የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3

3
1በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የነበረው ጦርነት ለረጅም ጊዜ ቆየ፤ ሆኖም ዳዊት እያየለ ሲሄድ፥ የሳኦል ቤት ግን እየደከመ ነበር።
የዳዊት ልጆች በኬብሮን
2 # 1ዜ.መ. 3፥1-4። ዳዊት በኬብሮን እያለ፥ ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ የበኲር ልጁ፥ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአሒኖዓም የተወለደው አምኖን፥ 3#2ሳሙ. 13፥37፤ 15፥8።ሁለተኛው፥ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጌል የተወለደው ኪልአብ፥ ሦስተኛው፥ ተልማይ ከተባለው ከገሹር ንጉሥ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም፥ 4#1ነገ. 1፥5።አራተኛው፥ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፤ አምስተኛው፥ ከአቢጣል የተወለደው ሸፋጥያ፥ 5ስድስተኛው፥ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትረዓም ነበር፤ እነዚህ ዳዊት በኬብሮን እያለ የተወለዱለት ናቸው።
የአበኔርና የኢያቡስቴ መለያየት
6የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ፥ አበኔር በሳኦል ቤት ሆኖ ኀይሉን ያጠናክር ነበር። 7#2ሳሙ. 16፥21-22፤ 21፥8-10፤ 1ነገ. 2፥21-22።ሳኦልም ሪጽፋን የምትባለውን የአያን ልጅ በዕቁባትነት አስቀምጦአት ነበር፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፥ “ለምንድን ነው ከአባቴ ዕቁባት ጋር የተኛኸው?” አለው። 8ይህ የአበኔር ንግግር እጅግ ያስቆጣው ኢያቡስቴ እንዲህ አለ፤ “እኔ ለአባትህ ለሳኦል ቤት፥ ለወንድሞቹና ለዘመዶቹ፥ ታማኝነቴን ሳላጎድል ይሄው አለሁ፤ አንተንም ለዳዊት እጅ አሳልፌ አልሰጠሁም፥ ዛሬ ግን አንተ በዚህች ሴት ትከሰኛለህን? በውኑ እኔ የውሻ ራስ ነኝ? 9#ሩት 1፥17።ጌታ ለዳዊት በመሐላ የሰጠውን ተስፋ ከፍጻሜ ሳላደርስ ብቀር እግዚአብሔር በአበኔር ላይ ይፍረድ፤ ከዚያ የባሰም ያምጣበት፤ 10#2ሳሙ. 5፥2፤ 1ሳሙ. 25፥30።ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ላይ የዳዊትን ዙፋን ለመመሥረት መንግሥትን ከሳኦል ቤት እንደሚወስድ ተስፋ ተሰጥቶታልና።” 11ኢያቡስቴም አበኔርን ስለ ፈራ ሌላ ቃል ሊመልስለት አልደፈረም።
12ከዚያም አበኔር ለዳዊት እንዲህ ሲሉ ለዳዊት እንዲነግሩት መልክተኞች ላከ፥ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፥ እጄም ከአንተ ጋር ትሆናለች፥ እስራኤልንም ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ።” 13#1ሳሙ. 18፥20-27።ዳዊትም፥ “ይሁን፥ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፥ ነገር ግን አንድ ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ፊቴን ለማየት በመጣህ ጊዜ፥ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ካላመጣህልኝ ፊቴን አታይም” አለ። 14ከዚያም ዳዊት፥ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልክተኞች ላከበት። 15#1ሳሙ. 25፥44።ኢያቡስቴም መልክተኛ ልኮ፥ ሜልኮልን ከባሏ ከላይሽ ልጅ ከፓልጢኤል ወሰዳት። 16ባሏም እስከ ባሑሪም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሎአት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፥ “ሂድ፥ ተመለስ” አለው፤ እርሱም ተመለሰ።
17አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ተመካከረ፥ “ቀደም ሲል ዳዊት ንጉሣችሁ እንዲሆን ፈልጋችሁ ነበር፤ 18ስለዚህ ጌታ ለዳዊት፥ ‘በአገልጋዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ተስፋ ስለ ሰጠው፥ ይህን አሁን አድርጉ።” 19እንዲሁም አበኔር ሄዶ ይህንኑ ለብንያማውያን ነገራቸው፤ ከዚያም እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለጉትን ሁሉ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ። 20አበኔር ከሃያ ሰዎች ጋር ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን በመጣ ጊዜ፤ ዳዊት ለአበኔርና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። 21ከዚያም አበኔር ዳዊትን፥ “ለጌታዬ ለንጉሡ መላውን እስራኤልን ልሰብስብ፥ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፥ ልብህ እንደተመኘውም ሁሉን እንድትገዛ ፈጥኜ ልሂድ” አለው። ስለዚህ ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ።
ኢዮአብ አበኔርን ገደለው
22በዚያን ጊዜም የዳዊት አገልጋዮችና ኢዮአብ ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለ ሄደ፥ በኬብሮን አልነበረም። 23ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሠራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፥ “የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መጣ፥ አሰናበተውም እርሱም በሰላም ሄደ” ብለው ለኢዮአብ ነገሩት። 24ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፤ “ምንድነው ያደረግከው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ፥ በሰላም እንዲሄድ ያሰናበትኸው ለምንድነው? 25የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ የመጣው ሊያታልልህ፥ መውጫና መግቢያህን ሊያውቅብህና፥ የምታደርገውን ሁሉ ሊሰልልህ ነው።” 26ከዚያም ኢዮአብ ከዳዊት ፊት እንደ ወጣ፤ ወደ አበኔር መልክተኞች ላከ፤ መልክተኞቹም ከሲራ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም ነበር።
27 # 2ሳሙ. 2፥17-23፤ 1ነገ. 2፥5፤31-33። አበኔርም ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ፥ ኢዮአብ ለብቻው የሚያነጋግረው በመምሰል ወደ ቅጽሩ በር ይዞት ሄደ፤ እዚያም የወንድሙን የአሣሄልን ደም ለመበቀል ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው። 28#2ሳሙ. 2፥22-23።ዳዊት ይህን ነገር ቆይቶ በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔም ሆንሁ መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በጌታ ፊት ለዘለዓለም ንጹሕ ነን፤ 29ደሙ በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይሁን፤ ከኢዮአብ ቤት ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ወይም የሥጋ ደዌ ያለበት፥ በምርኲዝ የሚሄድ አንካሳ፥ ወይም በሰይፍ ተመቶ የሚሞት ወይም የሚበላው ያጣ ራብተኛ አይታጣ።” 30አበኔር ገባዖን ላይ በተደረገው ጦርነት የኢዮአብንና የአቢሳን ወንድም አሣሄልን ገድሎት ስለ ነበር፥ እነርሱም አበኔርን ገደሉት።
31 # 2ሳሙ. 21፥10። ከዚያም ዳዊት ለኢዮአብና አብሮት ለነበረው ሕዝብ ሁሉ፥ “ልብሳችሁን ቀዳችሁና ማቅ ለብሳችሁ በአበኔር ፊት አልቅሱ” አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ከቃሬዛው በኋላ ሄደ። 32አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም ጮኾ በአበኔር መቃብር ላይ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንደዚሁ አለቀሱ። 33ንጉሡም ለአበኔር ይህን የኀዘን እንጉርጉሮ ተቀኘ፤
34“አበኔር እንደ ተራ ሰው ይሙት?
እግሮችህ በእግር ብረት አልገቡም፤
ሰው በክፉ ሰዎች ፊት እንደሚወድቅ
አንተም እንደዚሁ ወደቅህ።”
ሕዝቡም ሁሉ እንደገና አለቀሱለት። 35#ሩት 1፥17።ከዚያም ሕዝቡም ሁሉ ገና ሳይመሽ ዳዊትን እንጀራ እንዲበላ አጥብቀው ለመኑት። ዳዊት ግን፥ “ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ያድርግብኝ ከዚያም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ማለ። 36ሕዝቡም ሁሉ ይህንኑ ተመልክተው ደስ አላቸው፤ በእርግጥ ንጉሡ ያደረገው ሁሉ ሕዝቡን ደስ አሰኛቸው።
37በዚያን ዕለት ሕዝቡ ሁሉና እስራኤል በሙሉ ንጉሡ በኔር ልጅ በአበኔር ሞት እጁ እንዳልነበረበት ዐወቁ። 38ከዚያም ንጉሡ ለአገልጋዮቹ እንዲህ አለ፤ “በዛሬዪቱ ዕለት በእስራኤል መስፍንና ታላቅ ሰው መውደቁን አላወቃችሁምን? 39#መዝ. 28፥4፤ ኢሳ. 3፥11።ምንም እንኳ ዛሬ የተቀባሁ ንጉሥ ብሆንም፥ እኔ ደካማ ሰው ነኝ፤ እነዚህ የጽሩያ ልጆች እጅግ በርትተውብኛል። ጌታ ለክፉ አድራጊ የእጁን ይስጠው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ