ትንቢተ አሞጽ መግቢያ

መግቢያ
አሞጽ በደቡባዊ የይሁዳ አገር በምትገኝ ቴቁሔ በምትባል መንደር ተወለደ። ንጉሥ ኢዮርብዓም 2ኛ በነገሠበት ዘመን፥ ነቢዩ በሰሜናዊው የእስራኤል መንገሥት ላይ ትንቢትን ተናገረ። አሞጽ በበግ አርቢነት (1፥1)፥ በመንጋ ጠባቂነትና የዋርካ ዛፎችን በመንከባከብ (7፥14) ሥራ ላይ ተሠማርቶ ነበር። ስለዚህም በነቢያት ማኅበር እንዳልነበር፤ የነቢይም ልጅ እንዳልሆነ፥ ዳሩ ግን ጌታ ከዕለታዊ ሥራው ላይ እንደ ጠራው ተናግሮአል (7፥10-17)። አሞጽ ነቢይ ብቻ ሳይሆን ባለ ራእይም ጭምር ነበር (7፥1-9፤ 8፥1—9፥6)። እርሱ ትንቢቱን በተናገረበት ወቅት የእስራኤል መንግሥት ሰላም የሰፈነበትና ታላቅ ባለጸግነት የተቀዳጀበት ዘመን ነበር። ቢሆንም ሀብታሞች ደሀውን በመጨቆንና በመበደል ቁሳዊ ጥቅማ ጥቅሞች ያገኙ ነበር። ይህንንም ሁኔታ ነቢዩ አሞጽ በዝርዝር በማመልከት ወቅሶታል (4፥1፤ 5፥11፤ 6፥4-7፤)። የእስራኤል ሕዝብ የተለያዩ መሥዋዕትን በማቅረብ (4፥4፤ 5፥5)፥ በዓላትንም በማክበር (5፥21-23)፥ ውጫዊ የአምልኮ ሥርዓትን በቀናዒነት ቢፈጽሙም እንኳ የጽድቅንና የፍትሕን ተግባራት አለመፈጸማቸውን ነቢዩ ይናገራል። ሀብታሙ በደሀው ላይ የሚፈጽመውን ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ያወግዛል (2፥6፤ 3፥9-10፤ 4፥1፤ 8፥5-6)። ነቢዩ አሞጽ በመላ እስራኤል ለበዝባዦችና ለጨቋኞች የሚያደላ ሥርዓት ይቃወማል (3፥10፤ 5፥7-24፤ 6፥12)። ችግረኛው (2፥6፤ 4፥1፤ 5፥12፤ 8፥4፤6)፤ ደሀውና (2፥7፤ 5፥11፤ 8፥6) ተጨቋኙ (2፥7፤ 8፥4) ተገቢው ፍትሕ እንዲያገኝ ይከራከራል። እንዲሁም በእስራኤል ያለውን ብልሹ ሥነ ምግባርና (2፥4፤7፤8) የጣዖት አምልኮ (5፥26፤ 8፥14) ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። በጌልገላና በቤርሳቤህ የሚገኙትን የአምልኮ ስፍራዎች ያወግዛል (3፥14፤ 4፥4-5፤ 5፥4-5፤ 7፥10-13)። ነቢዩ የጌታን ፍርድ በአምስቱ ራእዮች ውስጥ ይመለከታል። እንዲሁም ስለ ሁለት የእስራኤል የመታደስ ቃል ኪዳን ትንቢት ይናገራል። ባጠቃላይ ትንቢተ አሞጽ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ሕግጋት በመተላለፋቸው በአሕዛብ፥ በይሁዳና በእስራኤል መንግሥታት ላይ የሚያመጣውን የቊጣውን ፍርድ የሚገልጽ ትንቢት ነው።
ትንቢተ አሞጽ በሦስት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል። አንደኛው ክፍል ከምዕራፍ አንድ እስከ ምዕራፍ ሁለት ያለው ነው፤ ይህም ስለ ነቢዩ አሞጽና የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ሕግ በመተላለፋቸው በሌሎች ሕዝቦች፥ በይሁዳና በእስራኤል መንግሥታት ላይ ስለተሰጠ ፍርድ ያወሳል። ሁለተኛው ክፍል ከምዕራፍ ሦስት እስከ ምዕራፍ ስድስት ድረስ ያለው ነው፤ ይህም የእግዚአብሔርን ኃያልነት ስለማወደስና ጌታ በእስራኤል ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ በሰፊው የሚዳስስ ነው። ሦስተኛው ክፍል ከምዕራፍ ሰባት እስከ ምዕራፍ ዘጠኝ ያለውን ያጠቃልላል፤ በዚህም ክፍል ውስጥ ስለ አምስቱ ራእዮች፤ ስለ ቤቴሉ ካህን አሚስያስ፤ ነቢዩ አሞጽ ስለ ተነበየው ትንቢትና ስለ መታደስ የቃል ኪዳን ተስፋ ይናገራል።
ትንቢተ አሞጽ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጠውን የቃል ኪዳኑን ሕግ መጠበቅ እንደሚገባ፥ የእግዚአብሔር ኃያልነቱና ቃል ኪዳኑ በእስራኤል ላይ ብቻ ሳይሆን በፍጥረታት ሁሉ ላይ እንደሚሠራ፥ ደካማውን የሕብረተሰብ ክፍል መበዝበዝና ፍትሕን በማጓደል መጨቆን እንደማይገባ ያስተምራል፤ ይህ የሆነ እንደሆነ ግን ጌታ በፍርዱ ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጥ በመልእክቱ ውስጥ ይናገራል። ትንቢተ አሞጽ፥ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር መመረጣቸው ከሌሎች ሕዝቦች የሚለያቸውና ባለጠግነትን የሚያጎናጽፋቸው ሳይሆን፥ ይልቁንም ፍትሕንና ጽድቅን እንዲፈጽሙ የሚያስገድዳቸው ኃላፊነት መሆኑን ያስረዳል። ፍትሕና ጽድቅ ካልተጨመሩበት በቀር ውጫዊ የአምልኮ ሥርዓትና ባለጠግነት ብቻቸውን የመዳንን የሕይወት የውኃ ምንጭ ሊያስገኙልን አይችሉም። ስለዚህም እንዲህ ያለውን በደሀው ላይ የሚደርሰውን ጭቆና በኀዘን በመመልከት ነቢዩ፦ “ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ” (5፥24) ብሎ ትንቢት ተናገረ።
ምዕራፍ

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ