ትንቢተ አሞጽ 3
3
1የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታ በእናንተ ላይ፥ ከግብጽ ምድር ባወጣሁት ወገን ሁሉ ላይ የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤ 2እንዲህም ይላል፦ “እኔ ከምድር ወገኖች ሁሉ እናንተን ብቻ አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ።
የነቢዩ ተግባር እና ተልእኮ
3“በውኑ ሁለት ሰዎች ተቀጣጥረው ሳይገናኙ በአንድነት ሊሄዱ ይችላሉን? 4ወይስ አንበሳ የሚነጥቀው ነገር ሳያገኝ በጫካ ውስጥ ያገሣልን? ወይስ የአንበሳ ደቦል አንዳች ነገር ሳይዝ በማደርያው ሆኖ ይጮኻልን? 5ወይስ ወፍ፥ የሚያጠምደው ነገር ሳይኖር፥ በምድር ላይ በወጥመድ ይያዛልን? ወይስ ወስፈንጠር አንዳች ነገር ሳይዝ ከምድር ይፈነጠራልን? 6ወይስ በከተማ ውስጥ መለከት ቢነፋ ሕዝቡ አይፈራምን? ወይስ ጌታ ካላደረገው በቀር በከተማ ላይ ክፉ ነገር ይሆናልን? 7በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባርያዎቹ ለነቢያት ሳይገልጥ ምንም ነገር አያደርግም። 8አንበሳው አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?”
ጌታ በሰማርያ ላይ ፍርድን አደረገ
9በአዛጦን የንጉሥ ቅጥሮችና በግብጽ ምድር ባሉ የንጉሥ ቅጥሮች ላይ አውጁ እንዲህም በሉ፦ “በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፥ በመካከልዋም የሆነውን ታላቁን ውካታ፥ በውስጧም ያለውን ግፍ ተመልከቱ።” 10“በንጉሥ ቅጥሮቻቸውም ግፍንና ቅሚያን የሚያከማቹ ቅን ነገር እንዴት እንደሚደረግ አያውቁም፥” ይላል ጌታ። 11ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ምድሪቱን በዙርያዋ ጠላት ይከባታል፤ ምሽግሽንም ከአንቺ ያፈርሳል፥ የንጉሥ ቅጥሮችሽም ይበዘበዛሉ።” 12ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እረኛ ከአንበሳ አፍ ሁለት እግርን ወይም የጆሮን ጫፍ እንደሚያድን፥ እንዲሁ በሰማርያ የተቀመጡት የእስራኤል ልጆች ከድንክ አልጋና ከአልጋ የእግር ቁራጭ ጋር ይድናሉ።”
13“ስሙ፥ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ፥” ይላል የሠራዊት አምላክ ጌታ እግዚአብሔር። 14#2ነገ. 23፥15።“እስራኤልን ስለ ኃጢአቱ በምበቀልበት ቀን የቤቴልን መሠዊያዎች ደግሞ እበቀላለሁ፤ የመሠዊያውም ቀንዶች ይሰበራሉ፥ ወደ ምድርም ይወድቃሉ። 15የክረምቱንና የበጋውን ቤት እመታለሁ፤ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፥ ታላላቅም ቤቶች ይፈርሳሉ፥” ይላል ጌታ።
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ