የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 16

16
ጢሞቴዎስ ጳውሎስና ሲላስን ተከትሎ እንደ ሄደ
1ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራንም ደረሰ። እነሆም፥ በዚያ የአንዲት ያመነች አይሁዳዊት ልጅ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀመዝሙር ነበረ፤ አባቱ ግን የግሪክ ሰው ነበረ። 2ለእርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች መሰከሩለት። 3ጳውሎስ ይህ ከእርሱ ጋር ይወጣ ዘንድ ወደደ፤ በእነዚያም ስፍራዎች ስለ ነበሩ አይሁድ ይዞ ገረዘው፤ አባቱ የግሪክ ሰው እንደሆነ ሁሉ ያውቁ ነበርና። 4በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቆረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው። 5አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ይበረቱ ነበር፤ በቍጥር ም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር።
ጳውሎስ ስለ መቄዶንያው ሰው ያየው ራእይ
6በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤ 7በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘድን ሞከሩ፤ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም፤ 8በሚስያም አጠገብ አልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። 9ራእይም ለጳውሎስ በሌሊት ታየው፤ አንድ የመቄዶንያ ሰው “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን፤” እያለ ቆሞ ሲለምነው ነበር። 10ራእዩንም ካየ በኋላ ወዲያው ወደ መቄዶንያ ልንወጣ ፈለግን፤ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ጠራን መስሎናልና።
የልድያ በክርስቶስ ማመን
11ከጢሮአዳም ተነሥተን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ በነገውም ወደ ናጱሌ በመርከብ ሄድን፤ 12ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ደረስን፤ እርሷም የመቄዶንያ ከተማ ሆና የወረዳ ዋና ከተማና ቅኝ አገር ናት፤ በዚህችም ከተማ አንዳንድ ቀን እንቀመጥ ነበር። 13በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን። 14ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ ያሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት። 15እርሷም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ “በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ፤” ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።
የጳውሎስና የሲላስ መታሰር
16ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቆለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። 17እርሷ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች “የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባርያዎች ናቸው፤” ብላ ትጮኽ ነበር። 18ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን “ከእርሷ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ፤” አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።
19ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ 20ወደ ገዢዎም አቅርበው “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። 21እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ፤” አሉ። 22ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፤ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ 23በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፤ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። 24እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፤ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸ።
25በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፤ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር 26ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ፤ የሁሉም እስራት ተፈታ። 27የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። 28ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ “ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፤” ብሎ ጮኸ። 29መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፤ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤ 30ወደ ውጭም አውጥቶ “ጌቶች ሆይ! እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” ኣላቸው። 31እነርሱም “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ፤” አሉት። 32ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው። 33በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቁስላቸውን አጠበላቸው፤ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤ 34ወደ ቤቱም አውጥቶ ማዕድ አቀረበላቸው፤ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ።
35በነጋም ጊዜ ገዢዎቹ “እነዚያን ሰዎች ፍታቸው፤” ብለው ሎሌዎቻቸውን ላኩ። 36የወኅኒውም ጠባቂ “ትፈቱ ዘንድ ገዢዎቹ ልከዋል፤ እንግዲህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ፤” ብሎ ይህን ቃል ለጳውሎስ ነገረው። 37ጳውሎስ ግን “እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበው በወኅኒ ጣሉን፤ አሁንም በስውር ይጥሉናልን? አይሆንም፤ ራሳቸው ግን መጥተው ያውጡን፤” አላቸው። 38ሎሌዎቹም ይህን ነገር ለገዢዎች ነገሩ፤ የሮሜ ሰዎችም እንደ ሆኑ በሰሙ ጊዜ ፈሩ። 39መጥተውም ማለዱአቸው፤ አውጥተውም ከከተማ ይወጡ ዘንድ ለመኑአቸው። 40ከወኅኒውም ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ፤ ወንድሞችንም ባዩ ጊዜ አጽናኑአቸውና ሄዱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ