የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 11

11
ሁለቱ ምስክሮች
1ከዚህ በኋላ ለመለኪያ እንደሚያገለግል በትር ያለ አንድ ሸንበቆ ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልኩ፦ “ተነሥ፤ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና መሠዊያውን ለካ፤ በዚያ የሚያመልኩትንም ቊጠር፤ #ዘካ. 2፥1-2። 2ከቤተ መቅደሱ ውጪ ያለውን ክፍት ቦታ ግን ተወው፤ እርሱ ለአሕዛብ የተሰጠ ስለ ሆነ አትለካው፤ አሕዛብ ቅድስቲቱን ከተማ ለአርባ ሁለት ወር ይረግጡአታል፤ #ሉቃ. 21፥24። 3ሁለቱ ምስክሮቼ የሐዘን ልብስ ለብሰው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን ትንቢት እንዲናገሩ ኀይል እሰጣቸዋለሁ።”
4እነርሱ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው፤ #ዘካ. 4፥3፤11-14። 5ማንም እነርሱን ሊጐዳ ቢፈልግ እሳት ከአፋቸው ወጥቶ ጠላቶቻቸውን ያቃጥላል፤ እነርሱን ሊጐዳ የሚፈልግ ሁሉ የሚሞተው በዚህ ዐይነት ነው። 6እነርሱ ትንቢት በሚናገሩባቸው በእነዚህ ቀኖች ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ እንዲሁም ውሃዎችን ወደ ደም ለመለወጥና በሚፈልጉትም ጊዜ ሁሉ በማንኛውም ዐይነት መቅሠፍት ምድርን ለመምታት ሥልጣን አላቸው። #1ነገ. 17፥1፤ ዘፀ. 7፥17-19፤ 1ሳሙ. 4፥8።
7ምስክርነታቸውን ከጨረሱ በኋላ ከጥልቁ ጒድጓድ የሚወጣው አውሬ ከእነርሱ ጋር ተዋግቶ ያሸንፋቸዋል፤ ይገድላቸዋልም፤ #ዳን. 7፥7፤21፤ ራዕ. 13፥5-7፤ 17፥8። 8ሬሳቸውም በምሳሌያዊ አጠራር ሰዶም ወይም ግብጽ በምትባል በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይጋደማል፤ ይህች ከተማ የእነርሱ ጌታ የተሰቀለባት ናት። #ኢሳ. 1፥9-10። 9ልዩ ልዩ ወገንና፥ ነገድ፥ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችና ሕዝቦች ሦስት ቀን ተኩል ሬሳቸውን ይመለከታሉ፤ ሬሳቸው እንዳይቀበርም ይከለክላሉ። 10እነዚህ ሁለቱ ነቢያት የምድር ሰዎችን አስጨንቀው ስለ ነበረ በምድር የሚኖሩ ሰዎች በነቢያቱ ሞት ደስ ይላቸዋል፤ በደስታም በዓል ያደርጋሉ፤ ስጦታም ይለዋወጣሉ። 11ነገር ግን ሦስት ቀን ተኩል ካለፈ በኋላ ሕይወት የሚሰጥ እስትንፋስ ከእግዚአብሔር መጥቶ ወደ ሬሳዎቹ ገባ፤ በእግራቸውም ቆሙ፤ ያዩአቸውም ሰዎች እጅግ ፈሩ። #ሕዝ. 37፥10። 12ከዚህ በኋላ ሁለቱ ነቢያት “ወደዚህ ወደ ላይ ውጡ!” የሚል ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸው እየተመለከቱአቸውም በደመና ወደ ሰማይ ወጡ። #2ነገ. 2፥11። 13በዚያኑ ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የከተማይቱም አንድ ዐሥረኛ ፈራረሰ፤ በምድር መናወጥም ምክንያት ሰባት ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ ከሞት የተረፉትም እጅግ ፈሩ፤ የሰማይንም አምላክ አከበሩ። #ራዕ. 6፥12፤ 16፥18።
14ሁለተኛው ወዮ አለፈ፤ እነሆ፥ ሦስተኛው ወዮ ቶሎ ይመጣል።
ሰባተኛው መለከት
15ሰባተኛውም መልአክ እምቢልታውን ነፋ፤ በሰማይም “የዓለም መንግሥት የጌታ የአምላካችንና የመሲሑ ሆናለች፤ እርሱ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል፤” የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ። #ዘፀ. 15፥18፤ ዳን. 2፥44፤ 7፥14፤27። 16በእግዚአብሔር ፊት በዙፋኖቻቸው ላይ የተቀመጡት ኻያ አራቱ ሽማግሌዎችም በግንባራቸው ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ 17እንዲህም አሉ፦
“ያለህና የነበርክ፤
ሁሉን የምትችል ጌታ አምላክ ሆይ!
ትልቁን ሥልጣንህን በእጅህ ስላደረግህና
ስለ ነገሥክ እናመሰግንሃለን።
18አሕዛብ ተቈጡ፤
የአንተም ቊጣ መጣ፤
ሙታን ፍርድ የሚያገኙበት ጊዜም ደረሰ፤
ለአገልጋዮችህ ለነቢያትና
ለቅዱሳን ስምህንም ለሚያከብሩት፥
ለታናናሾችና ለታላላቆች፥
ዋጋቸውን የምትሰጥበት ጊዜ ደረሰ፤
ምድርን ያጠፉአትን የምታጠፋበት ጊዜም ደረሰ።” #መዝ. 2፥5፤ 110፥5፤ 115፥13።
19በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ተከፈተ፤ የእርሱም የኪዳን ታቦት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ታየ። መብረቅ፥ ድምፅ፥ ነጐድጓድ፥ የምድር መናወጥና ታላቅም በረዶ ሆነ። #ራዕ. 8፥5፤ 16፥18፤21።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ