ትንቢተ ዘካርያስ 6
6
ነቢዩ ዘካርያስ ስለ አራቱ ሠረገሎች ያየው ራእይ
1በሌላም ራእይ አራት ሠረገሎች ከሁለት የነሐስ ተራራዎች መካከል ሲወጡ አየሁ። 2የመጀመሪያው ሠረገላ የሚሳበው በቀያይ ፈረሶች ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ በጥቋቊር ፈረሶች ነበር፤ #ራዕ. 6፥4-5። 3ሦስተኛው የሚሳበው በነጫጭ ፈረሶች ሲሆን አራተኛው ቡራቡሬ በሆኑ ፈረሶች ነበር፤ ሁሉም ኀይለኞች ነበሩ። #ራዕ. 6፥2። 4ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውንም መልአክ “ጌታዬ እነዚህ ሠረገሎች የምን ምሳሌ ናቸው?” ብዬ ጠየቅሁት።
5እርሱም “እነዚህ አራቱ ነፋሳት ናቸው፤ ቆመው ከሚያገለግሉበት ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት አሁን ገና መውጣታቸው ነው” አለኝ። #ራዕ. 7፥1።
6በጥቋቊር ፈረሶች ይሳብ የነበረው ሠረገላ ወደ ሰሜን፥ በነጫጭ ፈረሶች ይሳብ የነበረው ወደ ምዕራብ፥ በቡራቡሬ ፈረሶች ይሳብ የነበረው ወደ ደቡብ አገሮች ይሄዱ ነበር። 7ኀይለኞቹ ፈረሶች በወጡ ጊዜ ምድርን ለመቃኘት ተጣድፈው ነበር፤ መልአኩም “ሂዱ፤ ምድርን ቃኙ!” አላቸው፤ እነርሱም ምድርን ቃኙ። 8ከዚህ በኋላ መልአኩ “ወደ ሰሜን አገሮች የሄዱት ፈረሶች የእግዚአብሔርን ቊጣ እንዲበርድ አደረጉ” ሲል ወደ እኔ ጮኸ።
ኢያሱን ቀብቶ ለማንገሥ የተሰጠ ትእዛዝ
9እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 10“ሔልዳይ፥ ጦቢያና ይዳዕያ የተባሉት ስደተኞች የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሳትዘገይ አሁኑኑ ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ሂድ፤ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከባቢሎን የተመለሱ ምርኮኞች ናቸው፤ 11እነርሱ ከሰጡት ብርና ወርቅ ዘውድ ሠርተህ በሊቀ ካህናቱ በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ራስ ላይ ድፋለት። 12የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፦ ‘ቅርንጫፉ በቦታው ስለሚስፋፋ ቅርንጫፍ የሚባል ስም ያለው ይህ ሰው ነው። ባለበት ስፍራ በቅሎ ገናና ይሆናል፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ እንደገና ይሠራል፤ #ኤር. 23፥5፤ 33፥15፤ ዘካ. 3፥8። 13የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚመራ እርሱ ነው፤ የንጉሥነትን ክብር በመቀዳጀት በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ይገዛል፤ አንድ ካህን በዙፋኑ አጠገብ ይቆማል፤ ሁለቱም አብረው በስምምነትና በሰላም ይሠራሉ።’ 14ዘውዱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሔሌም ለተባለ ለሔልዳይ፥ ለጦቢያ፥ ለይዳዕያና ለሰፎንያስ ልጅ ሔን ለኢዮስያስ ክብር መታሰቢያ ሆኖ ይቀመጣል።”
15በዚያን ጊዜ በሩቅ የሚኖሩ ሰዎች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሲታደስ ለመርዳት ይመጣሉ። ቤተ መቅደሱ በታደሰ ጊዜ እኔን ወደ እናንተ የላከኝ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መሆኑን ታውቃላችሁ። ይህም ሁሉ የሚፈጸመው ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ ቃል ፍጹም ታዛዦች የሆናችሁ እንደ ሆነ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 6: አማ05
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997