የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ሮም ሰዎች 16

16
ሰላምታ
1ፌቤ በክንክሪያ ከተማ ቤተ ክርስቲያንን የምታገለግል ታማኝ እኅታችን መሆንዋን እንድታውቁ እወዳለሁ። 2እርስዋ እኔንና ሌሎችንም ብዙ ሰዎች የረዳች ስለ ሆነች ምእመናን እንግዶችን መቀበል እንደሚገባቸው ዐይነት በጌታ ስም ተቀብላችሁ በሚያስፈልጋት ነገር ሁሉ እንድትረዱአት ዐደራ እላችኋለሁ።
3በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ተባባሪዎቼ ለሆኑት ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ #ሐ.ሥ. 18፥2። 4እነርሱ በእኔ ምትክ ለመሞት እንኳ የተዘጋጁ ነበሩ፤ በዚህም ዘወትር አመሰግናቸዋለሁ፤ እኔም ብቻ ሳልሆን ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የተመለሱ ምእመናን አብያተ ክርስቲያን ጭምር ያመሰግኑአቸዋል። 5በእነርሱ ቤት ለጸሎት ለሚሰበሰቡት ምእመናንም ሰላምታ አቅርቡልኝ።
በእስያ ክፍለ ሀገር በመጀመሪያ በክርስቶስ ላመነውና ለምወደው ለኤጴኔጦስ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 6ለእናንተ ብዙ ለደከመችው ለማርያም ሰላምታ አቅርቡልኝ። 7ከእኔ ጋር ታስረው ለነበሩና በሐዋርያትም መካከል ታዋቂዎች ለነበሩት አይሁድ ዘመዶቼ፥ ለአንድሮኒቆስና ለዩኒያስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱ በክርስቶስ በማመን እኔን ይቀድሙኛል። #16፥7 ዩኒያስ፦ አንዳንድ የብራና ጽሑፎች “ዩሊያ” ይላሉ።
8በጌታ ለምወደው ለአምጵልያቶስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ 9በክርስቶስ ሥራ ተባባሪያችን ለሆነው ለዑርባኖስና ለምወደውም ለእስጣኩስ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 10በክርስቶስ መሆኑ ተፈትኖ ለተመሰከረለት ለአጴሊስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ ከአርስጦቡሎስ ቤተሰብ ለሆኑትም ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ 11ለአይሁዳዊው ዘመዴ ለሄሮድዮን ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ ከናርሲሰስ ቤተ ሰዎች በጌታ ላመኑት ሰላምታ አቅርቡልኝ።
12በጌታ አገልግሎት ለሚደክሙት ለትሩፋይናና ለትሩፎሳ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጌታ አገልግሎት እጅግ ለደከመችውና በክርስቶስ ለምወዳት ለፔርሲስ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 13ጌታን በማገልገል በጣም ለታወቀው ለሩፎስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እኔን እንደ ልጅዋ ትወደኝ ለነበረችው ለእናቱም ሰላምታ አቅርቡልኝ። #ማር. 15፥21። 14ለአስንክሪቶስና ለፍሌጎን፥ ለሄርሜስም፥ ለፓትሮባስም፥ ለሄርማስም፥ ከእነርሱም ጋር ላሉ ወንድሞች ሰላምታ አቅርቡልኝ። 15ለፊሎሎጎስ፥ ለዩልያ፥ ለኔርያና ለእኅቱም ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እንዲሁም ለኦሉምፓስና ከእነርሱም ጋር ላሉ ምእመናን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። 16በተቀደሰ መሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
የመጨረሻ ምክር
17ወንድሞች ሆይ! ለተቀበላችሁት ትምህርት ተቃዋሚዎች በመሆን በመካከላችሁ መከፋፈልንና ችግርን ከሚያመጡ ሰዎች ተጠንቀቁ፤ ከእነርሱም ራቁ! 18እንደእነዚህ ዐይነቶቹ ሰዎች ራሳቸውን እንጂ ጌታችንን ክርስቶስን አያገለግሉም። በለዘቡና በሚያቈላምጡ ቃላት የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ።
19ለወንጌል ቃል ታዛዦች መሆናችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ ስለ ታወቀ ደስ ያለኝ ቢሆንም፥ ነገር ግን ለመልካም ነገር ጥበበኞች ለክፉ ነገር ግን የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። 20ይህን ብታደርጉ የሰላም አምላክ ፈጥኖ ሰይጣንን በእግራችሁ ሥር ይቀጠቅጥላችኋል።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
21የሥራ ተባባሪዬ ጢሞቴዎስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እንዲሁም አይሁድ ዘመዶቼ የሆኑት ሉቂዮስና ኢያሶን ሶሲጳጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። #ሐ.ሥ. 16፥1።
22ይህን መልእክት የጻፍኩ እኔም ጠርጥዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ።
23እኔንና በዚህ ያለውን መላ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተናግደው ጋይዮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ የከተማይቱ በጅሮንድ የሆነው ኤራስጦስ፥ ወንድማችንም ቋርጦስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። #ሐ.ሥ. 19፥29፤ 1ቆሮ. 1፥14፤ 2ጢሞ. 4፥20። [ 24የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን! አሜን።]
የምስጋና ጸሎት
25እኔ በማበሥረው የምሥራች ቃል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚተላለፈው መልእክትና ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተደብቆ በቈየው፥ አሁን ግን በተገለጠው የእውነት ምሥጢር አማካይነት እርሱ በእምነታችሁ እንድትቆሙ ሊያደርጋችሁ ይችላል። 26አሁን ግን ይህ እውነት ተገልጦአል፤ በዘለዓለማዊው አምላክ ትእዛዝ ሁሉም አምነው እንዲታዘዙ በነቢያት መጻሕፍት አማካይነት ሕዝቦች ሁሉ እንዲያውቁት ተደርጓል።
27እርሱ ብቻ ጥበብ ላለው ለአንድ አምላክ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ምስጋና ይሁን! አሜን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

Free Reading Plans and Devotionals related to ወደ ሮም ሰዎች 16

YouVersion የእርስዎን ተሞክሮ ግላዊ ለማድረግ ኩኪዎችን ይጠቀማል። የእኛን ድረ ገጽ በመጠቀም፣ በግለሰብነት መመሪያችን ላይ እንደተገለጸው የእኛን የኩኪዎች አጠቃቀም ተቀብለዋል