የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16

16
ለቅዱሳን የተደረገ የገንዘብ መዋጮ
1 # ሮሜ 15፥25፤26። አሁን ደግሞ ለቅዱሳን የሚደረገውን የገንዘብ መዋጮ በተመለከተ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በሰጠሁት መመሪያ መሠረት አድርጉ። 2እኔ በምመጣበት ጊዜ የገንዘብ መዋጮ እንዳይደረግ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ እንደገቢው መጠን በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እየለየ ያስቀምጥ፤ 3እኔ ስመጣ እናንተ ለመረጣችኋቸው ሰዎች የመሸኛ ደብዳቤ ሰጥቼ ስጦታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ። 4የእኔ መሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ አብረውኝ ይሄዳሉ።
የጳውሎስ ዕቅድ
5 # የሐዋ. 19፥21። በመቄዶንያ በኩል ለመሄድ ስላቀድኩ በዚያ ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 6ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጉዞዬ እንድትረዱኝ፥ እናንተ ጋር እቆይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋር እሰነብት ይሆናል። 7አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ ጌታ ቢፈቅድ ረዘም ላለ ጊዜ እናንተ ዘንድ ለመሰንበት ተስፋ አደርጋለሁ። 8#ዘሌ. 23፥15-21፤ ዘዳ. 16፥9-11።#የሐዋ. 19፥8-10።ነገር ግን እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቆያለሁ፤ 9ምክንያቱም ታላቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤ ተቃዋሚዎችም ብዙ ናቸው።
10 # 1ቆሮ. 4፥17። ጢሞቴዎስ ወደ እናንተ ከመጣ፥ እርሱም እንደ እኔ የጌታን ሥራ የሚሠራ ነውና፥ አብሮአችሁ ያለ ሥጋት እንዲቀመጥ አድርጉ። 11ስለዚህ ማንም አይናቀው፤ በሰላም ወደ እኔ እንዲመለስ እርዱት፤ መመለሱንም ከወንድሞች ጋር እየጠበቅን ነው።
12ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ደግሞ፥ ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ አጥብቄ ለምኜው ነበር፤ እርሱ ግን አሁን ለመምጣት አልፈለገም፤ ሲመቸው ግን ይመጣል።
13ንቁ፤ በእምነት ጽኑ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ፤ 14የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ።
15 # 1ቆሮ. 1፥16። ወንድሞች ሆይ፥ የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች በአካይያ የመጀመሪያዎቹ አማኞች እንደሆኑና ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደሰጡ ታውቃላችሁ። 16እንደ እነርሱ ላሉትና ከእነርሱም ጋር በአገልግሎት ለሚደክሙ ሁሉ ታዘዙ። 17በእስጢፋኖስ፥ በፈርዶናጥስና በአካይቆስ መምጣት ደስ ብሎኛል፤ ምክንያቱም እናንተ እዚህ ባለመኖራችሁ የጐደለኝን አሟልተዋል፤ 18የእኔንም የእናንተንም መንፈስ አሳርፈዋታልና። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች እውቅና ይገባቸዋል።
የመሰናበቻ ቃል
19 # የሐዋ. 18፥2። በእስያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ፥ በቤታቸውም ያለችው ቤተ ክርስቲያን የከበረ ሰላምታ በጌታ ያቀርቡላችኋል። 20ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቅርቡላችኋል። እርስ በርሳችሁ በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ።
21እኔ ጳውሎስ፥ ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ ጽፌላችኋለሁ። 22ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ! ና! 23የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 24ፍቅሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ