።
14ይህን ብታደርግልኝ፥
በጽዮን አደባባይ፥
ምስጋናህን ሁሉ ለሕዝብ እናገራለሁ፤
ስላዳንከኝም ደስታዬን እገልጣለሁ።
15አሕዛብ በቈፈሩት ጒድጓድ ወደቁ፤
በደበቁት ወጥመድ ተያዙ።
16እግዚአብሔር በእውነተኛ ፍርዱ ተገለጠ፤
ክፉ ሰዎችም በክፉ ሥራቸው ወጥመድ ተያዙ።
17ክፉዎች ወደ ሙታን ዓለም ይወርዳሉ።
እግዚአብሔርንም ከረሱ ሕዝቦች ጋር ይቀላቀላሉ።
18ችግረኞች ዘወትር እንደ ተረሱ አይቀሩም፤
የድኾችም ተስፋ ከንቱ ሆኖ ለዘለዓለም አይጠፋም።
19አምላክ ሆይ! ሰዎች በብርታታቸው
እንዳይጓደዱብህ ተነሥ፤
በአሕዛብም ላይ ፍረድ።
20እግዚአብሔር ሆይ!
እንዲፈሩህና
ሰብአዊ ፍጡሮች መሆናቸውንም እንዲያውቁ አድርጋቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ