ወደ ሮም ሰዎች 11
11
እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ጨርሶ ያልጣለ መሆኑ
1እስቲ ደግሞ ልጠይቅ፦ እግዚአብሔር የራሱን ሕዝብ ጥሎአልን? ከቶ አልጣለውም! እኔም ራሴ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከአብርሃም ዘር የሆንኩ የብንያም ነገድ ነኝ። #ፊል. 3፥5። 2እግዚአብሔር አስቀድሞ የመረጠውን ሕዝብ አልጣለውም፤ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ኤልያስ ምን እንዳለ አታስታውሱምን? ደግሞስ ኤልያስ የእስራኤልን ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ምን ብሎ እንደ ከሰሰ አታውቁምን? 3በዚያን ጊዜ ኤልያስ “ጌታ ሆይ! ነቢያትህን ገደሉ፤ መሠዊያዎችህን አፈረሱ፤ እኔ ብቻ ቀረሁ፤ እኔንም ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ” ብሎ ነበር። #1ነገ. 19፥10፤14። 4ነገር ግን እግዚአብሔር ምን ብሎ መለሰለት? “ባዓል ለተባለው ጣዖት ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለራሴ አስቀርቻለሁ” ብሎታል። #1ነገ. 19፥18። 5በአሁኑም ዘመን ቢሆን፥ በጸጋ ተመርጠው የቀሩ ጥቂት እስራኤላውያን አሉ። 6ምርጫው በጸጋ ከሆነ በሥራ አይደለም ማለት ነው፤ በሥራ ከሆነማ፥ ጸጋ ዋጋቢስ በሆነ ነበር።
7ታዲያ፥ ውጤቱ ምን ሆነ? እስራኤላውያን የፈለጉትን አላገኙም፤ የተመረጡት ግን የፈለጉትን አገኙ፤ የቀሩት ልባቸውን አደነደኑ። 8ይህም “እግዚአብሔር ልቡናቸውን አደነዘዘ፤ ስለዚህ እስከ ዛሬ ድረስ በዐይናቸው አያዩም፤ በጆሮአቸውም አይሰሙም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። #ዘዳ. 29፥4፤ ኢሳ. 29፥10። 9ዳዊትም፦
“ማእዳቸው የሚይዝ ወጥመድ፥
የሚጥል ጒድጓድ ሆኖ ያሠቃያቸው!
ያደረጉት ክፋት በራሳቸው ላይ ይድረስ!
10ዐይናቸው እንዳያይ ይጨልም፤
ወገባቸውም በችግር ሁልጊዜ ይጒበጥ” ብሎአል። #መዝ. 69፥22-23።
11እስቲ፥ እንደገና ልጠይቅ፤ አይሁድ የወደቁት ዳግመኛ እንደማይነሡ ሆነው ነውን? አይደለም! በአይሁድ በደል ምክንያት አሕዛብ መዳንን አገኙ፤ ይህም የሆነው አይሁድ በአሕዛብ እንዲቀኑ ለማድረግ ነው። 12የአይሁድ በደል ለዓለም ብዙ በረከት አስገኝቶአል፤ የእነርሱም ውድቀት ለአሕዛብ በረከት ሆኖአል፤ አይሁድ ቢድኑማ ኖሮ በረከቱ ምን ያኽል ብዙ በሆነ ነበር!
የአሕዛብ መዳን
13አሁን እንግዲህ የምናገረው ለእናንተ ለአሕዛብ ነው፤ የአሕዛብም ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን በአገልግሎቴ ክብር ይሰማኛል፤ 14ይህንንም ማድረጌ የሥጋ ዘመዶቼ የሆኑትን አይሁድ ለማስቀናት ነው፤ በዚህም ሁኔታ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዶቹን ለማዳን እችል ይሆናል በማለት ነው። 15እግዚአብሔር እነርሱን በጣላቸው ጊዜ ሌላው የዓለም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቀ እግዚአብሔር እነርሱን በሚቀበላቸው ጊዜ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ይህማ ከሞት እንደ መነሣት ያኽል ነው!
16ከአንድ ዐይነት ሊጥ የመጀመሪያው ክፍል የተቀደሰ ከሆነ ሊጡ በሙሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ እንዲሁም የአንድ ዛፍ ሥሩ የተቀደሰ ከሆነ ቅርንጫፎቹም የተቀደሱ ይሆናሉ። 17እንደ ጓሮ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆኑ አይሁድ ተቈርጠው ቢወድቁና እናንተ እንደ ዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆናችሁ አሕዛብ በቦታቸው ተተክታችሁ የእነርሱን ሀብትና በረከት ተካፋዮች ብትሆኑ፥ 18እናንተ አሕዛብ እንደ ቅርንጫፍ ተቈርጠው በወደቁት አይሁድ ላይ አትታበዩ፤ ብትታበዩ ግን እናንተ ቅርንጫፎች ብቻ በመሆናችሁ ሥሩ እናንተን ይሸከማችኋል እንጂ እናንተ ሥሩን የማትሸከሙ መሆናችሁን አስታውሱ።
19ነገር ግን “ቅርንጫፎች ተሰብረው የወደቁት እኔ በቦታቸው እንድተካ ነው” ትሉ ይሆናል። 20አባባላችሁስ ልክ ነው፤ ነገር ግን እነርሱ ተቈርጠው የወደቁት ባለማመናቸው ሲሆን እናንተ ጸንታችሁ የቆማችሁት በማመናችሁ ነው፤ ታዲያ፥ መፍራት እንጂ መታበይ አይገባችሁም። 21እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት አይሁድ ካልራራላቸው ለእናንተም አይራራላችሁም። 22እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና አስፈሪነት ተመልከቱ፤ አስፈሪነቱን የሚያሳየው በወደቁት ላይ ሲሆን ቸርነቱን የሚያሳየው ግን ለእናንተ ነው፤ ይህንንም የሚያደርገው እርሱን በማመን ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው፤ ባትጸኑ ግን እናንተም ተቈርጣችሁ ትወድቃላችሁ። 23አይሁድ አለማመናቸውን ቢያስወግዱ ወደ ቀድሞው ቦታቸው ይመለሳሉ፤ እግዚአብሔር ወደ ቀድሞው ቦታቸው ሊመልሳቸው ይችላል። 24እናንተ አሕዛብ ግን በተፈጥሮ የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ሆናችሁ ሳለ ያለ ቦታችሁ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ መተከል ከቻላችሁ እነዚህ በተፈጥሮአቸው የጓሮ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆኑት አይሁድማ ወደ ቀድሞው ቦታቸው ተመልሰው መተከል እንዴት አይቻላቸውም!
የእግዚአብሔር ምሕረት ለሁሉም መሆኑ
25ወንድሞቼ ሆይ! “ዐዋቂዎች ነን” ብላችሁ አትመኩ፤ የምነግራችሁ አንድ ምሥጢር አለ፤ ይኸውም የእስራኤላውያን እምቢተኛነት ለዘለቄታው ሳይሆን አሕዛብ ሁሉ በሙላት ወደ እግዚአብሔር እስኪመጡ ድረስ መሆኑን ነው። 26እንግዲህ በዚህ ዐይነት እስራኤላውያን ሁሉ ይድናሉ። ስለዚህም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፦
“አዳኝ ከጽዮን ይመጣል፤
ከያዕቆብም ዘር ሁሉ ክፋትን ያስወግዳል፤ #ኢሳ. 59፥20።
27ኃጢአታቸውንም በደመሰስኩላቸው ጊዜ
ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው።” #ኤር. 31፥33-34።
28እስራኤላውያን የወንጌልን ቃል ባለመቀበላቸው ስለ እናንተ ስለ አሕዛብ ጥቅም የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነዋል፤ ነገር ግን በምርጫ በኩል በነገድ አባቶች ምክንያት የእግዚአብሔር ወዳጆች ናቸው። 29እግዚአብሔር ከመረጠና ጸጋውን ከሰጠ በኋላ ባደረገው ነገር ሐሳቡን አይለውጥም። 30እናንተ አሕዛብ ቀድሞ ለእግዚአብሔር የማትታዘዙ ነበራችሁ፤ አሁን ግን አይሁድ ባለመታዘዛቸው ምክንያት እናንተ የእግዚአብሔርን ምሕረት አገኛችሁ። 31እናንተ ምሕረትን ባገኛችሁበት ዐይነት እነርሱም ምሕረትን እንዲያገኙ እነርሱ አሁን ለእግዚአብሔር የማይታዘዙ ሆነዋል። 32እግዚአብሔር ምሕረቱን ለሰው ሁሉ ለማሳየት ሲል ሰዎችን ሁሉ የእምቢተኛነታቸው እስረኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው።
ለእግዚአብሔር የቀረበ ምስጋና
33የእግዚአብሔር ባለጸግነትና ጥበብ ዕውቀትም እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ የማይመረመር፥ መንገዱም የማይታወቅ ነው። #ኢሳ. 55፥8።
34“የጌታን አሳብ የሚያውቅ ማነው?
የእርሱ አማካሪ የሚሆንስ ማነው?
35ለእግዚአብሔር የሚያበድርና
ያበደረውንም የሚወስድ ማነው?”
#
ኢዮብ 41፥11። 36ሁሉም ነገር የተገኘው ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱ ነው፤ ለዘለዓለም ክብር ለእርሱ ይሁን! አሜን! #1ቆሮ. 8፥6።
Currently Selected:
ወደ ሮም ሰዎች 11: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997