1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7
7
ስለ ጋብቻ
1የጻፋችሁልኝን ነገር በተመለከተ፥ ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው። 2ነገር ግን ከዝሙት ለመራቅ እያንዳንዱ ወንድ ለራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዱዋም ሴት ለራስዋ ባል ይኑራት። 3ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፤ እንደዚሁም ደግሞ ሚስት ለባሏ። 4ሚስት በገዛ ሰውነቷ ላይ ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባሏ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሰውነቱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። 5ለጸሎት ለመትጋት ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ እንዲሁም ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ አብራችሁ ሁኑ። 6ዳሩ ግን ይህን እንደ ፈቃድ እላለሁ እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም። 7ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፤ አንዱ እንደዚህ ሌላውም እንደዚያ ዓይነት።
8ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤ 9ነገር ግን በመሻት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ካልቻሉ ያግቡ።
10 #
ማቴ. 5፥32፤ 19፥9፤ ማር. 10፥11፤12፤ ሉቃ. 16፥18። ላገቡት ግን የምሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፤ ይህም ትእዛዝ የጌታ ነው እንጂ የእኔ አይደለም፤ ያገባች ሴት ከባሏ አትለይ፤ 11ብትለይም ሳታገባ ለብቻዋ ትኑር፤ ወይም ከባሏ ጋር ትታረቅ፤ እንዲሁም ባል ሚስቱን አይፍታ።
12ሌሎችንም፥ ጌታም አይደለም፥ እኔ እላለሁ፤ ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር፥ እርሷም ከእርሱ ጋር ለመኖር ብትስማማ፥ አይፍታት፤ 13ያላመነ ባል ያላት ሚስትም ብትኖር ይህ ከእርሷ ጋር ለመኖር ቢስማማ፥ አትተወው። 14ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሶአልና፤ ያላመነችም ሚስት በባሏ ተቀድሳለች፤ እንደዚህ ካልሆነ ግን፥ ልጆቻችሁ ርኩሳን ናቸው፤ እንደዚህ ከሆነ ግን የተቀደሱ ናቸው። 15የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እኅት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል። 16ሚስት ሆይ! ባልሽን ታድኚ እንደሆን ምን ታውቂያለሽ? ወይስ ባል ሆይ! ሚስትህን ታድን እንደሆንህ ምን ታውቃለህ?
እግዚአብሔር ያዘዘው ሕይወት
17እያንዳንዱ ጌታ በሰጠውና እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያን ሁሉ የሰጠሁት መመሪያ ይህ ነው። 18#1መቃ. 1፥15።ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደሆነ፥ ወደ አለመገረዝ አይመለስ፤ ማንም ሳይገረዝ ተጠርቶ እንደሆነ፥ መገረዝን አይፈልግ። 19መገረዝ ቢሆን አለመገረዝም ቢሆን ምንም ማለት አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ። 20እያንዳንዱ ሲጠራ በነበረበት ሁኔታ ይኑር። 21ባርያ ሆነህ ተጠርተህ እንደሆነ አይገድህም፤ ነጻ ልትወጣ ቢቻልህ ግን ነጻነትን ተቀበል። 22ባርያ ሆኖ ሳላ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ ሳለ የተጠራ የክርስቶስ ባርያ ነው። 23በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባርያዎች አትሁኑ። 24ወንድሞች ሆይ! እያንዳንዱ በተጠራ ጊዜ የነበረበት ሁኔታ ምንም ይሁን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር።
ስላላገቡና ስለመበለቶች
25ደናግልን በተመለከተ የጌታ ትእዛዝ የለኝም፤ ነገር ግን በጌታ ምሕረት የታመንሁ እሆን ዘንድ ምክሬን እለግሳችሀለሁ፤ 26እንግዲህ አሁን ላለንበት ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። 27ሚስት አግብተህ እንደሆንህ መፋታትን አትሻ፤ ሚስት አላገባህ እንደሆንህ ለማግባት አትፈልግ። 28ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይገጥማቸዋል፤ እኔም ከዚያ ባስጣልኳችሁ ነበር። 29ዳሩ ግን ወንድሞች ሆይ! ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፤ 30የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ 31በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።
32ነገር ግን ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ 33ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንደሚያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፤ 34ልቡም ተከፍሎአል። ያላገባች ሴትና ድንግል በሰውነት በመንፈስም እንድትቀደስ የጌታን ነገር ታስባለች፤ ያገባች ግን ባሏን እንዴት ደስ እንደምታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች። 35ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአግባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም ለጌታ በጽናት እንድታገለግሉ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።
36ዳሩ ግን አንድ ሰው በእጮኛው ላይ መልካም አለማድረጉን ቢያስብ፥ እጮኛውም ዕድሜዋ ለጋብቻ ከደረሰ፥ ሊያገባም ከፈቀደ፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ። 37ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ምንም አስገዳጅ የለበትም፤ ፍላጎቱን ለመቆጣጠር ከቻለና እጮኛውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ። 38ስለዚህ ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ፥ ያላገባም የተሻለ አደረገ።
39ሚስት ባሏ በሕይወት እስካለ የታሰረች ናት፤ ባሏ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት። 40እንደ እኔ አስተያየት ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት፤ እኔም የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል።
Currently Selected:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ