2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21

21
የገባዖናውያን ብቀላ
1 # 2ሳሙ. 24፥13። በዳዊት ዘመነ መንግሥት፥ በተከታታይ ለሦስት ዓመት ራብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት ጌታን ጠየቀ፤ ጌታም፥ “ሳኦል ገባዖናውያንን ስለ ገደለ፥ እርሱና ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ። 2#ኢያ. 9፥3-27።ንጉሡም ገባዖናውያንን ጠርቶ አነጋገራቸው። ገባዖናውያን ከአሞራውያን የተረፉ እንጂ ከእስራኤል ወገን አልነበሩም፤ እስራኤላውያን ሊጠብቋቸው ቢምሉላቸውም፥ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ካለው ቅናት የተነሣ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር፤ 3ዳዊትም ገባዖናውያንን፥ “ምን ላድርግላችሁ? የጌታን ርስት ትባርኩ ዘንድ ማስተሰረያውን ምን ማድረግ አለብኝ?” ሲል ጠየቃቸው። 4ገባዖናውያንም፥ “በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ጉዳይ አይደለም፥ እንዲሁም ከእስራኤል ማንንም ለመግደል መብት የለንም” ብለው መለሱለት። ዳዊትም፥ “ታዲያ ምን ላድርግላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። 5እነርሱም፥ “እንድንፈራርስና በእስራኤልም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዳንኖር ካጠፋንና ደባ ከፈጸመብን ሰው 6ከእርሱ ዘሮች ሰባት ወንዶች ልጆች ይሰጠን፤ እኛም ከጌታ በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ በጌታ ፊት እንስቀላቸው” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ፥ “እሺ! እሰጣችኋለሁ” አለ። 7#2ሳሙ. 9፥13፤ 1ሳሙ. 18፥3፤ 20፥8-10፤15-16፤42።ንጉሥ ዳዊት በራሱና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል በጌታ ፊት ስላደረጉት መሐላ ሲል የሳኦልን ልጅ፥ የዮናታንን ልጅ መፊቦሼትን ከሞት አተረፈ። 8#2ሳሙ. 3፥7።ነገር ግን ንጉሡ የአያ ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች አርሞኒንና መፊቦሼትን፤ የሳኦል ልጅ ሜራብ ለመሖላታዊው ለባርዚላይ ልጅ ለአድሪኤል የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ጭምር ወሰደ፤ 9ከዚያም ለገባዖናውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ገድለው በኰረብታው ላይ በጌታ ፊት ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ሞቱ፤ የተገደሉትም እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ነበር።
10 # 2ሳሙ. 3፥31፤ 12፥16። የአያ ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ፥ በቋጥኝ ላይ ለራሷ አነጠፈች፤ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ ከሰማይ በሬሳዎቹ ላይ እስከወረደ ጊዜ ድረስ ቀን የሰማይ ወፎች ሌሊት የዱር አራዊት እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፤ 11የሳኦል ዕቁባት የአያ ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፥ 12#1ሳሙ. 31፥10-13።ዳዊት ሄዶ፥ ሳኦልን በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤት ሻን አደባባይ ከሰረቁት ከያቤሽ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፥ 13የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አምጥቶ፥ የእነዚያን የተሰቀሉትን ሰዎች ዐፅምም ሰበሰቡ። 14#2ሳሙ. 24፥25።የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።
15እንደገና በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤል መካከል ጦርነት ተደረገ። ዳዊትም ከሰዎቹ ጋር ሆኖ ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ወረደ፤ ዳዊትም ደከመው። 16ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነ ይሽቢበኖብ የተባለ ዳዊትን ለመግደል አሰበ። የናስ ጦሩ ሦስት መቶ ሰቅል የሚመዝንና አዲስ ሰይፍ የታጠቀ ሰው ነበረ። 17#1ነገ. 11፥36፤ 15፥4፤ 2ነገ. 8፥19።የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን ዳዊትን ለመታደግ መጣ፤ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለው። ከዚያም የዳዊት ሰዎች፥ “የእስራኤል መብራት እንዳይጠፋ ከእንግዲህ አንተ ከእኛ ጋር ወደ ጦርነት መውጣት የለብህም” ብለው ማሉለት። 18#1ዜ.መ. 20፥4-8።ከዚህ በኋላ ጎብ በተባለ ስፍራ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሌላ ጦርነት ተደረገ። በዚያን ጊዜም የሑሻው ተወላጅ ሲበካይ፥ ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነውን ሳፍን ገደለው።#2ሳሙ. 23፥27። 19#1ሳሙ. 17፥4፤ 7።ጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተደረገ ሌላ ጦርነትም፥ የቤተልሔሙ የያዒር ዓርጊምን ልጅ ኤልሐናን፥ የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሆነውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለው። 20እንደገና ጌት ላይ በተደረገው ጦርነት በእያንዳንዱ እጁና በእያንዳንዱ እግሩ ስድስት ስድስት ጣቶች ባጠቃላይ ሃያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ግዙፍ ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም ዘር ነበረ። 21#2ሳሙ. 13፥3።ይህም ሰው እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ፥ የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ዮናታን ገደለው። 22እነዚህ አራቱ በጌት የራፋይም ዘሮች የነበሩ ናቸው፤ እነርሱም በዳዊትና በአገልጋዮቹ እጅ ወደቁ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ