2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል መግቢያ
መግቢያ
ሁለተኛ ሳሙኤል ታሪኩን በሐተታ፥ በግጥም፥ በመዝሙር እና በሥነ ጽሑፋዊ ውበት የሚያቀርብ መጽሐፍ ነው። የሳኦልንና የዮናታንን ሞት በማስመልከት ዳዊት የኀዘን ቅኔ ሲቀኝ ሥነ ጹሑፋዊ ቅርጹ ግጥም እንደሆነ መረዳት ይቻላል። እንዲሁም ሁለተኛ ሳሙኤል የዳዊትን በመላው እስራኤል ላይ መንገሥ ያወሳ፤ በተጨማሪም ከአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ካሉት ጠላቶቹ ጋር የነበረውን ጦርነት በሐተታ መልክ ያቀርበዋል። እግዚአብሔር ከሳኦል እጅ ባዳነው ጊዜ ዳዊት በመዝሙር ተቀኝቷል። ሁለተኛ ሳሙኤል ማራኪ፥ ልብ አንጠልጣይ እና የአንባቢያንን ትኩረት የሚስብ መጽሐፍ ነው።
የመጽሐፉ አወቃቀር፦ ሁለተኛ ሳሙኤል በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ተዋቅሯል። የመጀመሪያው ክፍል ከምዕራፍ አንድ እስከ ምዕራፍ አራት ስለ ሳኦልና ዮናታን አሟሟት ከተረከ በኋላ ዳዊት በይሁዳ ነገድ ላይ በኬብሮን መንገሱን ያስገነዝበናል። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ከምዕራፍ አምስት ቍጥር አንድ እስከ ምዕራፍ ሀያ አራት ቍጥር ሀያ አምስት ያለው ሐሳብ ሲሆን ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ እንደ ነገሠ ይገልጻል። ሕዝቡ በዳዊት አስተዳደር ዘመን በምድራዊ ሀብት የበለጸጉበትና ጠላቶቻቸውን በጦርነት ድል ያደረጉበት ጊዜ ነበር። ዳዊት ታቦቱን ከአቢዳራ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ማምጣቱ በዳዊት ዘመን መንፈሳዊ ተሐድሶ እንደተካሔደ የሚያሳይ ምልክት ነው። ይሁን እንጂ ዳዊት በንግሥናው ጊዜ የልቡን ፍላጎትና ምኞት ለመፈጸም ሲል ክፉ ተግባር ፈጽሟል። የእግዚአብሔርንም ሕግ በመጻረር ከቤርሳቤህ ጋር ዝሙት ፈጽሞል ንጹሕ የሆነውን ኦርዮንን በተንኰል በጦር ሜዳ እንዲሞት አድርጓል። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በዳዊት ቤት ላይ ታላቅ ቅጣት እንዳመጣና በጠላቶቹም ፊት እንዳዋረደው ይገልጻል።
ዳዊት የዝሙትና ንጹሕ ሰውን የማስገደል ኀጢአቱ፥ እንዲሁም የወንዶች ልጆቹን ኀጢአት አይቶ እንዳላየ ሳይወቅሳቸው መቅረቱ፥ በቤተሰቡና በመላው አገሪቱ የሁከትና የብጥብጥ ምክንያት እንደሆነ እንመለከታለን።
የመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘት
የዳዊት ወደ ዙፋን መምጣት ወይም መንገሥ (1፥1—5፥1፥5)
ዳዊት በይሁዳ ላይ እነደ ነገሠ (1፥27—4፥12)
ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ እነደ ነገሠ (5፥5)
ዳዊት በንግሥናው ዘመን የፈጸማቸው ተግባራትና ያገኘው ክብር (5፥6—9፥13)
ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል ማድረጉና ኢየሩሳሌምን መያዙ (5፥6-25)
ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ማምጣቱ (6)
እግዚአብሔር ለዳዊት ቤት የገባው ንግሥና የገባው የዘላለም ቃል ኪዳን (7)
የዳዊት መንግሥት መስፋፋትና ለሀገሩም ሕዝብ ፍትሕ መስፈኑ (8)
ዳዊት ለዮናታን ለግባው ቃል ኪዳን ታማኝነት ማሳየቱ (9)
የዳዊት መንግሥት ድክመትና ውድቀት (10፥1—20፥26)
ዳዊት በዝሙት መበደሉና ነፍስ ማጥፋቱ (10፥1—12፥31)
የዳዊት ልጆች አምኖንና አቤሴሎም መሞት (13፥1—20፥26)
የዳዊት መንግሥት በፍጻሜው ላይ የነበረው ገጽታ (21፥1—24፥25)
ምዕራፍ
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል መግቢያ: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ