2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19
19
1ንጉሡም እጅግ አዘነ፤ በቅጽር በሩ ዐናት ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! በአንተ ፈንታ ምነው እኔ በሞትሁ ኖሮ! አቤሴሎም፥ ልጄን፥ ወየው ልጄን!” ይል ነበር። 2ለኢዮአብ፥ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰና እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው። 3ንጉሡ፥ “ስለ ልጁ አዝኖአል” መባሉን በዚያ ቀን ሠራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፥ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሠራዊት ዘንድ ወደ ኀዘን ተለውጦ ዋለ። 4በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ድምፅ ሳያሰማ ወደ ከተማ ገባ። 5#2ሳሙ. 15፥30።ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፥ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ፥ ልጄን! ልጄን!” እያለ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። 6ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፥ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የዕቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍረሃቸዋል። 7የሚጠሉህን ትወዳለህ፤ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳልሆኑ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን አልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ። 8በል አሁን ተነሥተህ ውጣና አገልጋዮችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው አብሮህ እንደማይሆን በጌታ ስም እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያሰከትልብሃል።” 9ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፥ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጦአል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ።
ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ
በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ወደየቤታቸው ሸሽተው ነበር። 10በመላው የእስራኤል ነገዶችም፥ ሕዝቡ እንዲህ እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር፤ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ የታደገን እርሱ ነው፤ አሁን ግን በአቤሴሎም ምክንያት ከአገር ሸሽቶ ሄዶአል፤ 11በላያችን ሆኖ እንዲገዛን የቀባነው አቤሴሎም ደግሞ በጦርነት ሞቷል፤ ታዲያ ስለ ንጉሡ የመመለስ ጉዳይ ለምንድን ነው ዝም የምትሉት?”
12ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል ሽማግሌዎችን እንዲህ በሏቸው አለ፤ ‘በመላው እስራኤል የሚባለው ሁሉ ለንጉሡ ባለበት የደረሰው ስለሆነ፥ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ? 13እናንተ የዐጥንቴ ፍላጭ፥ የሥጋዬ ቁራጭ ወንድሞቼ ናችሁ፤ ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?’ 14#2ሳሙ. 17፥25፤ 20፥4።አማሳይንም፥ ‘አንተስ የዐጥንቴ ፍላጭ፥ የሥጋዬ ቁራጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ በኢዮአብ ምትክ የሠራዊቴ አዛዥ ባላደርግህ፥ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፥ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ ብላችሁ ንገሩት።” 15እርሱም የይሁዳን ሰዎች ልብ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ ማረከው፤ እነርሱም “አንተም አገልጋዮችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ላኩበት። 16ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳም ሰዎች ንጉሡን ተቀብለው ዮርዳኖስን ለማሻገር እስከ ጌልገላ ድረስ መጥተው ነበር። 17#2ሳሙ. 16፥5-13።የባሑሪም ሰው የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሺምዒ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ሆኖ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ፈጥኖ ሄደ። 18#2ሳሙ. 16፥1-4፤ 19፥25-31።ከእርሱም ጋር አንድ ሺህ ብንያማውያን፥ እንዲሁም የሳኦል ቤተሰብ አገልጋይ ጺባ ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከሃያ አሽከሮቹ ጋር ሆኖ አብረውት ነበሩ። ከዚያም ንጉሡ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ፈጥነው ተሻገሩ። 19#2ሳሙ. 16፥13፤ ዘፀ. 22፥27፤ 1ነገ. 2፥8-9።የንጉሡን ቤተሰብ ለማምጣትና እርሱ የሚፈልገውንም ሁሉ ለማድረግ ዮርዳኖስን ተሻገሩ። የጌራ ልጅ ሳሚ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ በንጉሡም ፊት ተደፍቶ፥ 20እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ በደሌን አትቁጠርብኝ፥ ጌታዬ ንጉሡ፥ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀነ አገልጋይህ የበደልሁህን አታስብብኝ፥ በልብህም አታኑርብኝ። 21እኔ አገልጋይህ ኃጢአት መሥራቴን አውቃለሁና፤ እነሆ፥ ዛሬ ግን ጌታዬ ንጉሡን ለመቀበል ከዮሴፍ ቤት ሁሉ የመጀመሪያ ሆኜ መጥቻለሁ።” 22ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ፥ “ሺምዒ በጌታ የተቀባውን የረገመ ስለሆነ፥ መሞት አይገባውምን?” አለ። 23#2ሳሙ. 16፥9-10፤ 1ሳሙ. 11፥13፤ 1ነገ. 2፥8-9፤36-46።ዳዊትም፥ “እናንት የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬ ማንስ ቢሆን በእስራኤል ዘንድ መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ። 24ስለዚህ ንጉሡ ሺምዒን፥ “አትሞትም” አለው፤ ይህንንም ንጉሡ በመሐላ አጸናለት። 25የሳኦል ልጅ መፊቦሼትም ንጉሡን ለመቀበል ወረደ። ንጉሡ ከተሰደደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተመለሰበት ዕለት ድረስ ለእግሩ መጫሚያ አላደረገም፤ ጢሙን አልተላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም ነበር። 26#2ሳሙ. 16፥3።እርሱም ንጉሡን ለመቀበል ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፥ “መፊቦሼት፥ አብረኸኝ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 27#2ሳሙ. 9፥2-13።እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ ሽባ በመሆኔ፥ ‘ከንጉሡ ጋር መሄድ እንድችል አህያዬ ይጫንልኝና ልቀመጥበት’ ብዬ ነበር፤ ይሁን እንጂ አገልጋዬ አታለለኝ። 28በጌታዬ በንጉሡ ፊትም የእኔን የአገልጋይህን ስም አጥፍቶአል፤ ንጉሥ ጌታዬ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለሆንህ ደስ ያሰኘህን አድርግ። 29#2ሳሙ. 9፥9-11።የአባቴ ቤት ሁሉ ከንጉሥ ጌታዬ ሞት እንጂ ሌላ የሚገባው አልነበረም፤ አንተ ግን አገልጋይህን በማእድህ ከሚካፈሉት ጋር አስቀመጥኸው፤ ከዚህ በላይ ይደረግልኝ ብዬ ንጉሡን ለመጠየቅ ምን መብት አለኝ?” 30#2ሳሙ. 16፥4።ንጉሡም፥ “ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ጺባ እርሻውን ሁሉ እንድትካፈሉ አዝዣለሁ” አለው። 31መፊቦሼትም ንጉሡን፥ “ንጉሥ ጌታዬ እንኳን በደኅና ተመለሰ እንጂ፥ እርሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው። 32#2ሳሙ. 17፥27-29፤ 1ነገ. 2፥7፤ ዕዝ. 2፥61።እንዲሁም ገለዓዳዊው ባርዚላይ ከሮገሊም ወረደ፤ ንጉሡን ለመሸኘትም አብሮት ዮርዳኖስን ተሻገረ። 33ባርዚላይ በዕድሜ የገፋ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበር፤ እጅግ ባለጸጋ ስለ ነበረም ንጉሡ በማሕናይም ሳለ የሚመገበውን አምጥቶለት ነበር። 34ንጉሡም ባርዚላይ፥ “ከእኔ ጋር ተሻገርና በኢየሩሳሌም አብረኸኝ ኑር፤ የሚያስፈልግህን እኔ አደርግልሃለሁ” አለው። 35ባርዚላይ ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የምሄደው ለየትኛው ዕድሜዬ ብዬ ነው? 36እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ ታዲያ የሚያስደስቱና የማያስደስቱ ነገሮችን መለየት እችላለሁን? ከእንግዲህ አገልጋይህ የሚበላውንና የሚጠጣውን ጣዕሙን መለየት ይችላል? የሚዘፍኑትን የወንዶችና የሴቶችን ድምፅ አሁንስ መስማት እችላለሁ? ታዲያ አገልጋይህ ለንጉሥ ጌታዬ ለምን ተጨማሪ ሸክም ይሆናል? 37አገልጋይህ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከንጉሡ ጋር ጥቂት መንገድ ይሄዳል፤ ነገር ግን ንጉሡ በዚህ ሁኔታ ወሮታ የሚመልስልኝ ለምንድን ነው? 38በገዛ ከተማዬ ሞቼ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እንድቀበር፥ እባክህ፥ አገልጋይህን አሰናብተውና ይመለስ፤ ነገር ግን አገልጋይህ ኪምሃም እነሆ፤ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ ደስ ያለህንም ነገር አድርግለት።” 39ንጉሡም፥ “ኪምሃም ከእኔ ጋር ይሻገራል፤ አንተን ደስ የሚያሰኝህንም ሁሉ አደርግለታለሁ፤ ከእኔ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር ለአንተም አደርግልሃለሁ” አለው። 40ስለዚህም ሕዝቡ በሙሉ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ንጉሡም ተሻገረ። ንጉሡ ባርዚላይን ስሞ መረቀው፤ ባርዚላይም ወደ ቤቱ ተመለሰ። 41ንጉሡ ወደ ጌልገላ ሲሄድ፥ ኪምሃም አብሮት ሄደ። የይሁዳ ሠራዊት በሙሉ እንዲሁም ግማሹ የእስራኤል ሠራዊት ንጉሡን አጅበው አሻገሩት። 42ወዲያውም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ መጥተው፥ “ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን በሹልክታ ለብቻቸው ይዘው እርሱንና ቤተሰቡን ከተከታዮቹ ጋር ዮርዳኖስን ለምን አሻገሩ?” አሉት። 43የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ ለእስራኤል ሰዎች፥ “ይህን ያደረግነው ንጉሡ የቅርብ ዘመዳችን ስለሆነ ነው፤ ታዲያ ይህ እናንተን የሚያስቆጣ ነገር ነው? እኛ ከንጉሡ ተቀብለን አንዳች በልተናልን? ለራሳችንስ ምን የወሰድነው ነገር አለ?” አሉአቸው። 44#1ነገ. 11፥31።ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች፥ “እኛ እኮ ከንጉሡ ዐሥር እጅ ድርሻ አለን፤ ከዚህም በተጨማሪ በዳዊት ዘንድ ከእናንተ ይልቅ እኛ የበለጠ መብት አለን፤ ታዲያ እኛን የናቃችሁን ስለ ምንድነው? ንጉሣችን እንዲመለስ በመጀመሪያ የጠየቅነው እኛ አይደለምን?” አሉ። ነገር ግን የይሁዳ ሰዎች የሰጡት መልስ የእስራኤል ሰዎች ከሰጡት መልስ ይልቅ እጅግ የከረረ ነበር።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ