2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 1
1
ዳዊት የሳኦልን ሞት ሰማ
1 #
1ሳሙ. 30፥17-20፤ 31፥1-13። ሳኦል ከሞተ በኋላ፥ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ ሲመለስ፥ ሁለት ቀን በጺቅላግ ቆየ። 2በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ የተቀደደ ልብስ የለበሰ፥ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ። ወደ ዳዊት መጥቶም በግምባሩ በመደፋት እጅ ነሣ። 3ዳዊትም፥ “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፥ “ከእስራኤላውያን ሰፈር አምልጬ መጣሁ” በማለት መለሰለት። 4ዳዊትም፥ “እስቲ ምን ነገር እንደተፈጠረ ንገረኝ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “ሰዎቹ ከጦርነቱ ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል፤ ሞተዋልም፤ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ። 5ከዚያም ዳዊት ወሬውን የነገረውን ወጣት፥ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው። 6#2ሳሙ. 4፥10፤ 1ሳሙ. 31፥1-4፤ 1ዜ.መ. 10፥1-4።ወሬ ነጋሪው ወጣትም እንዲህ አለ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተመርኩዞ ሳለ፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከትለው ደረሱበት፤ 7ወደ ኋላውም ዞር ሲል አየኝና ጠራኝ፤ እኔም፥ ‘እነሆ አለሁ!’ አልኩት። 8እርሱም፥ ‘አንተ ማን ነህ?’ ብሎ ጠየቀኝ፤ እኔም ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስኩለት። 9ከዚያም፥ ‘እኔ የሞት ጣር ይዞኛል፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ። 10እኔም ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፥ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና በክንዱ ላይ የነበረውን አንባር ወስጄ፥ እነሆ ለጌታዬ አምጥቻለሁ።”
11 #
2ሳሙ. 13፥31። ከዚያም ዳዊት ልብሱን ቀደደ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሁሉ እንደዚሁ አደረጉ። 12#1ሳሙ. 31፥13።የወደቁት በሰይፍ ነበርና፥ ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፥ ለጌታ ሠራዊትና ለእስራኤል ቤትም አዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። 13ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት፥ “ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፥ “እኔ የአንድ መጻተኛ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ። 14#1ሳሙ. 10፥1፤ 24፥7፤ መዝ. 105፥15።ዳዊትም፥ “ታዲያ ጌታ የቀባውን ለማጥፋት እጅህን ስታነሣ እንዴት አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው። 15ከዚህ በኋላ ዳዊት ከጉልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፥ “በል ቅረብና ግደለው!” አለው። እርሱም መታው፤ ገደለውም። 16ዳዊትም፥ “ ‘ጌታ የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል የገዛ አፍህ መስክሮብሃልና፥ ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው።
የዳዊት የኀዘን እንጉርጉሮ
17ዳዊትም በሳኦልና በልጁ በዮናታን ሞት ምክንያት ይህን የኀዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤ 18#ኢያ. 10፥13።#ኢያ. 10፥13።የይሁዳንም ሕዝብ እንዲያስተምሩ አዘዘ፤ እነሆ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል።
19“እስራኤል ሆይ፤ ክብርህ በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል!
ኀያላኑ እንዴት ወደቁ!
20 #
መሳ. 16፥23፤ 1ሳሙ. 31፥9፤ ሚክ. 1፥10። የፍልስጥኤም ቆነጃጅት ደስ እንዳይላቸው፤
ያልተገረዙት ሴት ልጆች እልል እንዳይሉ፤
ይህን በጌት አትናገሩ፤
በአስቀሎናም መንገዶች አታውጁ፤
21 #
ዘፍ. 27፥28። እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፤
በዚያ የኀያሉ ሰው ጋሻ ረክሶአልና፤
የሳኦል ጋሻ በዘይት መወልወሉ ቀርቶአልና፤
ጠልም ሆነ ዝናብ አይውረድባችሁ፤
የቁርባን እህል የሚያበቅሉም እርሻዎች አይኑራችሁ።
22 #
1ሳሙ. 14፥47። ከሞቱት ሰዎች ደም፥ ከኀያላኑም ሥብ፥
የዮናታን ቀስት ተመልሳ አልመጣችም፤
የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰችም።
23ሳኦልና ዮናታን፥ የተዋደዱና የተስማሙ፤
በሕይወትም ሆነ በሞት ያልተለያዩ፤
ከንስርም ይልቅ የፈጠኑ፥
ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ።
24እናንት የእስራኤል ቆነጃጅት ሆይ!
ሐምራዊ ቀሚስና ቀጭን ፈትል ላለበሳችሁ፥
ልብሶቻችሁንም በወርቀ ዘቦ ላስጌጠላችሁ፥
ለሳኦል አልቅሱ።
25ኀያላን እንዴት በጦርነት ወደቁ!
ዮናታን በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል።
26 #
1ሳሙ. 18፥1-4። ወንድሜ ዮናታን ሆይ፤ እኔ ስለ አንተ አዘንሁ፤
አንተ ለእኔ እጅግ ውድ ነበርህ፤
ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበረ፤
ከሴት ፍቅርም ይልቅ የበረታ ነበር።
27ኀያላን እንዴት ወደቁ! የጦር መሣሪያዎቹስ እንዴት ጠፉ!”
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ