የዮሐንስ ራእይ 13
13
ሁለቱ አውሬዎች
1ከዚህ በኋላ አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ ዐሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፤ በቀንዶቹም ላይ ዐሥር ዘውዶች ነበሩ፤ በራሶቹም ላይ የስድብ ስሞች ነበሩ። #ዳን. 7፥3። 2ያየሁት አውሬ ነብር ይመስል ነበር፤ እግሮቹ የድብ እግሮች፥ አፉ የአንበሳ አፍ ይመስል ነበር። ዘንዶው የራሱን ኀይልና የራሱን ዙፋን ትልቅም ሥልጣን ለአውሬው ሰጠው። #ዳን. 7፥4-6። 3ከአውሬው ራሶች አንዱ ለሞት የሚያደርስ ቊስል እንደ ነበረው ሆኖ አየሁት፤ ነገር ግን ለሞት የሚያደርሰው ቊስሉ ድኖአል፤ ዓለም በሙሉ በመደነቅ አውሬውን ተከተለ። 4ለአውሬው ሥልጣን በመስጠቱ ሰዎች ሁሉ ለዘንዶው ሰገዱለት፤ “አውሬውን የሚመስል ማን ነው? ከእርሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” እያሉ ለእርሱም ሰገዱለት።
5የትዕቢትና የስድብ ቃል የሚናገርበት አፍ ለአውሬው ተሰጠው፤ አርባ ሁለት ወር በሥልጣን እንዲሠራም ተፈቀደለት። 6እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ስም፥ መኖሪያውንና በሰማይ የሚኖሩትን መሳደብ ጀመረ። #ዳን. 7፥8፤25፤ 11፥36። 7ቅዱሳንን እንዲዋጋና ድል እንዲነሣቸው ሥልጣን ተሰጠው፤ በነገድና በወገን፥ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች በሚናገሩና በሕዝብ ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው። #ዳን. 7፥21። 8ዓለም ሲፈጠር ጀምሮ ስሞቻቸው በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፈ በዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ። #መዝ. 69፥28።
9ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ! 10“ለመማረክ የተመደበ ይማረካል፤ በሰይፍ ለመገደል የተመደበ በሰይፍ ይገደላል፤” እንግዲህ የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚያስፈልገው በዚህ ጊዜ ነው። #ኤር. 15፥2፤ 43፥11።
11ሌላ አውሬ ደግሞ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ አነጋገሩም እንደ ዘንዶው ነበር፤ 12የመጀመሪያውን አውሬ ተክቶ በእርሱ ሥልጣን ይሠራ ነበር፤ ምድርና በእርስዋ ላይ የሚኖሩት ሁሉ ለመጀመሪያው አውሬው እንዲሰግዱ አደረገ፤ ይህም አውሬ ያ ለሞት የሚያደርስ ቊስል የዳነለት የመጀመሪያው አውሬ ነው። 13ይህ ሁለተኛው አውሬ ግን በሰዎች ፊት እሳትን ከሰማይ እስከማውረድ ድረስ ታላላቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር። 14በመጀመሪያው አውሬ ፊት እንዲያደርግ በተፈቀደለት ተአምራት ምክንያት በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ያስት ነበር፤ በሰይፍ ቈስሎ ለዳነው ለአውሬው ክብር ምስል እንዲሠሩም በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ያዛቸዋል። 15ሁለተኛው አውሬ ለመጀመሪያው አውሬ ምስል የሕይወት እስትንፋስ ለመስጠት ሥልጣን ተሰጠው፤ የሕይወት እስትንፋስ ለመስጠት ሥልጣን የተሰጠውም ምስሉ ለመናገር እንዲችልና ለእርሱ የማይሰግዱት ሁሉ እንዲገደሉ ያደርግ ዘንድ ነው። 16ሁለተኛው አውሬ ታናናሾችም ሆኑ ታላላቆች፥ ሀብታሞችም ሆኑ ድኾች፥ ጌቶችም ሆኑ አገልጋዮች፥ ሁሉም በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት እንዲያደርጉ አስገደዳቸው። 17በዚህ ዐይነት የአውሬውን ስም የሚያሳይ ምልክት ወይም የስሙ ቊጥር የሌለው ማንም ሰው መግዛትም ሆነ መሸጥ አይችልም።
18ጥበብ የሚፈለገው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው፤ አእምሮ ያለው የአውሬውን ቊጥር ያስላው፤ ቊጥሩ የሚያመለክተው ሰውን ነው፤ ቊጥሩም ስድስት መቶ ሥልሳ ስድስት ነው።
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 13: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997