የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6

6
በማያምኑ ዳኞች ፊት መፋረድ እንደማይገባ
1ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ጥል ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በአሕዛብ ፊት ሊፋረድ እንዴት ይደፍራል? 2ወይስ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፥ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ ያቅታችኋልን? 3እለታዊው የሕይወት ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? 4እንግዲህ ለዚህ መሰል ጉዳይ ፍርድ ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ እንዴት ታስቀምጣላችሁ? 5እንድታፍሩ ስል ይህን እላለሁ። ኧረ ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው አይገኝምን? 6ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋል!
7እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በእርስ ሙግት በመካከላችሁ መፍጠር ለእናንተ ሽንፈት ነው። ይልቅስ ብትበደሉ አይሻልምን? እንዲሁም ብትታለሉ አይሻልምን? 8ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ፤ ታታልሉማላችሁ፤ ያውም ወንድሞቻችሁን።
9ወይስ ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? አትሳሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ፥ 10ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 11ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።
ሰውነትን ለእግዚአብሔር ክብር ማዋል እንደሚገባ
12 # 1ቆሮ. 10፥23። “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤” ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፤ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። 13“ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤” እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሰውነት ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሰውነት ነው፤ 14እግዚአብሔርም ጌታን ከሞት አስነሣ፥ እኛንም በኀይሉ ያስነሣናል። 15ሰውነታችሁ የክርስቶስ አካል እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን የአካል ክፍሎች ወስጄ የአመንዝራ ክፍሎች አካል ላድርጋቸውን? ፈጽሞ ከቶ አይገባም። 16#ዘፍ. 2፥24።ወይስ ከአመንዝራ ጋር የሚገናኝ አንድ አካል እንዲሆን አታውቁምን? “ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤” ተብሏልና። 17ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። 18ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሰውነቱ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሰውነቱ ላይ ኃጢአትን ይሠራል። 19#1ቆሮ. 3፥16፤ 2ቆሮ. 6፥16።ወይስ ሰውነታችሁ፥ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት፥ በውስጣችሁም የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መሆኑን አታውቁም? እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም። 20በዋጋ ተገዝታችኋል፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ