ኦሪት ዘዳግም 1
1
የእስራኤል ሕዝብ ከኮሬብ እንዲነሡ የተሰጠ ትእዛዝ
1በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ትይዩ በሆነው ሱፍ ፊት ለፊት፥ በፋራን እና በጦፌልም፥ በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው። 2ከኮሬብ በሴይር ተራራ መንገድ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የዐሥራ አንድ ቀን መንገድ ነው። 3በአርባኛው ዓመት በዓሥራ አንደኛው ወር መጀመሪያ ቀን፥ ሙሴ፥ ጌታ ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው። 4#ዘዳ. 2፥24—3፥11፤ ዘኍ. 21፥21-35።በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስታሮትና በኤድራይ ተቀምጦ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመታ በኋላ፥ 5በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህን ሕግ ይገልጥ ጀመር፦
6 #
ዘፀ. 32፥34—33፥3። “ጌታ አምላካችን በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ ‘በዚህ ተራራ ለረጅም ጊዜ ቆይታችኋል፤ 7ተመልሳችሁ ተጓዙ፥ ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር፥ ወደ አጎራባቾቹም በዓረባም በደጋውና በቆላው ሁሉ፥ በኔጌብም በባሕርም ዳር ወዳሉ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም እስከ ታላቁ ወንዝም እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። 8#ዘዳ. 6፥10፤ 23፤ 9፥5፤ 27፤ 29፥13፤ 30፥20፤ 34፥4፤ ዘፍ. 12፥7፤ 13፥14-15፤ 15፥18-21፤ 17፥8፤ 26፥3-5፤ 28፥13-14።እነሆ፥ ምድሪቱን በፊታችሁ አኖራለሁ፥ ግቡ፥ ጌታ ለእነርሱ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውንም ምድር ውረሱ።’
የሕዝብ መሪዎች መሾም
9 #
ዘፀ. 18፥13-26፤ ዘኍ. 11፥16-30። “በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ ተናገርኋችሁ፦ ‘እኔ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፥#ዘዳ. 1፥31። 10#ዘዳ. 10፥22፤ ዘፍ. 15፥5፤ 22፥17፤ 26፥3-4፤ ዘፀ. 32፥13።ጌታ አምላካችሁ አብዝቶአችኋል፥ እነሆም፥ እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዛት ናችሁ። 11የአባቶቻችሁ አምላክ፥ ጌታ እንደ ተናገራችሁም፥ በዚህ ቍጥር ላይ ሺህ ጊዜ እጥፍ ይጨምር፥ ይባርካችሁም። 12እኔ ብቻዬን ድካምችሁን፥ ሸክማችሁንም፥ ክርክራችሁንም እሸከም ዘንድ እንዴት እችላለሁ? 13ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች፥ አስተዋዮች፥ አዋቂዎች የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፥ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ።’ 14እናንተም፦ ‘እናደርገው ዘንድ የተናገርኸው ይህ ነገር መልካም ነው፥’ ብላችሁ መለሳችሁልኝ። 15እኔም ጥበበኞችና አዋቂዎች የሆኑትን የነገዶቻችሁን አለቆች ተቀበልኩ፥ በእናንተም ላይ የሺህ አለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ የኀምሳ አለቆችም፥ የዐሥር አለቆችም ገዢዎችም በየነገዶቻቸው አደረግኋቸው። 16#ዘዳ. 10፥17-18፤ 16፥18-20።በዚያን ጊዜ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው። አልኋቸውም፦ ‘የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፥ በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ። 17በፍርድም አድልዎ አታድርጉ፥ ታላቁን እንደምትሰሙ፥ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ፥ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ፥ አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም እሰማዋለሁ፤’ 18በዚያን ጊዜም ልታደርጉት የሚገባችሁን ነገር ሁሉ አዘዝኋችሁ።
የሰላዮች ወደ ተስፋይቱ ምድር መላክ
19 #
ዘኍ. 13፥1-27። “ከኮሬብም ወጣን፥ ጌታ አምላካችን እንዳዘዘን በታላቁ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ሁሉ ባያችሁት ምድረ በዳ በኩል በተራራማው በአሞራውያን መንገድ ሄድን፥ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን።#ዘኍ. 11፥11-35። 20እኔም አልኋችሁ፦ ‘ጌታ አምላካችን ወደሚሰጠን ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር መጣችሁ፥ 21እነሆ፥ ጌታ አምላካችሁ ምድሪቱን በፊትህ አኑሮአል፥ የአባቶችህ አምላክ ጌታ እንዳለህ፥ ውጣ፥ ውረሳት፥ አትፍራ፥ አትደንግጥም።’
22“እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ፦ ‘ምድሪቱን እንዲሰልሉልንና እንወጣባት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንላክ’ አላችሁኝ።
23“ነገሩ መልካም ሆኖ ታየኝ፥ ከእናንተም ዐሥራ ሁለት ሰው መረጥሁ፥ ከየነገዱ ሁሉ አንዳንድ ሰው ነበረ። 24ሄዱም፥ ወደ ተራራማውም ወጡ፥ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጥተው ቃኙት። 25ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፥ ወደ እኛም ይዘውት መጡ፥ አሉንም፦ ‘ጌታ አምላካችን የሚሰጠን ምድር መልካም ናት።’
26 #
ዘኍ. 13፥28—14፥38። “እናንተ ግን በጌታ በአምላካችሁ ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ ወደ እርሷ መውጣትን አልፈቀዳችሁም፥#ዘዳ. 9፥23። 27#ዘዳ. 9፥28።በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ ብላችሁ አጉረመረማችሁ፦ ‘ጌታ ስለ ጠላን በአሞራውያን እጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ፥ ሊያጠፋን ከግብጽ ምድር አወጣን። 28#ዘዳ. 1፥28፤ 2፥10-11፤ 21፤ 9፥2፤ ዘኍ. 13፥22፤ 28፤ 33፤ ኢያ. 11፥21-22፤ 14፥12፤ 15፤ 15፥13-14፤ 21፥11፤ መሳ. 1፥20።ወዴትስ እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው፥’ ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አወኩት።
29“እኔም አልኋችሁ፦ ‘አትሸበሩ፥ እነርሱንም አትፍሩ፥ 30#ዘዳ. 3፥22፤ 8፥15፤ 32፥10፤ ዘፀ. 14፥13-14።በዓይናችሁ ፊት በግብጽ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ በፊታችሁ የሚሄደው ጌታ አምላካችሁ ስለ እናንተ ይዋጋል፤ 31ወደዚህም ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ በምድረ በዳም፥ ሰው ልጁን እንደሚንከባከብ፥ ጌታ አምላካችሁ እንዴት እንደተንከባከባችሁ አይታችኋል።’ 32ይህም ሆኖ በዚህ ነገር ጌታ አምላካችሁን አላመናችሁም፤ 33#ዘፀ. 13፥21፤ 40፥38፤ ዘኍ. 9፥15-16፤ 10፥33-34፤ 14፥14።እርሱ ግን የምትሰፍሩበትን ቦታ ለመፈለግ፥ ትሄዱበት ዘንድ የሚገባውንም መንገድ ለማሳየት ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን ጌታ አምላካችሁን አላመናችሁም።
እግዚአብሔር እስራኤላውያንን መቅጣቱ
34“ጌታም የቃላችሁን ድምፅ ሰምቶ ተቆጣም፤ እንዲህም ሲል ማለ፦ 35‘ከዚህ ክፉ ትውልድ፥ ከእነዚህ ሰዎች አንዳቸውም፥ ለአባቶቻችሁ እሰጣት ዘንድ የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር አያይም፤ 36#ኢያ. 14፥6-14።ከይፉኔ ልጅ ከካሌብ በቀር፤ እርሱ ያያታል፥ የረገጣትን ምድር ለእርሱ ለልጆቹም እሰጣለሁ፥ ምክንያቱም ጌታን ፈጽሞ ተከትሎአል።’ 37#ዘዳ. 4፥21፤ 34፥4፤ ዘኍ. 20፥12።በእናንተው ምክንያት ጌታ በእኔም ላይ ደግሞ ተቆጥቶ እንዲህም አለኝ፤ ‘አንተም ደግሞ ወደዚያ አትገባም፤ 38#ዘዳ. 31፥3፤ 7—8፤ ዘኍ. 27፥18-23፤ 34፥17፤ ኢያ. 1፥1-9።በፊትህ የሚቆመው የነዌ ልጅ ኢያሱ ወደዚያ ይገባል፤ እርሱ ለእስራኤል ምድሪቱን ያወርሳልና አበረታታው።’
39“ደግሞ፦ ‘ይማረካሉ ያላችኋቸው ሕፃናቶቻችሁ፥ ዛሬም መልካሙን ከክፉ መለየት የማይችሉ ልጆቻችሁ፥ እነርሱ ወደዚያ ይገባሉ፥ ምድሪቱንም ለእነርሱ እሰጣለሁ፥ ይወርሱአታልም። 40እናንተ ግን ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር አቅጣጫ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።’
41 #
ዘኍ. 14፥39-45። “እናንተም፦ ‘ጌታን በድለናል፥ ጌታ አምላካችን ልክ እንዳዘዘን፥ እንወጣለን እንዋጋለንም’ ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ከእናንተም ሰው ሁሉ የጦር መሣሪያውን ያዘ፥ ወደ ተራራማውም አገር መውጣትን አቀለላችሁት።
42“ጌታም፦ ‘እኔ በእናንተ መካከል አይደለሁምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ፥ አትዋጉም በላቸው’ አለኝ። 43እኔም ተናገርኋችሁ፥ እናንተ ግን በጌታ ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ አልሰማችሁም፥ በትዕቢታችሁም ወደ ተራራማው አገር ወጣችሁ። 44በዚያም በተራራማው አገር ይኖሩ የነበር አሞራውያን ወጥተው ተጋጠሙአችሁ፥ እንደ ንብ መንጋ አሳደዱአችሁ፥ እስከ ሔርማም ድረስ በሴይር ድል ነሷችሁ። 45ተመልሳችሁም በጌታ ፊት አለቀሳችሁ፥ እግዚአብሔር ግን ድምፃችሁን ሊሰማም፥ እናንተም ሊያዳምጥ አልወደደም። 46ስለዚህ እንደ ተቀመጣችሁበትም ዘመን መጠን፥ በቃዴስ ብዙ ቀን ተቀመጣችሁ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ