ኦሪት ዘዳግም 29
29
በሞዓብ ምድር የታደሰው ቃል ኪዳን
1ጌታ በኮሬብ ከገባው ቃል ኪዳን በተጨማሪ በሞዓብ ምድር ከእስራኤላውያን ጋር እንዲያደርግ ሙሴን ያዘዘው የኪዳኑ ቃሎች የሚከተሉት ናቸው፦
2ሙሴም እስራኤላውያንን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ በዐይኖቻችሁ ፊት በግብጽ ምድር፥ በፈርዖን፥ በአገልጋዮቹ ሁሉና በመላ አገሩ ላይ ያደረገውን አይታችኋል። 3ዐይኖቻችሁ ከባድ ፈተናዎችን፥ ታምራዊ ምልክቶችንና ታላላቅ ድንቆች አይተዋል። 4ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ጌታ የሚያስተውል ልቡና ወይም የሚያዩ ዐይኖች ወይም የሚሰሙም ጆሮች አልሰጣችሁም። 5አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ ስመራችሁ ልብሳችሁ አላረጀም፤ የእግራችሁም ጫማ አላለቀም። 6ቂጣ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም፤ ይህን ያደረግሁት እኔ እግዚአብሔር ጌታ እንደሆንኩ እንድታውቁ ነው። 7#ዘኍ. 21፥21-30፤ ዘኍ. 21፥31-35።ወደዚህም ስፍራ በደረሳችሁ ጊዜ፥ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎንና የባሳን ንጉሥ ዐግ ሊወጉን መጡ፤ ነገር ግን ድል አደረግናቸው። 8#ዘኍ. 32፥33።ምድራቸውንም ወርሰን ለሮቤላውያን፥ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠን። 9ስለዚህ የምታደርጉት ሁሉ እንዲከናወንላችሁ የዚህን ኪዳን ቃሎች በጥንቃቄ ተከተሉ።
10“እናንተ ሁላችሁ መሪዎቻችሁና አለቆቻችሁ፥ ሽማግሌዎቻችሁና ሹሞቻችሁ እንዲሁም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዛሬ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ቆማችኋል፤ 11ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ፥ በሰፈራችሁም ያለ እንጨትህን የሚቆርጥ ውኃህንም የሚቀዳ መጻተኛ አብረውህ ቆመዋል። 12እዚህ የቆምኸው ጌታ ዛሬ ከአንተ ጋር ወደሚያደርገውና በመሓላ ወደሚያጸናው ኪዳን ከጌታህ ከእግዚአብሔር ጋር ትገባ ዘንድ፥ 13ለአንተ በሰጠው ተስፋና ለአባቶችህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በማለላቸው መሠረት እርሱ አምላክህ ይሆን ዘንድ፥ አንተም ሕዝቡ መሆንህን፥ በዛሬው ዕለት ለማረጋገጥ ነው።
14“እኔም ይህን የመሓላ ኪዳን የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤ 15ነገር ግን ዛሬ በአምላካችን በጌታ ፊት ከእኛ ጋር በዚህ ከሚቆም ሰው ጋር እንዲሁም ዛሬም ከእኛ ጋር በዚህ ከሌለ ሰው ጋር ነው።
16“በግብጽ ምድር እንዴት እንደ ኖርንና ወደዚህ ስንመጣም በየአገሮቹ ውስጥ እንዴት እንዳለፍን ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 17በመካከላቸውም አስጸያፊ ምስሎቻቸውንና የዕንጨትና የድንጋይ፥ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን አይታችኋል። 18#ዕብ. 12፥15።የእነዚህን ሕዝቦች አማልክት ለማምለክ ልቡን ከጌታ ከእግዚአብሔር የሚመልስ ወንድም ሆነ ሴት ቤተሰብም ሆነ ነገድ ዛሬ ከመካከላችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ከመካከልህ እንዲህ ያለውን መርዘኛና መራራ የሆነ ፍሬ የሚያበቅል አይገኝባችሁ። 19እንደዚህ ያለው ሰው የዚህን መሐላ ቃል በሚሰማበት ጊዜ፥ በልቡ ራሱን በመባረክ፥ ‘ምንም እንኳ እንደ ልቤ ደንዳናነት ብሄድ ሰላም አለኝ’ ብሎ ያስባል። ይህም በለምለሙም ሆነ በደረቁ መሬት ላይ ጥፋትን ያመጣል። 20ጌታ በእርሱ ላይ ቁጣውና ቅናቱ ይነድበታል እንጂ ለዚያ ሰው ፈጽሞ ይቅርታ አያደርግም። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ርግማን ሁሉ ይወርድበታል፤ ጌታ ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል። 21በዚህ የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው የኪዳኑ ርግማን መሠረት ጌታ እርሱን ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል።
22“የሚቀጥለው ትውልድ ከእናንተ በኋላ የሚተኩት ልጆቻችሁና ከሩቅ አገር የሚመጡ እንግዶች በምድሪቱ የደረሰውን ታላቅ መቅሠፍትና ጌታ ያመጣባቸውን በሽታዎች ያያሉ። 23#ዘፍ. 19፥24፤25።ምድርም በሁለንተናዋ ዲንና ጨው፥ ዐመድም እንደ ሆነች፥ እንዳይዘራባት፥ እንዳይበቅልባትም፥ ማናቸውም ሣር እንዳይወጣባት፥ ጌታ በታላቅ ቁጣና መዓቱ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ፥ እንደ አዳማና ጺባዮ እንደ ሆነች ባዩ ጊዜ፥ 24አሕዛብም ሁሉ፥ ‘ጌታ በዚች ምድር ላይ ይህን ለምን አደረገባት? ይህ አስፈሪ ቁጣስ ንዴት ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። 25ሰዎችም እንዲህ ይላሉ፦ ‘የአባቶቻቸው አምላክ ጌታ ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር የገባውን ኪዳን ትተዉ፥ 26ወጥተውም የማያውቋቸውን፥ እርሱም ያላዘዛቸውን ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም። 27ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ርግማን ሁሉ እስኪያመጣ ድረስ የጌታ ቁጣ በዚህች ምድር ላይ ነደደ። 28በቁጣና በመቅሠፍት፥ በታላቅም መዓት ጌታ ከምድራቸው ነቀላቸው፤ ወደ ሌላም ምድር ጣላቸው። ዛሬም በዚያው ይገኛሉ።’
29“ምስጢሩ ለአምላካችን ለጌታ ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ እንድንከተል ለዘለዓለም ለእኛና ለልጆቻችን ነው።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 29: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ